ፍቅር እንድንሰብክ ይገፋፋናል
1 እኛ የይሖዋ ምሥክሮች ይበልጥ የምንታወቀው ቀናተኛ የመንግሥቱ ሰባኪዎች በመሆናችን ነው። (ማቴ. 24:14) በመላው ዓለም ከስድስት ሚልዮን በላይ አስፋፊዎች ያሉ ሲሆን አዲሶች ከእኛ ጋር መስበክ ሲጀምሩ ይህ ቁጥር እየጨመረ ይሄዳል። ቁጥሩ ይህን ያህል ነው የሚባለው በሥራው ላይ ተሳትፎ ማድረጋቸውን መሠረት በማድረግ ነው።
2 ይህን ፈታኝ ሥራ እንድንሠራ የሚገፋፋን ምንድን ነው? ተገድደን፣ በጥቅም ተደልለን ወይም የተለየ ክብር ስለምናገኝ አይደለም። ብዙዎቻችን መጀመሪያ ላይ እንደማንበቃ ተሰምቶን ፈራ ተባ ብለን የነበረ ሲሆን የሰዎችም ምላሽ ብዙውን ጊዜ በጎ አልነበረም። (ማቴ. 24:9) ብዙ ሰዎች ይህን ሥራ እንድንሠራ የሚገፋፋን ምን እንደሆነ ጨርሶ አይገባቸውም። በሥራው እንድንጸና ግድ የሚለን አንድ ነገር መኖር አለበት።
3 ፍቅር ያለው ኃይል:- ኢየሱስ ‘በፍጹም ልባችን፣ በፍጹም ነፍሳችን፣ በፍጹም አሳባችንና በፍጹም ኃይላችን ይሖዋን’ መውደድ እንዳለብን በተናገረ ጊዜ ከሁሉም የሚበልጠውን ትእዛዝ ለይቶ ገልጿል። (ማር. 12:30) ይሖዋን የምናፈቅረው ማንነቱንና ምንነቱን ይኸውም ‘ክብር፣ ውዳሴ፣ ኃይል ሊቀበል የሚገባው’ ሉዓላዊ ገዥ እንዲሁም የሁሉም ነገሮች ፈጣሪ መሆኑን በጥልቅ ስለምናደንቅ ነው። (ራእይ 4:11) አስደናቂ ባሕርያቱ ምንም አቻ አይገኝላቸውም።—ዘጸ. 34:6, 7
4 ይሖዋን ማወቃችንና እሱን ማፍቀራችን ብርሃናችንን በሰዎች ፊት እንድናበራ ይገፋፋናል። (ማቴ. 5:16) በሕዝብ ፊት ስናወድሰው፣ ስለ ድንቅ ሥራዎቹ ለሌሎች ስንናገርና የመንግሥቱን መልእክት ስናሰራጭ ብርሃናችን ይበራል። በሰማይ መካከል ሲበር እንደታየው መልአክ እኛም ‘ለሕዝብ፣ ለነገድ፣ ለቋንቋ ለወገን የምንሰብከው የዘላለም ወንጌል’ አለን። (ራእይ 14:6) ዓለም አቀፉን የስብከት ሥራችንን እንድናከናውን የሚገፋፋን ኃይል ፍቅር ነው።
5 ዓለም ስብከታችን ቦታ ሊሰጠው የማይገባ ‘የሞኝ’ ሥራ እንደሆነ አድርጎ ይመለከተዋል። (1 ቆሮ. 1:18) ሥራችንን ለማስቆም ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። ታማኝ ፍቅራችን እኛም እንደ ሐዋርያት “እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም። . . . ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” ብለን በድፍረት እንድንናገር ያበረታናል። (ሥራ 4:20፤ 5:29) የስብከቱ ሥራ ተቃውሞ ቢያጋጥመውም በመላው ምድር ላይ መስፋፋቱን ቀጥሏል።
6 ለይሖዋ ያለን ፍቅር ስለ በጎነቱ በስፋት እንድንናገር የሚያደርገን ልክ በውስጣችን እንደሚነድድ እሳት ነው። (ኤር. 20:9፤ 1 ጴጥ. 2:9) ‘ታላቅ ሥራውን ለሕዝብ ማስታወቃችንን’ እንቀጥላለን!—ኢሳ. 12:4, 5