የአውራጃ ስብሰባ—የደስታ ጊዜ!
1 የይሖዋ ምሥክሮች የሚያደርጓቸው የአውራጃ ስብሰባዎች የደስታ ጊዜያት ናቸው። እነዚህ ስብሰባዎች ከመቶ ለሚበልጡ ዓመታት በድርጅታችን ውስጥ ለተገኘው ጭማሪ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ይሖዋ አነስተኛ ከነበረው ጅምር አንስቶ ዓለም አቀፉን ሥራችንን በእጅጉ ሲባርከው ተመልክተናል። በዘመናችን በ1893 በቺካጎ ኢሊኖይስ በተደረገው የመጀመሪያ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ከተገኙት 360 ተሰብሳቢዎች መካከል 70ዎቹ ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን ለማሳየት ተጠምቀው ነበር። ባለፈው ዓመት “የአምላክ ቃል አድራጊዎች” በሚል ርዕስ በዓለም ዙሪያ ባደረግናቸው የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ በጠቅላላ 9, 454, 055 ተሰብሳቢዎች የተገኙ ሲሆን 129, 367 ሰዎች ተጠምቀዋል። ለደስታ የሚሆን እንዴት ያለ ታላቅ ምክንያት ነው!
2 ከመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አንስቶ የአምላክ ሕዝቦች የሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ከይሖዋ የሚመጣው ትምህርት ዋነኛ ማስተላለፊያ በመሆን አገልግለዋል። በዕዝራና በነህምያ ዘመን ሕዝቡ “ከማለዳ ጀምሮ እስከ ቀትር ድረስ” ሕጉ ሲነበብላቸው ያዳምጡ ነበር። (ነህ. 8:2, 3) በወቅቱ ሕዝቡ ሕጉን ይበልጥ ማስተዋል በመቻላቸው ‘ታላቅ ደስታ’ አግኝተዋል። (ነህ. 8:8, 12) የአውራጃ ስብሰባዎች ይሖዋ “በታማኝና ልባም ባሪያ” በኩል “በጊዜው” የሚያቀርብልንን ጠቃሚ ትምህርትና መንፈሳዊ ምግብ የምናገኝባቸው ዝግጅቶች በመሆናቸው እኛም ደስተኞች ነን። (ማቴ. 24:45) ኢየሱስ ሰው ለመኖር ‘ከይሖዋ አፍ የሚወጣ ቃል’ እንደሚያስፈልገው ስለተናገረ የአውራጃ ስብሰባዎች ለመንፈሳዊ ደህንነታችን በጣም አስፈላጊ ናቸው።—ማቴ. 4:4
3 በስብሰባው ላይ ለመገኘት ምንም ያህል ጥረት ብናደርግ የሚያስቆጭ አይሆንም:- ሁላችንም በዚህ ዓመት በሚደረገው “የአምላክ ቃል አስተማሪዎች” የአውራጃ ስብሰባ ላይ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ለመገኘት እቅድ ማውጣት ይገባናል። በእያንዳንዱ ዕለት ቀደም ብለን ለመድረስና የመደምደሚያው ጸሎት “አሜን!” ተብሎ እስኪቋጭ ድረስ ለመቆየት እቅድ ማውጣት ይገባናል። እንዲህ ለማድረግ ፕሮግራማችንን ማስተካከል ያስፈልገን ይሆናል። በአውራጃ ስብሰባው ላይ ለመገኘት ከመሥሪያ ቤት ፈቃድ የማግኘት ችግር ያጋጥመን ይሆናል። ከፈቀዱልኝ ይፍቀዱልኝ ብለን ችላ ማለት ሳይሆን ቁርጥ ያለ እርምጃ መውሰድ ይገባል። በስብሰባው ላይ ለመገኘት ማረፊያ እና/ወይም መጓጓዣ የሚያስፈልገን ከሆነ ቀደም ብለን ዝግጅት ማድረግ ይገባናል። ምንም ያህል ጥረት ቢጠይቅብን በኋላ የሚክስ ይሆናል!
4 የይሖዋ ሕዝቦች በአውራጃ ስብሰባ ላይ መገኘት ያለውን በረከት በብር ወይም በገንዘብ አይለውጡትም። በ1958 በኒው ዮርክ ከተማ በተደረገው መለኮታዊ ፈቃድ የተሰኘ የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ቁርጥ ውሳኔ አድርገው የነበሩ አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች ምሳሌ ተመልከት። አንድ ወንድም ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆኖ ለማገልገልና በአውራጃ ስብሰባው ላይ ለመገኘት በግንባታ ሞያ የተሰማራበትን የግል ድርጅቱን ለሁለት ሳምንት ዘግቶ ነበር። በቨርጂን ደሴቶች የሚኖር አንድ ወንድም ስድስት አባላት ያለውን መላ ቤተሰቡን ይዞ ለመሄድ አምስት ሄክታር መሬቱን ሸጧል። አንድ ወጣት ባልና ሚስት ከሁለት ወር እስከ ሰባት ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሦስት ልጆቻቸውን ወደ አውራጃ ስብሰባው ይዘው ለመሄድ የሞተር ጀልባቸውን ሸጠዋል። በካሊፎርኒያ ሦስት ወንድማማቾች ከሥራ ከቀሩ እንደሚባረሩ ተነግሯቸው ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ማስጠንቀቂያ በዚያ የማይረሳ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ከመገኘት አላገዳቸውም።
5 ይሖዋ ልባዊ ጥረታችንን ይባርካል:- ይሖዋ ሕዝቦቹ የሚያደርጉትን ጥረት ይመለከታል እንዲሁም ይባርካል። (ዕብ. 6:10) ለምሳሌ ያህል በ1950 በተደረገው የቲኦክራሲው እድገት የተባለ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ተገኝተው የነበሩ ሰዎች “አዲስ የነገሮች ሥርዓት” የሚል ታሪካዊ ንግግር አዳመጡ። ወንድም ፍሬደሪክ ፍራንዝ “በዚህ ዓለም አቀፍ የአውራጃ ስብሰባ ላይ የተገኘነው ሁላችን የአዲሲቱ ምድር ዕጩ መሳፍንት በዛሬዋ ምሽት በመካከላችን መኖራቸውን ማወቃችን አያስደስተንም?” የሚል ጥያቄ በማንሳት እዚያ የተገኙ ሰዎችን ፍላጎት ቀስቅሷል። ከ50 ከሚበልጡ ዓመታት በኋላም ዛሬ ስለ መዝሙር 45:16 ያገኘነው ግልጽ መረዳት ለደስታ ምክንያት ሆኖልናል።
6 አንድ የቤተሰብ ራስ ባለፈው ዓመት በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ከተገኘ በኋላ እንደሚከተለው ሲል የአድናቆት ደብዳቤ ጽፏል:- “ወንድሞች፣ ይህ የአውራጃ ስብሰባ ምን ያህል ሕይወት አድን እንደነበር አታውቁም። ቤተሰባችን በሥራ ዝውውር ምክንያት ከተማ መኖር ሲጀምር መንፈሳዊ ሚዛናችንን ፈጽሞ መጠበቅ አቃተን። . . . ክርስቲያናዊ ግዴታዎቻችንን መወጣቱን ችላ ማለት ጀመርን። ሌላው ቀርቶ በስብሰባዎች ላይ መገኘትና በአገልግሎት መካፈል ጨርሶ አቁመን ነበር። . . . ይህ የአውራጃ ስብሰባ እንደገና ያደሰን ሲሆን መንፈሳዊ ግቦችን እያወጣንና ግቦቻችን ላይ ለመድረስ በጥሩ ሁኔታ በመደራጀት ላይ እንገኛለን።”
7 ይሖዋ የሚያስፈልገንን መንፈሳዊ ምግብ በማቅረብ ላይ ነው። በአውራጃ ስብሰባዎቻችን አማካኝነት የተትረፈረፈ ገበታ ያዘጋጅልናል። ለዚህ ዝግጅት ያለን አድናቆት ቆርኔሌዎስ ሐዋርያው ጴጥሮስ መጥቶ ከጎበኘው በኋላ “እንግዲህ አንተ ከእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዝኸውን ሁሉ እንድንሰማ እኛ ሁላችን አሁን በእግዚአብሔር ፊት በዚህ አለን” በማለት እንደተናገረው እንድንል ሊያደርገን ይገባል። (ሥራ 10:33) በዚህ ዓመት “የአምላክ ቃል አስተማሪዎች” በሚል ርዕስ በሚደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ “በእግዚአብሔር ፊት” መገኘቱን ግባችን በማድረግ እንደሰት!