ሌሎችን ማሳመን የሚቻለው እንዴት ነው?
1 ሐዋርያው ጳውሎስ በአገልግሎቱ የሚያሳምን ሰው እንደነበር ይነገርለታል። (ሥራ 19:26) ንጉሥ አግሪጳ እንኳ ሳይቀር “በጥቂት ክርስቲያን ልታደርገኝ [“ልታሳምነኝ፣” NW ] ትወዳለህ” ብሎታል። (ሥራ 26:28) ጳውሎስ በአገልግሎቱ ሰዎችን የሚያሳምን እንዲሆን የረዳው ምንድን ነው? የመወያያ ነጥቦቹን ከአድማጮቹ ሁኔታ ጋር እያስማማ ከቅዱሳን ጽሑፎች ምክንያቱን እየጠቀሰ ያስረዳ ስለነበር ነው።—ሥራ 28:23
2 እኛም የጳውሎስን ምሳሌ በመኮረጅ በአገልግሎታችን ሌሎችን የምናሳምን መሆን አለብን። እንዴት? ለሌሎች በምንናገርበትና እነርሱም የሚሉትን በምንሰማበት ጊዜ ማስተዋልን በመጠቀም ነው። (ምሳሌ 16:23 NW ) ይህን ለማድረግ የሚረዱ ሦስት ጠቃሚ እርምጃዎችን እንመልከት።
3 በጥንቃቄ አዳምጡ:- ሰውዬው በሚናገርበት ጊዜ የምትስማሙባቸውን የጋራ ነጥቦች ለማግኘት አዳምጡ። የተቃውሞ ሐሳብ ከሰነዘረ የተቃወመበትን ምክንያት ለማስተዋል ጥረት አድርጉ። እንዲህ ማድረጋችሁ ምን እንደሚያምን፣ ለምን እንደሚያምንበትና እንዲያምን ያደረገው ነገር ምን እንደሆነ በትክክል እንድታውቁ ይረዳችኋል። (ምሳሌ 18:13) በዘዴ ሐሳቡን እንዲገልጽ አድርጉ።
4 ጥያቄዎችን ጠይቅ:- አንድ ሰው በሥላሴ እንደሚያምን ቢናገር “ከድሮም ጀምሮ በሥላሴ ታምን ነበር?” የሚል ጥያቄ ልታቀርብለት ትችላለህ። በማስከተልም “መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን እንደሚል ለማወቅ ጥልቅ ጥናት አድርገሃል?” ልትል ትችላለህ። እንዲሁም “እግዚአብሔር የሥላሴ ክፍል ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽና በቀጥታ ሊነግረን አይገባም ነበር?” ብለህ መጠየቅ ትችላለህ። ሰውዬው የሚሰጠው መልስ ቅዱሳን ጽሑፎችን በመጠቀም ከግለሰቡ ጋር ምክንያታዊ ውይይት ለማድረግ ይረዳሃል።
5 አሳማኝ ምክንያት አቅርብ:- አንድ የይሖዋ ምሥክር ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው ብላ ለምታምን ለአንዲት ሴት ‘ሁለት ሰዎች እኩል መሆናቸውን ልታስተምሪኝ ብትፈልጊ የትኛውን የቤተሰብ ዝምድና በምሳሌነት ትጠቀሚያለሽ?’ የሚል ጥያቄ አቀረበላት። ሴትየዋም “የሁለት ወንድማማቾችን ምሳሌ እጠቀም ይሆናል” ስትል መለሰች። አክሎም “ምናልባትም ተመሳሳይ መንቲያዎችን ልትጠቀሚ ትችያለሽ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እንደ አባት ራሱን ደግሞ እንደ ልጅ እንድንመለከታቸው ሲያስተምረን ምን መልእክት እያስተላለፈ ነበር?” አላት። ሴትየዋ አንደኛው በዕድሜና በስልጣን እንደሚበልጥ እየገለጸ እንደነበር ተረዳች። (ማቴ. 20:23፤ ዮሐ. 14:28፤ 20:17) የማሳመን ችሎታው አእምሮዋንና ልቧን መንካት ችሏል።
6 እርግጥ ነው፣ አቀራረባችን ምንም ያክል ምክንያታዊና ትክክል ቢሆን ሁሉም ሰው እውነትን ይቀበላል ማለት አይደለም። ሆኖም እንደ ጳውሎስ የመንግሥቱን መልእክት እንዲቀበሉ እያሳመንናቸው በአገልግሎት ክልላችን ውስጥ ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ለማግኘት እንትጋ።—ሥራ 19:8