የጥያቄ ሣጥን
◼ ተጨማሪ የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት ቡድን ማቋቋም ተገቢ የሚሆነው መቼ ነው?
አዲስ የመጽሐፍ ጥናት ቡድን ማቋቋም አስፈላጊ የሚሆነው በመንግሥት አዳራሽ የሚደረገውን ጨምሮ እያንዳንዱ የመጽሐፍ ጥናት ቡድን 15 ወይም ከዚያ ጥቂት ያነሱ ተሰብሳቢዎች እንዲኖሩት ለማድረግ ሲባል ነው። ይህ እንዲሆን የሚፈለገው ለምንድን ነው?
የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት ቡድኖች አነስተኛ የተሰብሳቢ ቁጥር እንዲኖራቸው መደረጉ የቡድኑ መሪ ለእያንዳንዱ ተሰብሳቢ ትኩረት እንዲሰጥ ያስችለዋል። ከዚህም በተጨማሪ ሁሉም በዚያ የሚኖረውን አመቺ ሁኔታ ተጠቅመው ስለሚያምኑበት ነገር በሰዎች ፊት የመናገር ሰፊ አጋጣሚ ይከፍትላቸዋል። (ዕብ. 10:23፤ 13:15) በጉባኤው የአገልግሎት ክልል ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች አነስተኛ ተሰብሳቢዎች ያሏቸው ቡድኖች መኖራቸው በመጽሐፍ ጥናት እንዲሁም በመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ ላይ መገኘቱን ይበልጥ አመቺ ያደርገዋል። የመጽሐፍ ጥናት ቡድኖቻቸውን ቁጥር የጨመሩ ጉባኤዎች አጠቃላዩ የመጽሐፍ ጥናት ተሰብሳቢዎች ቁጥር ከፍ እንዳለ አስተውለዋል።
የተሰብሳቢ ቁጥሩ ከዚህም ያነሰ ሊሆን ቢችልም ሌላ የመጽሐፍ ጥናት ቡድን ማቋቋም አስፈላጊ የሚሆንባቸው የተለዩ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙ ይችላሉ። በገለልተኛ ክልል ውስጥ ወይም ደግሞ አሁን ያለው መሰብሰቢያ በሚጠብበት ወይም መቀመጫ በሚያንስበት ጊዜ እንደዚያ ማድረግ ሊያስፈልግ ይችል ይሆናል። አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ለአረጋውያን፣ ለምሽት ፈረቃ ሠራተኞች ወይም የይሖዋ ምሥክር ያልሆነ ባል ላላቸው እህቶች ጥቅም ሲባል ቀን የሚደረግ የመጽሐፍ ጥናት ቡድን ማቋቋም ይቻላል።
እያንዳንዱ የመጽሐፍ ጥናት ቡድን በመንፈሳዊ ጠንካራና ንቁ የሆኑ አስፋፊዎች እንዲሁም ጥሩ ችሎታ ያለው መሪና አንባቢ ሊኖሩት ይገባል። በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንድሞች እነዚህን ኃላፊነቶች ለመሸከም ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል።
ሽማግሌዎች እያንዳንዱ የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት ቡድን መጠነኛ የሆነ የተሰብሳቢ ቁጥር እንዳለው፣ ጥሩ መንፈሳዊ እንክብካቤ እንደሚደረግለትና አመቺ መሰብሰቢያ ቦታ ማግኘቱን በመከታተል ለጉባኤው እድገት አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይችላሉ። ሁሉም ከዚህ ልዩ መንፈሳዊ ዝግጅት የተሟላ ጥቅም ማግኘት እንዲችሉ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ አዳዲስ የመጽሐፍ ጥናት ቡድኖች ማቋቋሙ ተገቢ ነው። ቤታችሁ የመጽሐፍ ጥናት እንዲደረግበት መፍቀድ ትችሉ ይሆን? እንዲህ ያደረጉ ብዙ ወንድሞችና እህቶች መንፈሳዊ በረከቶች አግኝተዋል።