ክርስቲያናዊ ክብርን በማንጸባረቅ ክርስቶስን ተከተሉ
1. በዚህ ዓመት የሚደረገው የአውራጃ ስብሰባ ጭብጥ ክርስቲያናዊ ክብርን ከማንጸባረቅ ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው?
1 መጽሐፍ ቅዱስ፣ የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥ የሆነው ይሖዋ ክብር እንደተላበሰ ይገልጻል። (መዝ. 104:1) ኢየሱስ የተናገራቸውም ሆኑ ያደረጋቸው ነገሮች አባቱንና የአባቱን ዝግጅቶች የሚያስከብሩ ነበሩ። (ዮሐ. 17:4) በቅርቡ በምናደርገው “ክርስቶስን ተከተሉ!” በተሰኘው የአውራጃ ስብሰባ ላይ እያንዳንዳችን የኢየሱስን ምሳሌ በመኮረጅ ይሖዋን ለማስከበር የሚያስችሉንን አጋጣሚዎች እናገኛለን።
2. በእያንዳንዱ የስብሰባው ክፍለ ጊዜ መገኘታችን ይሖዋን የሚያስከብረው እንዴት ነው?
2 ክብር የተላበሰ አምልኮ:- ይሖዋ ባዘጋጀልን መንፈሳዊ ድግስ ላይ ለመገኘት የሚያስችለንን ዝግጅት በማድረግ እሱን ማክበር እንችላለን። ከአሠሪያችሁ ጋር በመነጋገር አርብን ጨምሮ በሁሉም ቀናት በስብሰባው ላይ ለመገኘት እንድትችሉ ሁኔታችሁን አመቻችታችኋል? መቀመጫ ለማግኘትም ሆነ በመክፈቻው መዝሙርና ጸሎት ላይ ለመገኘት እንድትችሉ ቀደም ብላችሁ ለመምጣት እቅድ አውጥታችኋል? ስብሰባው ከሚካሄድበት ቦታ ሳትወጡ ከወንድሞቻችሁ ጋር ምሳችሁን ለመመገብ የሚያስችላችሁን ዝግጅት አድርጋችኋል? እያንዳንዱ ክፍለ ጊዜ ሲጀምር ሊቀ መንበሩ ሙዚቃው ከመጀመሩ በፊት ቦታ ቦታችንን እንድንይዝ በአክብሮት ይጠይቀናል፤ በዚህ ወቅት ሁላችንም ጭውውታችንን ወዲያውኑ አቋርጠን በመቀመጥ ፕሮግራሙ የሚጀምርበትን ሰዓት መጠባበቅ ይኖርብናል።
3. ፕሮግራሙን በትኩረት መከታተላችን አምልኳችንን ክብር የተላበሰ እንዲሆን የሚያደርገው እንዴት ነው?
3 በተጨማሪም ዝግጅቱን በትኩረት መከታተላችን በሰማይ የሚኖረውን አባታችንን ያስከብረዋል። አንድ ጋዜጠኛ በአካባቢው የተደረገውን የአውራጃ ስብሰባ ከተመለከተ በኋላ “በስብሰባው ላይ የተገኙት ሁሉ የሚቀርበውን ንግግር በጥሞና ማዳመጣቸው እንዲሁም ለመንፈሳዊ ነገር አድናቆት እንዳላቸው በሚያሳይ መንገድ መከታተላቸው” ብዙዎችን እንዳስደነቀና “ይህ ባሕርይም በምሳሌነት የሚታይ” እንደሆነ ዘግቧል። አክሎም በስብሰባው ላይ ስላያቸው ልጆች ሲናገር “በጣም የሚገርመው አብዛኞቹ ልጆች . . . ሥርዓታማ ናቸው፤ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ሲነበቡ አውጥተው ይከታተላሉ” በማለት ዘግቧል። ስብሰባው በመካሄድ ላይ እያለ ወሬ ማውራት፣ በሞባይል ስልኮች በጽሑፍ አማካኝነት መልእክት መለዋወጥ፣ ምግብ መብላት አሊያም በመተላለፊያዎች ወዲያ ወዲህ ማለት ተገቢ አይደለም። ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር መቀመጥ ይኖርባቸዋል። ወላጆች እንዲህ ካደረጉ፣ ልጆቻቸው ከስብሰባው የተሟላ ጥቅም እንዲያገኙ መርዳት ይችላሉ። (ዘዳ. 31:12፤ ምሳሌ 29:15) እንዲህ ያሉ ጥረቶች ለሌሎች ያለንን አክብሮትና እየቀረበ ላለው በጣም አስፈላጊ መንፈሳዊ ምግብ ያለንን አመስጋኝነት የሚያሳዩ ናቸው።
4. በስብሰባው ወቅት አለባበሳችን የሚያስከብር መሆኑ አስፈላጊ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
4 ክብር የሚንጸባረቅበት አለባበስ:- ብዙዎች ባለፈው ዓመት በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ “በማንኛውም ጊዜ ክርስቲያናዊ ክብር አንጸባርቁ” በሚል ጭብጥ በቀረበው ንግግር ላይ ለተሰጡት ማሳሰቢያዎች ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል። ንግግሩ የአምላክ አገልጋዮች በአለባበሳቸውም ሆነ በአበጣጠራቸው ክርስቲያናዊ ክብር ለማንጸባረቅ ጥረት ማድረግ እንደሚኖርባቸው ጎላ አድርጎ የሚጠቅስ ነበር። በዚህ ዓመትም ይህ ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። አለባበሳችን ለይሖዋ እንዲሁም የእሱ ምሥክሮች ሆነን እንድናገለግል ላገኘነው መብታችን ያለንን አመለካከት የሚያንጸባርቅ ነው። ምንጊዜም አለባበሳችን “እግዚአብሔርን እናመልካለን” ለሚሉ ሰዎች የሚገባ መሆን ይኖርበታል።—1 ጢሞ. 2:9, 10
5. ስብሰባውን በምናደርግበት አካባቢ ዘና ለማለት ስንወጣ አለባበሳችን ክብር የሚንጸባረቅበት እንዲሆን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
5 አለባበሳችን ክብር የሚንጸባረቅበት መሆን ያለበት በስብሰባው ላይ በምንሆንበት ጊዜ ብቻ ነው? ስብሰባው በሚደረግበት አካባቢ የሚገኙ በርካታ ሰዎች ያደረግነውን ባጅ እንደሚመለከቱ አስታውሱ። አለባበሳችን ከሌሎች ሰዎች የተለየን መሆናችንን በግልጽ ማሳየት ይኖርበታል። በመሆኑም ከስብሰባው በኋላም እንኳ ለምሳሌ ያህል ምግብ ለመመገብ በምንወጣበት ጊዜ አለባበሳችን የአውራጃ ስብሰባውን ለመካፈል ከመጣ አንድ አገልጋይ የሚጠበቅ መሆን ይገባዋል፤ ይህ ደግሞ እንደ ጂንስ፣ ቁምጣ ወይም ቲሸርት ያሉ ልብሶችን ከመልበስ መቆጠብን ይጨምራል። እንዲህ ማድረጋችን ለአካባቢው ነዋሪዎች ግሩም ምሥክርነት ይሰጣል! ይሖዋ አለባበሳችን አገልጋዮቹ መሆናችንን የሚያሳይ ከሆነ ይደሰታል።
6. ክርስቲያናዊ ክብርን ማንጸባረቅ ምን ጥሩ ውጤቶች ያስገኛል?
6 አስደሳች ውጤቶች:- በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ክርስቲያናዊ ክብር ማንጸባረቃችን መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመመሥከር የሚያስችለንን አጋጣሚ የሚፈጥርልን ከመሆኑም ባሻገር የሚመለከቱን ሰዎችም ለእኛ ጥሩ አመለካከት እንዲኖራቸው ያደርጋል። አንድ የአውራጃ ስብሰባ ከተጠናቀቀ በኋላ አንድ ባለ ሥልጣን “እንዲህ ዓይነት የታረመ ጠባይ ያላቸው ሰዎች አይተን አናውቅም፤ አምላክ እንደ እናንተ እንድንሆን ይጠብቅብናል” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ክርስቲያናዊ ክብር ማንጸባረቃችን አንዳችን ለሌላው አክብሮትና ፍቅር እንዳለን የሚያሳይ ሲሆን ይሖዋንም ያስከብራል። (1 ጴጥ. 2:12) በተጨማሪም አምላክን እንደምንፈራ እንዲሁም ከአባታችን ላገኘነው የመማር መብት አመስጋኝ እንደሆንን ያሳያል። (ዕብ. 12:28) በጉጉት በምንጠብቀው “ክርስቶስን ተከተሉ!” በተባለው የዚህ ዓመት የአውራጃ ስብሰባ ላይ ክርስቲያናዊ ክብርን ለማንጸባረቅ ጥረት እናድርግ።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
District Convention Reminders
ውራጃ ስብሰባ ማሳሰቢያዎች
◼ ሰዓት:- ፕሮግራሙ በሦስቱም ቀናት ከጠዋቱ 3:20 ላይ ይጀምራል። የመሰብሰቢያ ቦታው በር የሚከፈተው ከጠዋቱ 2:00 ላይ ነው። የመክፈቻ ሙዚቃው መሰማት ሲጀምር ሁላችንም ቦታ ቦታችንን መያዝ ይኖርብናል። ይህም ስብሰባውን ሥርዓት ባለው መንገድ ለመጀመር ያስችላል። ፕሮግራሙ ዓርብ እና ቅዳሜ 11:05 እንዲሁም እሁድ 10:10 ላይ ይደመደማል።
◼ መቀመጫ መያዝ:- መቀመጫ መያዝ የሚቻለው አብረዋችሁ ለሚኖሩና ከእናንተ ጋር በመኪና ለሚመጡ ሰዎች ብቻ መሆኑን አስታውሱ።
◼ ምሳ:- በእረፍት ሰዓት ምግብ ፍለጋ የስብሰባውን ቦታ ትታችሁ ከመሄድ ይልቅ እባካችሁ ምሳ ይዛችሁ ኑ። አስፈላጊ ከሆነ በመቀመጫችሁ ሥር ሊቀመጥ የሚችል መጠነኛ የምግብ መያዣ ዕቃ መጠቀም ይቻላል። ጠርሙስ ነክ ዕቃዎችንና የአልኮል መጠጦችን ወደ ስብሰባው ቦታ ማምጣት አይፈቀድም።
◼ መዋጮ:- የአውራጃ ስብሰባዎችን ማደራጀት ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል። በመንግሥት አዳራሽም ሆነ በአውራጃ ስብሰባ ላይ ለዓለም አቀፉ ሥራ በፈቃደኝነት መዋጮ በማድረግ አድናቆታችንን ማሳየት እንችላለን። በስብሰባው ላይ መዋጮ የሚደረጉ ቼኮች ለ“የይሖዋ ምሥክሮች” [“Yeyihowa Misikiroch”] የሚከፈሉ መሆናቸው መገለጽ አለበት።
◼ የምስልና የድምፅ መቅረጫ መሣሪያዎች:- የትኛውንም ዓይነት የመቅረጫ መሣሪያ በስብሰባው ቦታ ካለው የኤሌክትሪክ መስመር ወይም የድምፅ ማስተላለፊያ መሣሪያ ጋር ማገናኘት አይፈቀድም። እነዚህን የመሰሉ ነገሮች የምትጠቀሙ ከሆነ ሌሎች ስብሰባውን እንዳይከታተሉ የማያደናቅፉ መሆን ይገባቸዋል።
◼ ቅጾች:- እባካችሁ ተከታትላችሁ እርዱት (S-43) የሚለው ቅጽ በስብሰባው ላይ መደበኛ ባልሆነ መንገድ መሥክረንለት ፍላጎት ስላሳየ ሰው መረጃ ለመስጠት ያገለግላል። አስፋፊዎች ወደ አውራጃ ስብሰባው ሲመጡ አንድ ወይም ሁለት S-43 ቅጾችን ይዘው መምጣት ይኖርባቸዋል። ይህ ቅጽ በአውራጃ ስብሰባው የጽሑፍ ክፍል ውስጥም ይገኛል። ቅጹን ከሞላችሁ በኋላ ለአውራጃ ስብሰባው የጽሑፍ ክፍል አሊያም ወደ ጉባኤያችሁ ስትመለሱ ለጉባኤው ጸሐፊ ልትሰጡት ትችላላችሁ።—የየካቲት 2005 የመንግሥት አገልግሎታችን ገጽ 6ን ተመልከቱ።