ቅዱስ ነገሮችን ታደንቃላችሁን?
1 ቅዱስ ነገሮችን ታደንቃላችሁ? ተብለን ብንጠየቅ ፈጠን ብለን አዎን የሚል ምላሽ እንደምንሰጥ የታወቀ ነው! የምናደንቃቸው አንዳንድ ቅዱስ የአምላክ ዝግጅቶች የትኞቹ ናቸው?
2 ከሰማዩ አባታችን ጋር የተቀራረበ ወዳጅነት የመመሥረት መብት በማግኘታችን ምንኛ ደስተኞች ነን! እኛ ‘ወደ እሱ የምንቀርብ ከሆነ እሱም እንደሚቀርበን’ ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (ያዕ. 4:8) ማንም ቢሆን ያለ ኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት የዘላለም ሕይወት ማግኘት አይችልም። (ዮሐ. 3:16) ከልብ በመነጨ የአመስጋኝነት ስሜት ተነሳስተን በጣም ውድ ለሆነው ለዚህ የአምላክ ስጦታ ጥልቅ አድናቆት እንዳለን በየዕለቱ በጸሎት እንገልጻለን።
3 በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ የይሖዋ ምድራዊ ድርጅት ቅዱስ ናቸው። በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ስንመራ፣ እርስ በርስ ያጣመረንን የወንድማማች ፍቅር ስናጠናክር፣ ቲኦክራሲያዊውን ሥርዓት በጥንቃቄ ስንከተልና አመራር ከሚሰጡን ወንድሞች ጋር ስንተባበር ለይሖዋ ዝግጅቶች ተገቢው አድናቆት እንዳለን እናሳያለን።—1 ጴጥ. 1:22
4 በታማኝና ልባም ባሪያ አማካኝነት የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ይቀርብልናል። በዚህ ዓመት በምናደርገው “የአምላክ ቃል አድራጊዎች” የአውራጃ ስብሰባ ላይ ይህ በተግባር ሲገለጽ እናያለን። በስብሰባው ላይ ስንገኝ በእጅጉ የሚያስፈልገንን ጠቃሚ መመሪያ እናገኛለን እንዲሁም ከወንድሞቻችን ጋር ሞቅ ያለ ወዳጃዊ ስሜት እንለዋወጣለን። ቅዱስ ለሆነው ለዚህ ዝግጅት ልባዊ አድናቆት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
5 የይሖዋን ቤት ቸል አትበሉ:- ነህምያ የኢየሩሳሌምን ግንብ መልሰው ለመገንባት ተግተው የሚሠሩትን ሰዎች ‘የአምላካቸውን ቤት ቸል እንዳይሉ’ በጥብቅ አሳስቦ ነበር። (ነህ. 10:39) በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ “ቤት” የሚባለው እሱ ለአምልኮ ያወጣው ዝግጅት ነው። የአውራጃ ስብሰባዎቻችን የዚህ ዝግጅት አካል ናቸው። ለዝግጅቱ ቸልተኞች እንዳልሆንን ይልቁንም ከፍ ያለ አድናቆት እንዳለን ለይሖዋ ለማሳየት በስብሰባው ላይ መገኘትና በትኩረት መከታተል ይገባናል። (ዕብ. 10:24, 25) ለዚህ ቅዱስ ዝግጅት ልባዊ አድናቆት እንዳለን ለማሳየት ከወዲሁ ምን እቅዶች ማውጣት ይገባናል?
6 ሦስቱንም ቀን ተገኙ:- ሁላችንም በአውራጃ ስብሰባው ላይ ሦስቱንም ቀን ለመገኘት እቅድ ማውጣት ይገባናል። በእያንዳንዱ ዕለት ቀደም ብላችሁ ለመገኘትና እሁድ ቀን የመደምደሚያ ጸሎት እስኪቀርብ ለመቆየት እቅድ አውጥታችኋል? እንደዚያ ከሆነ ታላቅ በረከት ታገኛላችሁ። በአውራጃ ስብሰባ ላይ መገኘት ሁልጊዜ ቀላል ላይሆን ይችላል። ከመሥሪያ ቤት የዕረፍት ጊዜ ለመውሰድ ቁርጥ ያለ አቋም መያዝ ሳይጠይቅባችሁ አይቀርም። ትራንስፓርት ሁልጊዜ እንዳሰብነው ላይገኝ ይችላል። ሆኖም እነዚህ ችግሮች በአውራጃ ስብሰባው ላይ ከመገኘት እንዲያግዷችሁ አትፍቀዱ።
7 የሚከተለውን ግሩም ምሳሌ ተመልከቱ:- ባለፈው ዓመት የእርስ በርስ ጦርነት በሚካሄድበት አንድ የአፍሪካ አገር ውስጥ ወንድሞች በአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት በጉዞ ላይ እያሉ ወታደሮች አጋጠሟቸው። ወታደሮቹ “ለመሆኑ እናንተ እነማን ናችሁ፤ የምትሄዱትስ ወዴት ነው?” በማለት ጠየቋቸው። ወንድሞች “የይሖዋ ምሥክሮች ነን። ወደ አውራጃ ስብሰባ እየሄድን ነው” በማለት መልስ ሰጡ። አንደኛው ወታደር እንዲህ የሚል አስተያየት ሰጠ:- “እናንተ የይሖዋ ምሥክሮች ምንም ነገር አትፈሩም። መንገዳችሁን ቀጥሉ፤ ያለአንዳች ችግር ስብሰባችሁን ታደርጋላችሁ። ይሁን እንጂ በየመንገዱ ላይ ብዙ ወታደሮች ስለሚያጋጥሟችሁ ጠንቀቅ በሉ። ምንጊዜም የመንገዱን መሃል ይዛችሁ ሂዱ! ብዙ ሰዎች ሰብሰብ ብለው ካያችሁ እናንተ የመንገዱን መሃል ይዛችሁ መሄዳችሁን ቀጥሉ!” ወንድሞች ልክ እንደተባሉት አድርገው ለስብሰባው በሰላም ደረሱ። እነዚህ ወንድሞች ለቅዱስ ነገሮች አድናቆት በማሳየታቸው በእጅጉ ተክሰዋል።
8 እኛም እምነታቸውን መኮረጅና በአውራጃ ስብሰባችን ላይ የሚቀርበው የትኛውም ክፍል እንዳያመልጠን ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ እንደምንችል ምንም ጥርጥር የለውም። በስብሰባው ላይ ለመገኘት አንዳንድ ማስተካከያዎች ማድረግ የሚያስፈልገን ከሆነ ፕሮግራሙን ሙሉ በሙሉ ለመካፈል የምናደርገውን ጥረት ይሖዋ እንደሚባርክልን በማወቅ መመሪያ እንዲሰጠን እንጠይቀው።
9 በረከቶቹን ማጨድ:- በአምላክ ቃል አማካኝነት ወደ መዳን እንደምንደርስ ስለምንገነዘብ ለቃሉ ከፍተኛ ጉጉት አለን። (1 ጴጥ. 2:2) በዚህ የአውራጃ ስብሰባ ላይ መገኘታችንና በትኩረት መከታተላችን እያንዳንዳችን በቃሉ ላይ ጠንካራ እምነት እንድንገነባና ሰይጣን የሚሰነዝርብንን ጥቃት በተሻለ ሁኔታ እንድንቋቋም ይረዳናል። እንደዚህ በማድረግ ቅዱስ ለሆኑ ነገሮች ከፍተኛ አድናቆት እንዳለንና ‘ነፍሳቸውን ለማዳን ከሚያምኑት እንጂ ከሚያፈገፍጉ’ መካከል እንዳልሆንን ለይሖዋና ለሰዎች እናሳያለን።—ዕብ. 10:39፤ 12:16፤ ምሳሌ 27:11
10 ይሖዋ አምላክ የሰማይን መስኮት የሚከፍትበትንና መንፈሳዊ በረከቶችን አትረፍርፎ የሚያፈስበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን። (ሚል. 3:10) “የአምላክ ቃል አድራጊዎች” የአውራጃ ስብሰባ ዓርብ ጠዋት ከሚኖረው መክፈቻ አንስቶ እሁድ ከሰዓት በኋላ የመደምደሚያው ጸሎት ተደርጎ “አሜን!” እስኪባል ድረስ በፕሮግራሙ ላይ ለመገኘት ግብ አውጡ። እንዲህ ካደረጋችሁ ከፍተኛ ደስታ ታገኛላችሁ!