የአውራጃ ስብሰባ—አስደሳች የአምልኮ ወቅት
1. በጥንቷ እስራኤል ይከበሩ የነበሩ በዓሎች በዘመናችን ከሚደረጉት የአውራጃ ስብሰባዎች ጋር የሚመሳሰሉት እንዴት ነው?
1 ዮሴፍ፣ ማርያም፣ ልጆቻቸውና ሌሎች ሰዎች በዓመታዊ በዓሎች ላይ ለመገኘት አዘውትረው ወደ ኢየሩሳሌም ይሄዱ ነበር። በእነዚህ ወቅቶች እነሱም ሆኑ ሌሎች የይሖዋ አምላኪዎች የዕለት ተዕለት ጭንቀቶቻቸውን ወደ ጎን በመተው በጣም አስፈላጊ በሆኑት መንፈሳዊ ነገሮች ላይ ትኩረት ያደርጉ ነበር። እነዚህ የበዓል ወቅቶች ስለ ይሖዋ ጥሩነት ለመናገርና በዚያ ላይ ለማሰላሰል እንዲሁም ስለ ሕጎቹ ለማሰብ የሚያስችል አጋጣሚ ይከፍቱላቸው ነበር። መጪው የአውራጃ ስብሰባ እኛም በይሖዋ አምልኮ አስደሳች ወቅት እንድናሳልፍ ተመሳሳይ አጋጣሚ ይከፍትልናል።
2. ለሚመጣው አውራጃ ስብሰባ ለመዘጋጀት ምን ማድረግ ይኖርብናል?
2 ዝግጅት አስፈላጊ ነው፦ የኢየሱስ ቤተሰቦች ከናዝሬት ወደ ኢየሩሳሌም ደርሶ ለመመለስ 200 ኪሎ ሜትር በእግራቸው መጓዝ ይጠይቅባቸው ነበር። ኢየሱስ ምን ያህል ወንድሞችና እህቶች እንዳሉት ባናውቅም ዮሴፍና ማርያም እቅድ ማውጣትና ብዙ ጥረት ማድረግ እንደሚጠይቅባቸው መገመት እንችላለን። እናንተስ በሚመጣው አውራጃ ስብሰባ ላይ ሦስቱንም ቀን ለመገኘት አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጋችኋል? ይህ ደግሞ ከመሥሪያ ቤታችሁ እረፍት መውሰድ ወይም ፈቃድ ለማግኘት አሠሪያችሁን አሊያም የልጃችሁን አስተማሪ ማነጋገር ሊጠይቅባችሁ ይችላል። ሆቴል የምታርፉ ከሆነ ክፍል እንዲያዝላችሁ ዝግጅት አድርጋችኋል? ከጉባኤያችሁ የተለየ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው አስፋፊዎች በአውራጃ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ቅድሚያውን ወስደህ መርዳት ትችላለህ?—1 ዮሐ. 3:17, 18
3. እስራኤላውያን ያከብሯቸው የነበሩ በዓሎች የሚያንጽ ወዳጅነት ለመመሥረት አጋጣሚ የሚፈጥሩት እንዴት ነበር?
3 የሚያንጽ ወዳጅነት፦ አይሁዳውያን ያከብሯቸው የነበሩ በዓሎች ከሌሎች የእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር ለመቀራረብ የሚያስችል ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥሩላቸው ነበር። የኢየሱስ ቤተሰቦች ከድሮ ጓደኞቻቸው ጋር እንደገና ለመገናኘት ይጓጉ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። በተጨማሪም በበዓሉ ላይ ወይም በጉዞ ወቅት ከሚያገኟቸው አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች ጋር አዲስ ወዳጅነት ለመመሥረት የሚያስችል አጋጣሚ ይፈጥርላቸው ነበር።
4. አንድነት ያለውን ክርስቲያናዊ የወንድማማች ማኅበር አቅልለን እንደማንመለከተው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
4 ታማኝና ልባም ባሪያ በአውራጃ ስብሰባ ላይ የሚቀርቡ ንግግሮችን በጽሑፍ መልክ ከማዘጋጀት ይልቅ አንድ ላይ ተሰብስበን እንድናዳምጥ የሚያደርገው እርስ በርስ እንድንበረታታ ለማድረግ ነው። (ዕብ. 10:24, 25) በመሆኑም በእያንዳንዱ ቀን የመድረኩ ሊቀ መንበር ፕሮግራሙ ሊጀመር እንደሆነ የሚጠቁመውን ሙዚቃ ከማስተዋወቁ በፊት ከሌሎች ጋር መጨዋወት እንድትችሉ ቀደም ብላችሁ ለመድረስ እቅድ አውጡ። በምሳ ሰዓት ላይ ምግብ ፍለጋ የስብሰባውን ቦታ ለቀን ከመውጣት ይልቅ ቀለል ያለ ምግብ ይዘን በመምጣት እዚያው ስብሰባው ቦታ ቆይተን ከሌሎች ወንድሞቻችን ጋር እንድንተዋወቅና እንድንጨዋወት ማበረታቻ ተሰጥቶናል። አንድነት ያለው ክርስቲያናዊ የወንድማማች ማኅበር አቅልለን ልናየው የማይገባ ውድ የይሖዋ ስጦታ ነው።—ሚክ. 2:12
5. ከፕሮግራሙ ሙሉ ጥቅም ለማግኘት ምን ሊረዳን ይችላል?
5 የመማሪያ ጊዜ፦ ኢየሱስ ከልጅነቱ ጀምሮ በዓላት የሚከበሩባቸውን ወቅቶች በሰማይ ስለሚኖረው አባቱ ለመማር ይጠቀምባቸው ነበር። (ሉቃስ 2:41-49) እኛም ሆንን ቤተሰቦቻችን በስብሰባው ላይ ከሚቀርቡት ክፍሎች ሙሉ ጥቅም ለማግኘት ምን ሊረዳን ይችላል? ስብሰባው በሚካሄድበት ወቅት ከቦታችሁ አትነሱ፤ እንዲሁም ሳያስፈልግ ወሬ ከማውራት ተቆጠቡ። የሞባይል ስልካችሁ ወይም ሌሎች ተመሳሳይ መሣሪያዎች እናንተንም ሆነ ሌሎችን እንዳይረብሹ አስፈላጊውን ጥንቃቄ አድርጉ። ትኩረታችሁን በተናጋሪው ላይ አድርጉ፤ እንዲሁም አጫጭር ማስታወሻዎችን ያዙ። ልጆቻችሁ ትምህርቱን እየተከታተሉ እንደሆነ መቆጣጠር እንድትችሉ በቤተሰብ አንድ ላይ ተቀመጡ። ምሽት ላይ ትንሽ ጊዜ ወስዳችሁ በተማራችኋቸው ነጥቦች ላይ ተወያዩ።
6. አለባበስና አጋጌጥን በተመለከተ ምን ነገር ልብ ልንል ይገባል?
6 አለባበስና አጋጌጥ፦ በበዓሉ ላይ ለመገኘት ይጓዙ የነበሩት የኢየሱስ ቤተሰቦችም ሆኑ ይሖዋን የሚያመልኩ ሌሎች አይሁዳውያን ሰማያዊ ጥለትና ዘርፍ ያለው ልብስ ይለብሱ ስለነበር በጉዞ ላይ ያሉ የውጭ አገር ነጋዴዎች በቀላሉ ይለዩአቸው ነበር። (ዘኍ. 15:37-41) ክርስቲያኖች ለየት ያሉ ልብሶችን ባይለብሱም ልከኛ፣ ሥርዓታማና ንጹሕ ልብስ በመልበሳችን ተለይተን እንታወቃለን። ራቅ ካለ አካባቢ ስብሰባ ወደሚካሄድበት ከተማ በምንጓዝበትና ከዚያ በምንመለስበት ጊዜ እንዲሁም ከተማው ውስጥ በምንቆይበት ጊዜ ለአለባበሳችን ተገቢውን ትኩረት መስጠት ይኖርብናል። ከፕሮግራሙ በኋላ ልብስ መቀየር ቢያስፈልገን እንኳ የሚያስከብር አለባበስ ሊኖረን እንዲሁም ባጅ ልናደርግ ይገባናል። እንዲህ ማድረጋችን የይሖዋ ምሥክር ካልሆኑ ሰዎች እንድንለይ እንዲሁም የሚመለከቱን ሰዎች ለእኛ ጥሩ ግምት እንዲያድርባቸው ያደርጋል።
7. በአውራጃ ስብሰባ ላይ ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆኖ የመሥራቱን ጉዳይ ልናስብበት የሚገባው ለምንድን ነው?
7 ፈቃደኛ ሠራተኞች ያስፈልጋሉ፦ የአውራጃ ስብሰባው በተቃና ሁኔታ መከናወን እንዲችል በርካታ ፈቃደኛ ሠራተኞች ያስፈልጋሉ። በሥራው ለመካፈል ራሳችሁን በፈቃደኝነት ማቅረብ ትችላላችሁ? (መዝ. 110:3) በአውራጃ ስብሰባ ላይ የሚሠሩ ሥራዎች የቅዱስ አገልግሎት ክፍል ከመሆናቸውም በላይ ግሩም ምሥክርነት ይሰጣሉ። የአንድ ስብሰባ ቦታ ሥራ አስኪያጅ፣ ሕንፃውን ባጸዱት ፈቃደኛ ሠራተኞች በጣም በመገረሙ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “እስካሁን ድረስ በዚህ ሕንፃ ውስጥ ሲካሄዱ ካየኋቸው ሁሉ ይበልጥ አስደናቂ ለሆነው ለዚህ ዝግጅት ላመሰግናችሁ እወዳለሁ። የይሖዋ ምሥክሮች የተለያችሁ ሰዎች እንደሆናችሁና በድርጅታችን ውስጥ የተሰበሰባችሁበትን ቦታ ከተረከባችሁበት ሁኔታ በበለጠ ንጹሕ አድርጋችሁ እንደምታስረክቡ ሲነገር ሁልጊዜ እሰማ ነበር። እናንተም ሆናችሁ ድርጅታችሁ ይህን ቦታ ለአካባቢው ኅብረተሰብ የተሻለ ሥፍራ እንዲሆን አድርጋችኋል፤ ይህንንም ያደረጋችሁት እስከ ዛሬ ካገኘናቸው ሁሉ እጅግ ሥርዓታማ የሆኑ ሰዎችን ተጠቅማችሁ በመሆኑ በጣም ደስ ብሎናል።”
8. ስብሰባው በሚደረግበት ከተማ ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ምሥክርነት ለመስጠት ምን አጋጣሚ አለ?
8 ለመመሥከር የሚያስችሉ አጋጣሚዎች፦ የአውራጃ ስብሰባው በሚደረግበት ከተማ የሚኖሩ በርካታ ሰዎች ጥሩ አለባበስና አጋጌጥ ያላቸው ባጅ ያደረጉ ሰዎች ሲመለከቱ ስለ እነዚህ ሰዎች የማወቅ ፍላጎት እንደሚያድርባቸው የታወቀ ነው፤ ይህ ደግሞ ስለ ስብሰባው ለመናገር አጋጣሚ ይከፍትልናል። አንድ የአራት ዓመት ልጅ ፕሮግራሙ ካለቀ በኋላ በስብሰባው ላይ የወጣውን አዲስ ጽሑፍ ይዞ ወደ አንድ ምግብ ቤት በመሄድ ለአስተናጋጇ ያሳያታል። ይህ ደግሞ የልጁ ወላጆች ሴትየዋን በስብሰባው ላይ እንድትገኝ ለመጋበዝ ጥሩ አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል።
9. የኢየሱስ ቤተሰቦች ይሖዋ ላደረገው መንፈሳዊ ዝግጅት የነበራቸውን አድናቆት መከተል የምንችለው እንዴት ነው?
9 በጥንቷ እስራኤል የበዓል ወቅቶች መንፈሳዊ አመለካከት የነበራቸው አይሁዳውያን በጉጉት የሚጠብቋቸው አስደሳች ወቅቶች ነበሩ። (ዘዳ. 16:15) የኢየሱስ ቤተሰቦች በበዓሎቹ ላይ ተገኝተው ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም ማንኛውንም መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኞች ነበሩ። እኛም አውራጃ ስብሰባዎቻችንን በሰማይ ከሚገኘው አፍቃሪ አባታችን የተሰጡን ስጦታዎች አድርገን ስለምንመለከታቸው ለእነዚህ ስብሰባዎች ተመሳሳይ የአድናቆት ስሜት አለን። (ያዕ. 1:17) ይሖዋን በደስታ ለምናመልክበት ለዚህ ዓመታዊ ስብሰባ ዝግጅት የምናደርግበት ወቅት አሁን ነው!
የአውራጃ ስብሰባ ማሳሰቢያዎች
◼ የስብሰባው ሰዓት፦ ፕሮግራሙ በሦስቱም ቀናት ከጠዋቱ 3:20 ላይ ይጀምራል። የመሰብሰቢያው ቦታ በር የሚከፈተው ከጠዋቱ 2 ሰዓት ላይ ነው። የመክፈቻው ሙዚቃ ሊጀምር እንደሆነ የሚገልጽ ማስታወቂያ ሲነገር ሁላችንም ቦታ ቦታችንን መያዝ ይኖርብናል፤ ይህም ፕሮግራሙን ክብር ባለው መንገድ ለማስጀመር ያስችላል። ፕሮግራሙ ዓርብና ቅዳሜ 10:55 እንዲሁም እሁድ 9:40 ላይ ይደመደማል።
◼ መኪና ማቆሚያ፦ አብዛኛውን ጊዜ ያለው የመኪና ማቆሚያ ውስን በመሆኑ መኪና ካለው ሰው ጋር በመሄድ የመኪናዎቹን ቁጥር መቀነስ እንችላለን። በተጨማሪም በራሳችሁ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት እባካችሁ ጥረት አድርጉ።
◼ መቀመጫ መያዝ፦ መቀመጫ መያዝ የሚቻለው ከእናንተ ጋር በመኪና ለሚመጡ፣ በአንድ ቤት አብረዋችሁ ለሚኖሩ እንዲሁም ከእናንተ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ላይ ለሚገኙ ሰዎች ብቻ መሆኑን አስታውሱ።—1 ቆሮ. 13:5
◼ ምሳ፦ በእረፍት ሰዓት ምግብ ፍለጋ ከስብሰባው ቦታ ወጥታችሁ ከመሄድ ይልቅ እባካችሁ ምሳ ይዛችሁ ኑ። በመቀመጫችሁ ሥር ሊቀመጥ የሚችል መጠነኛ ዕቃ መጠቀም ይቻላል። ትላልቅ ዕቃዎችንና ጠርሙስ ነክ ዕቃዎችን ወደ ስብሰባው ቦታ ማምጣት አይፈቀድም።
◼ መዋጮ፦ በመንግሥት አዳራሽም ሆነ በአውራጃ ስብሰባ ላይ ለዓለም አቀፉ ሥራ በፈቃደኝነት መዋጮ በማድረግ ለስብሰባው የተሰማንን አድናቆት መግለጽ እንችላለን። በአውራጃ ስብሰባው ላይ መዋጮ የሚደረጉ ቼኮች ሁሉ ለ“የይሖዋ ምሥክሮች” የሚከፈሉ መሆናቸው መገለጽ አለበት።
◼ አደጋዎችና ድንገተኛ ሕመም፦ አንድ ሰው በስብሰባው ቦታ ላይ ድንገተኛ ሕመም ካጋጠመው የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ መስጫ ክፍል የሚገኝበትን ቦታ እንዲጠቁማችሁ በቅርብ ያለውን አስተናጋጅ አነጋግሩ።
◼ ጫማ፦ በየዓመቱ ከጫማ ጋር በተያያዘ ብዙ ጉዳት ይደርሳል። በመሆኑም በደረጃዎችና እነዚህ በመሳሰሉ ቦታዎች ስትራመዱ ጉዳት እንዳይደርስባችሁ ልከኛና ምቹ የሆነ ጫማ እንድታደርጉ እናበረታታችኋለን።
◼ የመስማት ችግር ያለባቸው፦ ስብሰባው በአንዳንድ ቦታዎች በኤፍኤም የሬዲዮ ሞገድ ይተላለፋል። በዚህ ዝግጅት መጠቀም እንድትችሉ በባትሪ የሚሠራ የኤፍኤም መቀበያና የጆሮ ማዳመጫ ይዛችሁ መምጣት ያስፈልጋችኋል።
◼ የምስልና የድምፅ መቅረጫ መሣሪያዎች፦ የትኛውንም ዓይነት የመቅረጫ መሣሪያ በስብሰባው ቦታ ካለው የኤሌክትሪክ መስመር ወይም የድምፅ ማስተላለፊያ መሣሪያ ጋር ማገናኘት አይፈቀድም። እነዚህን የመሰሉ ነገሮች የምትጠቀሙ ከሆነ ሌሎች ስብሰባውን እንዳይከታተሉ በማያደናቅፍ መንገድ መጠቀም ይኖርባችኋል።
◼ የሕፃናት ጋሪዎችና የመናፈሻ ወንበሮች፦ የሕፃናት ጋሪዎችንና የመናፈሻ ወንበሮችን ወደ ስብሰባው ቦታ ይዞ መምጣት ተገቢ አይደለም። ይሁን እንጂ ከወላጆች አጠገብ ባለ ወንበር ላይ ሊታሰሩ የሚችሉ ለልጆች ደህንነት ተብለው የሚዘጋጁ ወንበሮችን (child-safety seats) ይዞ መምጣት ይቻላል።
◼ ቅጾች፦ እባካችሁ ተከታትላችሁ እርዱት (S-43) የሚለው ቅጽ በስብሰባው ላይ መደበኛ ባልሆነ መንገድ መሥክረንለት ፍላጎት ያሳየን ሰው በሚመለከት መረጃ ለመስጠት ያገለግላል። ቅጹን ከሞላችሁ በኋላ ለአውራጃ ስብሰባው የጽሑፍ ክፍል አሊያም ወደ ጉባኤያችሁ ስትመለሱ ለጉባኤው ጸሐፊ ልትሰጡት ትችላላችሁ።
◼ ምግብ ቤቶች፦ ምግብ ቤት በምትመገቡበት ጊዜ መልካም ምግባር በማሳየት የይሖዋን ስም አስከብሩ። ለአስተናጋጆች ጉርሻ ወይም ቲፕ መስጠት የተለመደ ነው።
◼ መንግሥት አዳራሾችን መጠቀም፦ የመንግሥት አዳራሾችን ለማደሪያነት ባትጠቀሙባቸው እንመርጣለን። መንግሥት አዳራሾችን ለዚህ ዓላማ መጠቀም የግድ ከሆነ ግን ሁሉም ሰው የመንግሥት አዳራሹን ምንጊዜም ንጹሕና ሥርዓታማ አድርጎ የመያዝ ኃላፊነት እንዳለበት ሊሰማው ይገባል። መተኛዎቹ በሥርዓት ተጣጥፈው መቀመጥ ይኖርባቸዋል፤ የፈሰሰ ነገር ካለ ወዲያውኑ መወልወል ይገባዋል፤ እንዲሁም ወረቀቶችና ሌሎች ቆሻሻዎች በቅርጫት ወይም በሌላ ነገር ውስጥ መሰብሰብ ይኖርባቸዋል።
◼ ጽዳት፦ የንጽሕና ክፍል የመሰብሰቢያ ቦታው በፕሮግራም እንዲጸዳ ዝግጅት የሚያደርግ ቢሆንም ሁላችንም ይሖዋ ከሕዝቦቹ የሚጠብቀውን የንጽሕና መሥፈርት ለመጠበቅ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት እንችላለን። በመሆኑም በአዳራሹ ወለል ላይም ይሁን በግቢው ውስጥ ወረቀት ወይም ሌላ ቆሻሻ መጣል ተገቢ አይደለም። ቆሻሻዎች ለዚያ ዓላማ በተዘጋጁ ቅርጫቶች ውስጥ መጣል ይኖርባቸዋል። እንዲህ የሚደረግ ከሆነ የአውራጃ ስብሰባው የሚካሄድበት ቦታ በፕሮግራሙ ወቅትም ሆነ በእረፍት ሰዓት የተዝረከረከ አይሆንም። በተጨማሪም ከተቀመጥንበት ቦታ ስንነሳ የወደቀ ነገር ካለ ለማንሳት ዞር ዞር ብለን አካባቢውን መመልከታችን የሚያስመሰግን ነው።
◼ የፈቃደኛ አገልግሎት፦ ፈቃደኛ ሠራተኞች ሆነን አስፈላጊ ሥራዎች የምናከናውን ከሆነ በአውራጃ ስብሰባው ላይ የምናገኘው ደስታ እጥፍ ድርብ ይሆናል። (ሥራ 20:35) ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆነው ማገልገል የሚፈልጉ ሁሉ በስብሰባው ቦታ ለሚገኘው የፈቃደኛ አገልግሎት ክፍል ማሳወቅ ይኖርባቸዋል። ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች በወላጅ አሊያም ወላጅ በሚመድብላቸው ሞግዚት ወይም ሌላ ትልቅ ሰው ሥር በመሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ።
[በገጽ 6, 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የአውራጃ ስብሰባ ማሳሰቢያዎች
◼ የስብሰባው ሰዓት፦ ፕሮግራሙ በሦስቱም ቀናት ከጠዋቱ 3:20 ላይ ይጀምራል። የመሰብሰቢያው ቦታ በር የሚከፈተው ከጠዋቱ 2 ሰዓት ላይ ነው። የመክፈቻው ሙዚቃ ሊጀምር እንደሆነ የሚገልጽ ማስታወቂያ ሲነገር ሁላችንም ቦታ ቦታችንን መያዝ ይኖርብናል፤ ይህም ፕሮግራሙን ክብር ባለው መንገድ ለማስጀመር ያስችላል። ፕሮግራሙ ዓርብና ቅዳሜ 10:55 እንዲሁም እሁድ 9:40 ላይ ይደመደማል።
◼ መኪና ማቆሚያ፦ አውራጃ ስብሰባ በሚደረግባቸው ቦታዎች ላይ የመኪና ማቆሚያው በእኛ ሥር ከሆነ ተሰብሳቢዎቹ በሙሉ እንደ እንደሚመጡበት ቅደም ተከተል ያለምንም ክፍያ ይስተናገዳሉ። ለአካል ጉዳተኞች በተዘጋጀው ቦታ ላይ ማቆም የሚችሉት መንግሥት አካል ጉዳተኛ መሆናቸውን አምኖበት ታርጋ የሰጣቸው ሰዎች ብቻ ናቸው። አብዛኛውን ጊዜ የሚኖረው የመኪና ማቆሚያ ቦታ ውስን በመሆኑ መኪና ካለው ሰው ጋር በመሄድ የመኪናዎቹን ቁጥር መቀነስ እንችላለን።
◼ መቀመጫ መያዝ፦ መቀመጫ መያዝ የሚቻለው ከእናንተ ጋር በመኪና ለሚመጡ፣ በአንድ ቤት አብረዋችሁ ለሚኖሩ እንዲሁም ከእናንተ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ላይ ለሚገኙ ሰዎች ብቻ መሆኑን አስታውሱ።—1 ቆሮ. 13:5
◼ ምሳ፦ በእረፍት ሰዓት ምግብ ፍለጋ ከስብሰባው ቦታ ወጥታችሁ ከመሄድ ይልቅ እባካችሁ ምሳ ይዛችሁ ኑ። በመቀመጫችሁ ሥር ሊቀመጥ የሚችል አነስተኛ መጠን ያለው ዕቃ መጠቀም ይቻላል። ትላልቅ ዕቃዎችንና ጠርሙስ ነክ ዕቃዎችን ወደ ስብሰባው ቦታ ማምጣት አይፈቀድም።
◼ መዋጮ፦ በመንግሥት አዳራሽም ሆነ በአውራጃ ስብሰባ ላይ ለዓለም አቀፉ ሥራ በፈቃደኝነት መዋጮ በማድረግ ለስብሰባው የተሰማንን አድናቆት መግለጽ እንችላለን። በአውራጃ ስብሰባው ላይ መዋጮ የሚደረጉ ቼኮች ሁሉ ለ“ክርስቺያን ኮንግሪጌሽን ኦቭ ጀሆቫስ ዊትነስስ” የሚከፈሉ መሆናቸው መገለጽ አለበት።
◼ አደጋዎችና ድንገተኛ ሕመም፦ አንድ ሰው በስብሰባው ቦታ ላይ ድንገተኛ ሕመም ካጋጠመው በአቅራቢያችሁ የሚገኘውን አስተናጋጅ አነጋግሩ። አስተናጋጁ ስብሰባው በሚካሄድበት ቦታ የችግሩን ክብደት የሚገመግመውና እርዳታ የሚሰጠው የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና መስጫ ክፍል የት እንደሚገኝ ወዲያውኑ ይጠቁማችኋል። አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ይህ ክፍል ውጪ ከሚገኙት የሕክምና ተቋማት የባለሙያ ድጋፍ ሊጠይቅ ይችላል። ይህ ዝግጅት ተሰብሳቢዎች አነስተኛ ለሆኑ ጉዳዮችም ጭምር ለሆስፒታል ድንገተኛ ሕክምና ክፍል የሚያደርጉትን የሞባይል ስልክ ጥሪ ይቀንሳል።
◼ ጫማ፦ በየዓመቱ ከጫማ ጋር በተያያዘ ብዙ ጉዳት ይደርሳል። በመሆኑም በደረጃዎችና እነዚህ በመሳሰሉ ቦታዎች ያለ ችግር መራመድ እንድትችሉ ልከኛና ምቹ የሆነ ጫማ እንድታደርጉ እናበረታታችኋለን።
◼ የመስማት ችግር ያለባቸው፦ ስብሰባው በኤፍኤም የሬዲዮ ሞገድም ይተላለፋል። በዚህ ዝግጅት መጠቀም እንድትችሉ በባትሪ የሚሠራ የኤፍ ኤም መቀበያና የጆሮ ማዳመጫ ይዛችሁ መምጣት ያስፈልጋችኋል።
◼ የምስልና የድምፅ መቅረጫ መሣሪያዎች፦ የትኛውንም ዓይነት የመቅረጫ መሣሪያ በስብሰባው ቦታ ካለው የኤሌክትሪክ መስመር ወይም የድምፅ ማስተላለፊያ መሣሪያ ጋር ማገናኘት አይፈቀድም። እነዚህን የመሰሉ ነገሮች የምትጠቀሙ ከሆነ ሌሎች ስብሰባውን እንዳይከታተሉ በማያደናቅፍ መንገድ መጠቀም ይኖርባችኋል።
◼ የሕፃናት ጋሪዎችና የመናፈሻ ወንበሮች፦ የሕፃናት ጋሪዎችንና የመናፈሻ ወንበሮችን ወደ ስብሰባው ቦታ ይዞ መምጣት ተገቢ አይደለም። ይሁን እንጂ ከወላጆች አጠገብ ባለ ወንበር ላይ ሊታሰሩ የሚችሉ ለልጆች ደህንነት ተብለው የሚዘጋጁ ወንበሮችን (child-safety seats) ይዞ መምጣት ይቻላል።
◼ ሽቶዎች፦ አብዛኞቹ ስብሰባዎች የሚካሄዱት አየር እንደልብ በማይተላለፍባቸው ዝግ አዳራሾች ውስጥ ነው። በመሆኑም የመተንፈሻ አካል ችግር ወይም ከዚያ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የጤና ችግሮች ላለባቸው ሰዎች ጤንነት ስንል ኃይለኛ መዓዛ ያላቸውን ሽቶዎችና ኮሎኞች ባለመጠቀም ፍቅራዊ አሳቢነት ማሳየት እንችላለን።—1 ቆሮ. 10:24
◼ ቅጾች፦ እባካችሁ ተከታትላችሁ እርዱት (S-43) የሚለው ቅጽ በስብሰባው ላይ መደበኛ ባልሆነ መንገድ መሥክረንለት ፍላጎት ያሳየን ሰው በሚመለከት መረጃ ለመስጠት ያገለግላል። አስፋፊዎች አንድ ወይም ሁለት ቅጾችን ወደ ስብሰባው ይዘው መምጣት ይኖርባቸዋል። ቅጹን ከሞላችሁ በኋላ ለአውራጃ ስብሰባው የጽሑፍ ክፍል አሊያም ወደ ጉባኤያችሁ ስትመለሱ ለጉባኤው ጸሐፊ ልትሰጡት ትችላላችሁ።—የኅዳር 2009 የመንግሥት አገልግሎታችን ገጽ 4ን ተመልከቱ።
◼ ምግብ ቤቶች፦ ምግብ ቤት በምትመገቡበት ጊዜ መልካም ምግባር በማሳየት የይሖዋን ስም አስከብሩ። ለአስተናጋጆች ከ15 እስከ 20 በመቶ ጉርሻ ወይም ቲፕ መስጠት የተለመደ ነው።
◼ ሆቴሎች፦ (1) እባካችሁ ከምትጠቀሙበት ቁጥር በላይ ክፍል እንዲያዝላችሁ አትጠይቁ፤ እንዲሁም በክፍላችሁ ውስጥ ከሚፈቀደው ሰው በላይ አታሳድሩ። (2) እንዲያዝላችሁ የጠየቃችሁትን ክፍል የማትፈልጉት ከሆነ ወዲያውኑ ለሆቴሉ አሳውቁ። (3) የሻንጣ መጫኛ ጋሪዎችን በሚያስፈልጋችሁ ሰዓት ብቻ ውሰዱ። እንዲሁም ሌሎች ሰዎች መጠቀም እንዲችሉ ጋሪዎቹን ወዲያውኑ መልሱ። (4) መኝታ ክፍል ውስጥ ምግብ ማብሰል የማይፈቀድ ከሆነ አታብስሉ። (5) ክፍላችሁን ለሚያጸዱ ሠራተኞች በየቀኑ ጉርሻ ወይም ቲፕ ትታችሁ ሂዱ። (6) በሆቴሉ ውስጥ ያረፉ እንግዶችን ለማስተናገድ ሲባል ቁርስ፣ ቡና ወይም በረዶ በሚቀርብበት ጊዜ ከተፈቀደው በላይ አትውሰዱ። (7) ከሆቴሉ ሠራተኞች ጋር ባላችሁ ግንኙነት በማንኛውም ጊዜ የመንፈስ ፍሬን አሳዩ። እነዚህ ሠራተኞች በጣም ብዙ እንግዶችን የሚያስተናግዱ ሲሆን የምናሳየውን ደግነት፣ ትዕግሥትና ምክንያታዊነት ያደንቃሉ። (8) ሬከመንድድ ሎጂንግ ሊስት በተባለው ዝርዝር ላይ የተገለጸው ዋጋ የአንድን ቀን ሙሉ ዋጋ የሚያመለክት ነው፤ ታክስን ግን አይጨምርም። ከዋጋው በላይ ሒሳብ ከተጠየቃችሁ ወይም ላላዘዛችኋቸው ወይም ላልተጠቀማችሁባቸው ነገሮች እንድትከፍሉ ከተጠየቃችሁ ለመክፈል ፈቃደኞች አትሁኑ፤ ከዚህ ይልቅ በተቻለ ፍጥነት ጉዳዩን በስብሰባው ቦታ ለሚገኘው የማረፊያ ክፍል አሳውቁ። (9) ከክፍላችሁ ጋር በተያያዘ ችግር ካጋጠማችሁ ወደ ስብሰባው ስትመጡ እርዳታ ለማግኘት ጉዳዩን ለመስተንግዶ ክፍል አሳውቁ።
◼ የፈቃደኛ አገልግሎት፦ ፈቃደኛ ሠራተኞች ሆነን አስፈላጊ ሥራዎች የምናከናውን ከሆነ በአውራጃ ስብሰባው ላይ የምናገኘው ደስታ እጥፍ ድርብ ይሆናል። (ሥራ 20:35) ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆነው ማገልገል የሚፈልጉ ሁሉ በስብሰባው ቦታ ለሚገኘው የፈቃደኛ አገልግሎት ክፍል ማሳወቅ ይኖርባቸዋል። ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች በወላጅ ወይም ወላጅ በሚመድብላቸው ሞግዚት ወይም ሌላ ትልቅ ሰው ሥር በመሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ።