በመንፈሳዊ ድግስ ላይ ለመገኘት ተዘጋጅተሃል?
1. ድግስ መደገስ ምን ዓይነት ዝግጅት ማድረግ ይጠይቃል?
1 ድግስ መደገስ ብዙ ዝግጅት ይጠይቃል። ደጋሹ ምግብ ለመሥራት የሚያስፈልጉ ነገሮችን መግዛት ከዚያም ምግቡን አጣፍጦ መሥራትና ለእንግዶች ማቅረብ ይኖርበታል። ምግቡን ለማቅረብ የሚደረገው መስተንግዶ የተደራጀ ሊሆን ይገባል። በተጨማሪም ድግሱ የሚደረግበትን ቦታ ማሰናዳት ያስፈልጋል። እንግዶችም ቢሆኑ በተለይ ከሩቅ አካባቢ የሚመጡ ከሆነ በድግሱ ላይ ለመገኘት ዝግጅት ማድረግ አለባቸው። እንዲህ ያለውን ዝግጅት ማድረግ ብዙ ጥረት ቢጠይቅም ጣፋጭና ገንቢ ምግብ ከወዳጅ ዘመድ ጋር መመገብ ከሚያስገኘው ደስታ አንጻር ሲታይ የምንከፍለው መሥዋዕትነት ምንም አያስቆጭም። በቅርቡ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በጉጉት ከሚጠብቁት አንድ መንፈሳዊ ድግስ ማለትም “ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ!” ከተሰኘው የአውራጃ ስብሰባ ጥቅም ለማግኘት ቁጥራቸው ይነስም ይብዛ በቡድን በቡድን ሆነው ይሰበሰባሉ። ፕሮግራሙን የማዘጋጀቱና ስብሰባውን የማደራጀቱ ሥራ በአብዛኛው ተጠናቋል። በመሆኑም ሁላችንም በዚህ ድግስ ላይ እንድንገኝ ተጋብዘናል። በስብሰባው ላይ ለመገኘትና ከትምህርቱ የተሟላ ጥቅም ለማግኘት እኛም በግለሰብ ደረጃ ዝግጅት ማድረግ ይኖርብናል።—ምሳሌ 21:5
2. በድግሱ ላይ የሚቀርቡትን መንፈሳዊ ምግቦች በሙሉ ለመመገብ ምን ማድረግ ያስፈልገናል?
2 የተሟላ ጥቅም ለማግኘት ጣሩ፦ በድግሱ ላይ የሚቀርበውን እያንዳንዱን ምግብ አጣጥማችሁ ለመመገብ ከወዲሁ ዝግጅት አድርጋችኋል? ዓርብን ጨምሮ በሦስቱም ቀን ስብሰባ ላይ እንደምትገኙ ለአሠሪያችሁ ማሳወቅ ይኖርባችሁ ይሆናል። ትራንስፖርትንና ማረፊያ ቦታን በተመለከተ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጋችኋል? በዕድሜ የገፉ፣ የጤና እክል ያለባቸው እንዲሁም እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሌሎች የጉባኤው አባላት በስብሰባው ላይ እንዲገኙ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ሽማግሌዎች ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል።—ኤር. 23:4፤ ገላ. 6:10
3. ሳንጋበዝ በብሔራት አቀፍ የአውራጃ ስብሰባ ላይ መገኘት የሌለብን ለምንድን ነው?
3 በአንዳንድ አካባቢዎች ብሔራት አቀፍ የአውራጃ ስብሰባዎች ይደረጋሉ። እንዲህ ባሉ ስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ የሚጋበዙት የተወሰኑ ጉባኤዎችና ከውጭ አገር የሚመጡ ልዑካን መሆናቸውን ማስታወስ ይኖርባችኋል። ቅርንጫፍ ቢሮው እንዲህ ያሉትን ዝግጅቶች በሚያደርግበት ጊዜ በስብሰባው ቦታ የሚኖረውን ወንበርና በአካባቢው ያለውን አልቤርጎ ግምት ውስጥ በማስገባት የተጋባዦች ቁጥር ምን ያህል መሆን እንዳለበት በጥንቃቄ ይወስናል። በመሆኑም አስፋፊዎች ሳይጋበዙ በብሔራት አቀፍ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ቢገኙ መጨናነቅ እንዲፈጠር ሊያደርጉ ይችላሉ።
4. የእያንዳንዱ ቀን ስብሰባ ፕሮግራም ከመጀመሩ በፊት ዝግጁ እንድንሆን ምን ሊረዳን ይችላል?
4 ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት ወንበር ማግኘት እንድትችሉ በስብሰባው ላይ በጊዜ ለመገኘት ዝግጅት አድርጉ። ስብሰባው ከመጀመሩ በፊት ጥቂት ደቂቃ ወስዳችሁ በወረቀት ላይ የታተመውን ፕሮግራም ለመቃኘት ሞክሩ። እንዲህ ማድረጋችሁ ለሚቀርበው ትምህርት ልባችሁን እንድታዘጋጁ ይረዳችኋል። (ዕዝራ 7:10 የ1954 ትርጉም) የመድረኩ ሊቀ መንበር ስብሰባው መጀመሩን የሚያሳውቀው ሙዚቃ እንደሚሰማ በሚገልጽበት ጊዜ ሙዚቃውን ማዳመጥ እንድትችሉ ቦታ ቦታችሁን ያዙ፤ እንዲሁም በመክፈቻው መዝሙርና ጸሎት ላይ ለመካፈል ዝግጁ ሁኑ።
5. ቤተሰባችን ከፕሮግራሙ የተሟላ ጥቅም ማግኘት የሚችለው እንዴት ነው?
5 በአውራጃ ስብሰባው ወቅት በቤተሰብ ሆናችሁ መቀመጣችሁ ልጆቻችሁ ትምህርቱን በጥሞና እያዳመጡ እንደሆነ ለመቆጣጠር ያስችላችኋል። (ዘዳ. 31:12) ሁላችንም ጥቅሶች በሚነበቡበት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱሳችንን አውጥተን እንድንከታተል ተበረታተናል። አጠር ያለ ማስታወሻ መያዛችሁ ፕሮግራሙን በትኩረት እንድትከታተሉ ሊረዳችሁ ይችላል። የያዛችሁት ማስታወሻ የንግግሮቹን ዋና ዋና ነጥቦች በሌላ ጊዜ ለመከለስ ይረዳችኋል። ስብሰባው እየተካሄደ ሳያስፈልግ ከማውራት ወይም ከወንበራችሁ ተነስታችሁ ከመሄድ ተቆጠቡ። ሞባይል ስልክ ካለን እኛንም ሆነ በስብሰባው ላይ ያሉትን ሌሎች ሰዎች እንዳይረብሽ መጠንቀቅ አለብን። የጠዋቱም ሆነ የከሰዓት በኋላው ስብሰባ ካለቀ በኋላ ከፕሮግራሙ ያገኛችሁትን ጥቅም አንስታችሁ ለምን ከሌሎች ጋር አትወያዩም?
6. የአውራጃ ስብሰባ ካሉት ግሩም ገጽታዎች መካከል አንዱ ምንድን ነው? ሙሉ በሙሉ ልንጠቀምበት የምንችለውስ እንዴት ነው?
6 በአውራጃ ስብሰባው ላይ ስንገኝ በዓለም ላይ ፈጽሞ የማይታየውን ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ያለንን ወዳጅነት ለማጠናከር የሚያስችል አጋጣሚ እናገኛለን። (መዝ. 133:1-3፤ ማር. 10:29, 30) አጠገባችሁ ከተቀመጡት ጋር ለመተዋወቅና በምሳ እረፍት ወቅት አንዳንድ ጭውውቶችን ለማድረግ ግብ ብታወጡ ጥሩ ነው። ምግብ ቤት ሄደን ከመመገብ ይልቅ ቀለል ያለ ምግብ ይዘን በመምጣት የምሳ ሰዓታችንን በስብሰባው ቦታ ማሳለፋችን የሚያስገኘው አንዱ ጥቅም ይህ ነው። እርስ በርሳችን እንድንበረታታ የሚያስችሉን እንዲህ ያሉት አጋጣሚዎች እንዳያመልጡን ጥረት እናድርግ።—ሮም 1:11, 12
7. የምንለብሰውን ልብስ በተመለከተ ምን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይኖርብናል?
7 አለባበስ፦ ይሖዋ እስራኤላውያን በልብሳቸው ጫፍ ላይ ሰማያዊ ጥለት ያለው ዘርፍ እንዲያደርጉ አዟቸው የነበረ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። (ዘኍ. 15:37-41) የልብሳቸው ዘርፍ እስራኤላውያን የይሖዋ አምላኪዎች መሆናቸውን ለይቶ የሚያሳውቅ የሚታይ ምልክት ነበር። በዛሬው ጊዜም በአውራጃ ስብሰባ ላይ ስንገኝ አለባበሳችን ልከኛና ክብር ያለው መሆኑ ከዓለም የተለየን እንድንሆን ያደርገናል። እንዲህ ያለው አለባበስ ስብሰባው ካለቀ በኋላ ወደ ምግብ ቤቶች በምንሄድበት ወቅትም ሆነ በሌሎች አጋጣሚዎች ለሚመለከቱን ሰዎች ጥሩ ምሥክርነት ለመስጠት ያስችለናል። በመሆኑም ስለምትለብሱት ልብስ አስቀድማችሁ በጥንቃቄ አስቡ።
8. የአውራጃ ስብሰባው በሚካሄድበት አካባቢ ላሉ ሰዎች ምሥክርነት መስጠት የምንችለው እንዴት ነው?
8 ምሥክርነት ስጡ፦ መጠነኛ ዝግጅት በማድረግ የአውራጃ ስብሰባው በሚካሄድበት አካባቢ ላሉ ሰዎች ምሥክርነት መስጠት እንችል ይሆናል። አንድ ወንድም ስብሰባው እንዳለቀ ከባለቤቱ ጋር ወደ አንድ ምግብ ቤት ሄዶ ነበር፤ ከዚያም ያደረገውን ባጅ በማሳየት “ብዙ ሰዎች እንደዚህ ዓይነት ባጅ እንዳደረጉ አስተውለሃል?” በማለት የምግብ ቤቱን አስተናጋጅ ጠየቀው። አስተናጋጁም እንዲህ ያሉ ሰዎችን እንደተመለከተ ሆኖም ባጁን ያደረጉት ለምን እንደሆነ ግራ እንደገባው ተናገረ። ከዚህ ተነስተው ውይይት ያደረጉ ሲሆን ወንድምም አስተናጋጁን በአውራጃ ስብሰባው ላይ እንዲገኝ መጋበዝ ችሏል።
9. የድግሱ ባለቤት ለሆነው ለይሖዋ ያለንን አድናቆት መግለጽ የምንችለው እንዴት ነው?
9 በስብሰባው ላይ የሚቀርቡትን ንግግሮች፣ ቃለ ምልልሶችና ሠርቶ ማሳያዎች በሙሉ የሚያቀርቡት ወንድሞቻችን ቢሆኑም በየዓመቱ የሚዘጋጀው የዚህ መንፈሳዊ ድግስ ባለቤት አፍቃሪ የሆነው የሰማዩ አባታችን ይሖዋ ነው። (ኢሳ. 65:13, 14) በእያንዳንዱ የስብሰባ ቀን ላይ በመገኘትና የቀረበውን መንፈሳዊ ምግብ በማጣጣም ለድግሱ ባለቤት ያለንን አድናቆት ማሳየት እንችላለን። ታዲያ በዚህ መንገድ አድናቆታችሁን ለመግለጽ አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቃችኋል?
[በገጽ 2 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የስብሰባው ሰዓት
ፕሮግራሙ በሦስቱም ቀናት ከጠዋቱ 3:20 ላይ ይጀምራል። የመሰብሰቢያው ቦታ በር የሚከፈተው ከጠዋቱ 2 ሰዓት ላይ ነው። የመክፈቻው ሙዚቃ መሰማት ሲጀምር ሁላችንም ቦታ ቦታችንን መያዝ ይኖርብናል፤ ይህም ፕሮግራሙን ሥርዓት ባለው መንገድ ለማስጀመር ያስችላል። ፕሮግራሙ ዓርብና ቅዳሜ 10:55 እንዲሁም እሁድ 10 ሰዓት ላይ ይደመደማል። ብሔራት አቀፍ የአውራጃ ስብሰባ በሚካሄድባቸው ቦታዎች የሐሙሱ ዕለት ስብሰባ የሚጀምረው ከሰዓት በኋላ 7:20 ላይ ሲሆን የሚደመደመው ደግሞ 10:45 ላይ ይሆናል።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የአውራጃ ስብሰባ ማሳሰቢያዎች
◼ መቀመጫ መያዝ፦ መቀመጫ መያዝ የሚቻለው ከእናንተ ጋር በመኪና ለሚመጡና አብረዋችሁ ለሚኖሩ ሰዎች ብቻ መሆኑን አስታውሱ።
◼ ምሳ፦ በእረፍት ሰዓት ምግብ ፍለጋ ከስብሰባው ቦታ ወጥታችሁ ከመሄድ ይልቅ እባካችሁ ምሳ ይዛችሁ ለመምጣት ጥረት አድርጉ። በመቀመጫችሁ ሥር ሊቀመጥ የሚችል መጠነኛ ዕቃ መጠቀም ይቻላል። ትላልቅ ዕቃዎችን፣ ጠርሙስ ነክ ዕቃዎችንና የአልኮል መጠጦችን ወደ ስብሰባው ቦታ ማምጣት አይፈቀድም።
◼ መዋጮ፦ በመንግሥት አዳራሽም ሆነ በአውራጃ ስብሰባ ላይ ለዓለም አቀፉ ሥራ በፈቃደኝነት መዋጮ በማድረግ ለስብሰባው የተሰማንን አድናቆት መግለጽ እንችላለን። በአውራጃ ስብሰባው ላይ መዋጮ የሚደረጉ ቼኮች ሁሉ ለ“የይሖዋ ምሥክሮች” የሚከፈሉ መሆናቸው መገለጽ አለበት።
◼ አደጋዎችና ድንገተኛ ሕመም፦ አንድ ሰው በስብሰባው ቦታ ላይ ድንገተኛ ሕመም ካጋጠመው የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ መስጫ ክፍል የሚገኝበትን ቦታ እንዲጠቁማችሁ በቅርብ ያለውን አስተናጋጅ አነጋግሩ።
◼ የምስልና የድምፅ መቅረጫ መሣሪያዎች፦ የትኛውንም ዓይነት የመቅረጫ መሣሪያ በስብሰባው ቦታ ካለው የኤሌክትሪክ መስመር ወይም የድምፅ ማስተላለፊያ መሣሪያ ጋር ማገናኘት አይፈቀድም። እነዚህን የመሰሉ ነገሮች የምትጠቀሙ ከሆነ ሌሎች ስብሰባውን እንዳይከታተሉ የማያደናቅፉ መሆን ይገባቸዋል።
◼ የሕፃናት ጋሪዎችና የመናፈሻ ወንበሮች፦ የሕፃናት ጋሪዎችንና የመናፈሻ ወንበሮችን ወደ ስብሰባው ቦታ ይዞ መምጣት ተገቢ አይደለም። ይሁን እንጂ ከወላጆች አጠገብ ባለ ወንበር ላይ ሊታሰሩ የሚችሉ ለልጆች ደህንነት ተብለው የሚዘጋጁ ወንበሮችን (child-safety seats) ይዞ መምጣት ይቻላል።