በምታስተምሩበት ጊዜ አሳማኝ ማስረጃ አቅርቡ
1. በአገልግሎት ላይ የአምላክን ቃል ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም ሲባል ብዙ ጊዜ ምንን ይጨምራል?
1 እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ያሉ ውጤታማ አገልጋዮች ‘የእውነትን ቃል በአግባቡ መጠቀም’ ሲባል ከቅዱሳን መጻሕፍት ጥቅሶችን መጥቀስ ማለት ብቻ እንዳልሆነ ይገነዘባሉ። (2 ጢሞ. 2:15) የአምላክን ቃል ተጠቅመን በምናስተምርበት ጊዜ “አሳማኝ ማስረጃ” ማቅረብ የምንችለው እንዴት ነው?—ሥራ 28:23
2. ሰዎች ለአምላክ ቃል ያላቸውን አክብሮት ለማሳደግ ምን ማድረግ እንችላለን?
2 የአምላክ ቃል ይናገር፦ በመጀመሪያ ደረጃ የምናነጋግረው ሰው መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ጥበብ እንደያዘ እንዲገነዘብ በሚያደርግ መንገድ ተናገሩ። በአምላክ ቃል ላይ ያለን የመተማመን ስሜት የምናነጋግረው ሰው የሚነበበውን ጥቅስ በትኩረት እንዲከታተል ሊያነሳሳው ይችላል። (ዕብ. 4:12) ምናልባት እንዲህ ልንል እንችላለን፦ “ይህን ጉዳይ በሚመለከት አምላክ ምን አመለካከት እንዳለው ማወቁ ጠቃሚ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። እስቲ ቃሉ ምን እንደሚል ልብ ይበሉ።” ሁኔታው አመቺ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ ከአምላክ ቃል ላይ በቀጥታ በማንበብ ቃሉ ራሱ እንዲናገር አድርጉ።
3. አንድን ጥቅስ ካነበብን በኋላ የምናነጋግረው ሰው ትርጉሙን እንዲረዳ ምን ማድረግ እንችላለን?
3 በሁለተኛ ደረጃ ላነበባችሁት ጥቅስ ማብራሪያ ስጡ። ብዙ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የተነበበላቸውን ጥቅስ መረዳት ይቸግራቸዋል። ብዙ ጊዜ ጥቅሱ ካነሳነው ርዕሰ ጉዳይ ጋር እንዴት እንደሚያያዝ ማብራራት አስፈላጊ ነው። (ሉቃስ 24:26, 27) በጥቅሱ ውስጥ ያሉትን ቁልፍ ቃላት ለዩ። የምናነጋግረው ግለሰብ የጥቅሱን ሐሳብ መረዳቱን ለማወቅ ጥያቄ መጠየቅ ሊረዳ ይችላል።—ምሳሌ 20:5፤ ሥራ 8:30
4. አሳማኝ ማስረጃ እያቀረብን በምናስተምርበት ጊዜ ልንወስደው የሚገባው ሦስተኛ እርምጃ ምንድን ነው?
4 ከቅዱሳን መጻሕፍት እየጠቀሱ ማወያየት፦ በሦስተኛ ደረጃ ልቡን ለመንካት ጥረት አድርጉ። የቤቱ ባለቤት ጥቅሱን በግለሰብ ደረጃ እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚችል እንዲገነዘብ እርዱት። ከቅዱሳን መጻሕፍት እየጠቀስን ማስረዳታችን፣ አንድ ሰው አመለካከቱን እንዲለውጥ ሊያደርገው ይችላል። (ሥራ 17:2-4፤ 19:8) ለምሳሌ ያህል፣ ዘፀአት 6:3ን [የ1879 ትርጉም] ካነበብን በኋላ ለቤቱ ባለቤት ከአንድ ሰው ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት ስሙን ማወቅ ምን ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ልናስረዳው እንችላለን። ምናልባትም “የአምላክን ስም ማወቅህ ለእሱ የምታቀርበውን ጸሎት ይበልጥ ትርጉም ያለው እንዲሆን የሚያደርግ አይመስልህም?” ብለን ልንጠይቀው እንችላለን። በዚህ መንገድ ጥቅሱን ከሰውየው የግል ሕይወት ጋር ማዛመዳችን ጥቅሱ ያለውን ጠቀሜታ ጎላ አድርጎ ለመግለጽ ይረዳል። ከአምላክ ቃል ላይ አሳማኝ ማስረጃ እያቀረብን በዚህ መንገድ ማስተማራችን ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች እውነተኛና ሕያው አምላክ ወደሆነው ወደ ይሖዋ እንዲሳቡ ያደርጋቸዋል።—ኤር. 10:10