የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • km 8/05 ገጽ 3-5
  • በታላቅ ጉባኤ መካከል ይሖዋን አመስግኑ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በታላቅ ጉባኤ መካከል ይሖዋን አመስግኑ
  • የመንግሥት አገልግሎታችን—2005
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ይሖዋን በከፍተኛ ጉጉት ተጠባበቁ
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2006
  • ክርስቲያናዊ ክብርን በማንጸባረቅ ክርስቶስን ተከተሉ
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2007
  • በመንፈሳዊ የምንመገብበትና የምንደሰትበት ዝግጅት
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2008
  • የአውራጃ ስብሰባ—አስደሳች የአምልኮ ወቅት
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2010
ለተጨማሪ መረጃ
የመንግሥት አገልግሎታችን—2005
km 8/05 ገጽ 3-5

በታላቅ ጉባኤ መካከል ይሖዋን አመስግኑ

1, 2. የአውራጃ ስብሰባው ምን የማድረግ አጋጣሚ ይሰጠናል? ይህንንስ በየትኞቹ መንገዶች ማድረግ እንችላለን?

1 በየዓመቱ የምናደርጋቸው የአውራጃ ስብሰባዎች ይሖዋን ለማወደስ ግሩም አጋጣሚ ይሰጡናል። እኛም “በታላቅ ጉባኤ መካከል አመሰግንሃለሁ፤ ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበትም አወድስሃለሁ” በማለት የዘመረው የዳዊት ዓይነት ስሜት አለን። (መዝ. 35:18) ከፊታችን በሚደረገው “አምላካዊ ታዛዥነት” በተሰኘው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ሁላችንም ለይሖዋ ውዳሴ ማምጣት የምንችለው እንዴት ነው?

2 ይህን ማድረግ የምንችልበት አንደኛው መንገድ በጸባያችን ነው። የአንድ የስብሰባ ቦታ የአስተዳደር ቢሮ “የእናንተን ስብሰባ ካየን በኋላ ቦታውን ሌሎች የሃይማኖት ድርጅቶች ሊከራዩ ሲመጡ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባውን ግሩም በሆነ ሁኔታ እንዴት እንደሚያደራጁ መጥተው እንዲያዩ ነግረናቸዋል” የሚል አስተያየት ሰጥቷል። በአለባበሳችን፣ በምናሳየው የትብብር መንፈስና በጸባያችን ለአምላካችን እንዲህ የመሰለ ታላቅ የምስጋና ቃል እንዲቀርብ እያንዳንዳችን የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናበረክታለን።—1 ጴጥ. 2:12

3, 4. በስብሰባው ላይም ሆነ ከስብሰባው በኋላ ባለው ጊዜ አለባበሳችን ለክርስቲያኖች የሚገባ እንዲሆን ልከኝነት እንዴት ሊረዳን ይችላል?

3 አለባበስና አበጣጠር:- አለባበሳችንና አበጣጠራችን ይሖዋን የሚያስከብር እንዲሆን የልከኝነት ባሕርይ ሊኖረን ይገባል። (1 ጢሞ. 2:9) የአገልግሎት ትምህርት ቤት መጽሐፍ በገጽ 132 ላይ “ጨዋ የሆነ ሰው ሌሎችን የሚያስከፋ ወይም ወደ ራሱ ትኩረት የሚስብ ነገር ላለማድረግ ይጠነቀቃል” ይላል። በብዙ አገሮች ውስጥ ቅጥ ያጣ አለባበስ የተለመደ እየሆነ መጥቷል። ነገር ግን ይሖዋ፣ እሱን በሚገባ ለመወከል የምናደርገውን ጥረት ያደንቃል። (ሥራ 15:14) ምንም እንኳ የአውራጃ ስብሰባው የተደረገው በስፖርት ማዘውተሪያ ቦታ ወይም በመዝናኛ ሥፍራ ሊሆን ቢችልም ይህ የሦስት ቀን ስብሰባ ለእኛ “ታላቅ ጉባኤ” ነው። ከዚህም የተነሳ በይሖዋ ፊት ስንሰበሰብ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ላለው ለመጨረሻው ከፍተኛ አካል ክብር በሚያመጣ መንገድ መልበስ ይኖርብናል።—1 ዜና 29:11

4 የእያንዳንዱ ቀን የስብሰባ ፕሮግራም ካበቃ በኋላም ቢሆን ለአለባበሳችን ትኩረት ልንሰጥ ይገባናል። በእረፍት ጊዜያችን ወይም ወደ ምግብ ቤት ስንሄድ ይበልጥ ዘና የሚያደርገንን ልብስ መልበስ እንመርጥ ይሆናል። በእነዚህ ጊዜያትም ቢሆን አለባበሳችንና አበጣጠራችን “እግዚአብሔርን እናመልካለን” ለሚሉ ሰዎች የሚገባ ዓይነት መሆን አለበት። (1 ጢሞ. 2:10) ተገቢ የሆነ ልብስ የሚለካው በዓለም ዘንድ ባለው ተቀባይነት አይደለም። (1 ዮሐ. 2:16, 17) በክርስቲያናዊ ጽሑፎቻችን ላይ በተለያዩ አጋጣሚዎች ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ሊለብሷቸው የሚችሉ ልከኛና ተገቢ የሆኑ አለባበሶች ወጥተዋል። ስብሰባው በሚደረግበት ከተማ ሳለን ባጅ ካርድ ማድረጋችን በማንኛውም ጊዜ ክርስቲያን አገልጋዮች መሆናችንን ያስታውሰናል።—2 ቆሮ. 6:3, 4

5, 6. ይሖዋ ላቀረበልን መንፈሳዊ ገበታ አድናቆት እንዳለን እንዴት ማሳየት እንችላለን?

5 ለይሖዋ ማዕድ አክብሮት አሳዩ:- የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ ከፊታችን ግብዣ አዘጋጅቶልናል። (ኢሳ. 25:6፤ 1 ቆሮ. 10:21) የይሖዋን መንፈሳዊ ገበታ ከፍ አድርገን የምንመለከት ከሆነ ግባችን በሦስቱም የአውራጃ ስብሰባ ቀናት ላይ መገኘት ይሆናል። የማረፊያ ቦታን፣ መጓጓዣንና ከሥራ ፈቃድ መጠየቅን ለመሳሰሉት ነገሮች ዝግጅት አድርገሃል? ስብሰባው ቦታ በጊዜ መድረስና መቀመጫ መያዝ፣ ከወንድሞችህ ጋር ጊዜ ማሳለፍ እንዲሁም በመክፈቻው መዝሙርና ጸሎት አብረሃቸው ይሖዋን ማወደስ እንድትችል የምትዘገጃጅበትና ወደዚያ የምትጓዝበት በቂ ጊዜ መድበሃል?—መዝ. 147:1

6 ለይሖዋ ማዕድ ያለን አክብሮት ፕሮግራሙን በትኩረት እንድንከታተል እንዲሁም ከሌሎች ጋር ከማውራት፣ ምግብ ከመብላት ወይም ወዲያ ወዲህ ከመዘዋወር እንድንቆጠብ ያደርገናል። ይሖዋ በወቅቱ የሚያስፈልገንን መንፈሳዊ ምግብ በታማኝና ልባም ባሪያ ክፍል በኩል አቅርቦልናል። (ማቴ. 24:45 የ1954 ትርጉም) ማናችንም ብንሆን የትኛውም የፕሮግራሙ ክፍል እንዲያመልጠን አንፈልግም። ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር በመቀመጥ ሙሉ በሙሉ ከስብሰባው ተጠቃሚ እንዲሆኑ መርዳት ይኖርባቸዋል።—ዘዳ. 31:12

7. በምሳ እረፍት ወቅት ምን እንድናደርግ ተጠይቀናል? ለምንስ?

7 በእረፍት ሰዓት ምግብ ፍለጋ ከስብሰባው ቦታ ከመውጣት ይልቅ ምሳ ይዛችሁ እንድትመጡ ትጠየቃላችሁ። ባለፈው ዓመት በተደረገው ስብሰባ ላይ ብዙ ወንድሞችና እህቶች ይህንን መመሪያ በጥብቅ መከተላቸው የሚያስመሰግን ነው። በዚህ ዓመት ደግሞ ሁላችንም እንዲህ ብናደርግ ምንኛ መልካም ነው! (ዕብ. 13:17) ይህ ዝግጅት ከወንድሞቻችን ጋር የሚያንጽ ጊዜ ለማሳለፍ ጥሩ አጋጣሚ ከመስጠቱም በላይ ለይሖዋ ክብር የሚያመጣ አንድነትና ሰላም የሰፈነበት ሁኔታ እንዲኖር አስተዋጽኦ ያበረክታል።—መዝ. 133:1

8, 9. የአውራጃ ስብሰባው ይሖዋን ለማመስገን የሚያስችል ምን ተጨማሪ አጋጣሚ ይሰጠናል?

8 መደበኛ ባልሆነ መንገድ መመስከር:- ወደ ስብሰባው ቦታ ስንሄድም ሆነ ከዚያ ስንመለስ ይሖዋን በከንፈራችን የምናመሰግንበት ብዙ አጋጣሚ አለን። (ዕብ. 13:15) በምግብ ቤት እየተመገብን ወይም ከሆቴል ሠራተኞች ጋር እየተነጋገርን ካለን ምሥክርነት ለመስጠት ቀዳዳ መፈለግ ይኖርብናል። ስብሰባው አእምሯችንና ልባችን መንፈሳዊ በሆኑ ነገሮች እንዲሞሉ ያደርጋል። እነዚህን መልካም ነገሮች ለምናገኛቸው ሰዎች እናካፍላቸው።—1 ጴጥ. 3:15

9 ይሖዋን “በታላቅ ጉባኤ መካከል” ለማወደስ ይህን አጋጣሚ በከፍተኛ ጉጉት እንጠብቃለን። (መዝ. 26:12) እንግዲያው ሁላችንም በአንድነት “አምላካዊ ታዛዥነት” በተሰኘው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ይሖዋን እናመስግን።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የአውራጃ ስብሰባ ማሳሰቢያዎች

◼ ሰዓት:- ፕሮግራሙ በሦስቱም ቀናት ከጠዋቱ 3:30 ላይ ይጀምራል። ከጠዋቱ 2:00 በሮች ይከፈታሉ። የዕለቱ ፕሮግራም ለመጀመር ጥቂት ደቂቃ ሲቀረው የዕለቱ ሊቀ መንበር የመክፈቻ ሙዚቃው እየተሰማ እያለ መድረክ ላይ በተዘጋጀለት ወንበር ላይ ይቀመጣል። በዚህ ወቅት ሁላችንም ቦታ ቦታችንን መያዝ ይኖርብናል። ይህም ስብሰባውን ሥርዓት ባለው መንገድ ለመጀመር ያስችላል። ፕሮግራሙ አርብና ቅዳሜ 11:05 ላይ ሲደመደም እሁድ ደግሞ 10:10 ላይ ያበቃል።

◼ መኪና ማቆሚያ:- የመኪና ማቆሚያ ባላቸው በሁሉም የስብሰባ ቦታዎች ላይ ክፍያ የማይጠየቅ ሲሆን መኪናዎች እንደ አመጣጣቸው ቦታ ያገኛሉ። ደረት ላይ የሚለጠፈው ባጅ ካርድ መኪና ለማቆም እንደ መታወቂያ ሆኖ ያገለግላል። አብዛኛውን ጊዜ መኪና ማቆሚያ ቦታ ውስን ስለሚሆን በአንድ መኪና ውስጥ አንድ ወይም ሁለት ሆኖ ከመምጣት ይልቅ በተቻለ መጠን በዛ ብሎ መምጣቱ ይመረጣል።

◼ መቀመጫ መያዝ:- መቀመጫ መያዝ የሚቻለው አብረዋችሁ ለሚኖሩና ከእናንተ ጋር በመኪና ለሚመጡ ሰዎች ብቻ መሆኑን አስታውሱ።

◼ መዋጮዎች:- አውራጃ ስብሰባ ማደራጀት ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል። በመንግሥት አዳራሽም ሆነ በአውራጃ ስብሰባ ላይ ለዓለም አቀፉ ሥራ በፈቃደኝነት አስተዋጽኦ በማድረግ አድናቆታችንን ማሳየት እንችላለን። በስብሰባው ላይ መዋጮ የሚደረጉ ቼኮች ለ “የይሖዋ ምሥክሮች” [“Yeyihowa Misikiroch”] የሚከፈሉ መሆናቸው መገለጽ አለበት።

◼ ምሳ:- በእረፍት ጊዜ ምግብ ፍለጋ የስብሰባውን ቦታ ትታችሁ ከመሄድ ይልቅ እባካችሁ ምሳ ይዛችሁ ኑ። አስፈላጊ ከሆነ በመቀመጫችሁ ሥር ሊቀመጥ የሚችል መጠነኛ የምግብ መያዣ ዕቃ መጠቀም ይቻላል። ጠርሙሶችንና የአልኮል መጠጦችን ወደ ስብሰባው ቦታ ማምጣት አይፈቀድም።

◼ የምስልና የድምፅ መቅረጫ መሣሪያዎች:- የትኛውንም ዓይነት የመቅረጫ መሣሪያ በስብሰባው ቦታ ካለው የኤሌክትሪክ መስመር ወይም የድምፅ ማስተላለፊያ መሣሪያ ጋር ማያያዝ አይፈቀድም። እነዚህን የመሰሉ ነገሮች የምትጠቀሙ ከሆነ ሌሎች ስብሰባውን እንዳይከታተሉ የማያደናቅፍ መሆን ይገባዋል።

◼ ፎቶግራፍ ማንሳት:- ፎቶግራፍ ማንሳት ከፈለጋችሁ ስብሰባው እየተካሄደ ፍላሽ መጠቀም አይኖርባችሁም።

◼ ሞባይል ስልኮች:- በሞባይል ስልኮች ምክንያት የሌሎች ትኩረት እንዳይከፋፈል ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ