በመንፈሳዊ የምንታደስበት የሦስት ቀን ስብሰባ
1. ከዚህ ዓመት የአውራጃ ስብሰባ ምን እናገኛለን?
1 በዚህ በመንፈሳዊ ድርቅ በተጠቃ የሰይጣን ዓለም ውስጥ ይሖዋ የአገልጋዮቹን ነፍስ ማርካቱን ቀጥሏል። (ኢሳ. 58:11) ይሖዋ እኛን ለማበርታት ከሚጠቀምባቸው ዝግጅቶች አንዱ ዓመታዊው የአውራጃ ስብሰባ ነው። የዚህ ዓመት የአውራጃ ስብሰባ እየተቃረበ ሲመጣ መንፈሳዊ በረከቶችን ለመቀበልና ለሌሎች ለማካፈል መዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው?—ምሳሌ 21:5
2. የትኞቹን ዝግጅቶች ማጠናቀቅ ያስፈልገናል?
2 በሦስቱም የስብሰባ ቀናት ለመገኘት እስካሁን ዝግጅት ካላደረግህ ከግልህም ሆነ ከሰብዓዊ ሥራህ ጋር በተያያዘ ፕሮግራምህን አሁኑኑ ማስተካከል ይኖርብሃል። ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት ለመድረስና ቦታ ለማግኘት እንድትችል ስብሰባው ወደሚደረግበት ቦታ ለመድረስ ምን ያህል ጊዜ እንደሚፈጅብህ አስልተኸዋል? ይሖዋ ካዘጋጀልን ኃይላችንን የሚያድስ መንፈሳዊ ምግብ ውስጥ ምንም እንዲያመልጠን እንደማንፈልግ ጥርጥር የለውም! (ኢሳ. 65:13, 14) ታዲያ የማረፊያና የመጓጓዣ ዝግጅትህን አጠናቀሃል?
3. እኛም ሆንን ቤተሰባችን ከፕሮግራሙ የተሟላ ጥቅም እንድናገኝ ምን ሊረዳን ይችላል?
3 በስብሰባው ላይ አእምሮህ እንዳይባዝን ምን ሊረዳህ ይችላል? የሚቻል ከሆነ በስብሰባው ዕለት ማታ ማታ በቂ እረፍት አድርግ። ዓይንህ በተናጋሪው ላይ እንዲያተኩር አድርግ። እያንዳንዱ ጥቅስ ሲነበብ መጽሐፍ ቅዱስህን ገልጠህ ተከታተል። አጭር ማስታወሻ ያዝ። ወላጆች ልጆቻቸው ትምህርቱን በትኩረት እንዲከታተሉ ለመርዳት እንዲያስችላቸው ቤተሰቦች አንድ ላይ ቢቀመጡ የተሻለ ነው። (ምሳሌ 29:15) ምናልባትም የፕሮግራሙን ጎላ ያሉ ነጥቦች በእያንዳንዱ ምሽት በቤተሰብ ደረጃ ልትከልሱ ትችላላችሁ። ስብሰባው ካለቀ በኋላም ቤተሰባችሁ ጥቅም ማግኘት እንዲችል ልትሠሩባቸው የሚገቡ አንዳንድ ነጥቦችን ለመከለስ በቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችሁ ላይ ጊዜ መመደብ ትችላላችሁ።
4. በጉባኤያችን ውስጥ ያሉ ሌሎች ሰዎች መንፈሳዊ በረከት እንዲያገኙ ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው?
4 ሌሎች በመንፈሳዊ እንዲታደሱ መርዳት፦ እንደ እኛ ሁሉ ሌሎችም መንፈሳዊ በረከት እንዲያገኙ እንፈልጋለን። በስብሰባው ላይ ለመገኘት እርዳታ የሚያስፈልጋቸው በዕድሜ የገፉ ወይም ሌላ ችግር ያለባቸው አስፋፊዎች አሉ? አንተስ እነሱን ለመርዳት ትችል ይሆን? (1 ዮሐ. 3:17, 18) ሽማግሌዎች በተለይ ደግሞ የቡድን የበላይ ተመልካቾች እንዲህ ያሉ አስፋፊዎች አስፈላጊውን እርዳታ እንዲያገኙ ዝግጅት ማድረግ አለባቸው።
5. የስብሰባውን መጋበዣ ማሰራጨት የምንችለው እንዴት ነው? (በተጨማሪም ከላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።)
5 ከዚህ ቀደም እናደርግ እንደነበረው የአውራጃ ስብሰባችን ከመጀመሩ ሦስት ሳምንት ቀደም ብለን ሌሎች በስብሰባው ላይ እንዲገኙ ለመጋበዝ በሚደረገው ዘመቻ ላይ እንካፈላለን። ጉባኤዎች የደረሳቸውን የመጋበዣ ወረቀት የማሰራጨት እንዲሁም በተቻለ መጠን ክልላቸውን የመሸፈን ግብ ሊኖራቸው ይገባል። ዘመቻው ከተጠናቀቀ በኋላ ቤተሰባችሁ የመጋበዣ ወረቀቱ ከተረፈው መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት በምትሰጡበት ጊዜ እንድትጠቀሙበት ስብሰባው ወደሚካሄድበት ቦታ ይዛችሁት ልትመጡ ይገባል። በዓርብ ዕለቱ ስብሰባ ላይ ይህን በሚመለከት ተጨማሪ መመሪያ ይሰጣል። ቤተሰባችሁ እንደማይጠቀምበት የሚሰማችሁ ትርፍ የመጋበዣ ወረቀት ካለ ስብሰባው ወደሚካሄድበት ቦታ ስትገቡ ለምታገኙት አስተናጋጅ መስጠት ይኖርባችኋል። የእሁድ ዕለቱ የመጨረሻ ንግግር ሲቀርብ የመጋበዣ ወረቀቱ ስለሚያስፈልጋችሁ እባካችሁ ለራሳችሁ አንድ ቅጂ አስቀሩ።
6. በስብሰባው ቦታ ሥርዓታማ መሆናችንን ማሳየት የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
6 ሥርዓታማ መሆናችን መንፈስን ያድሳል፦ “ራሳቸውን የሚወዱ” እና የሌሎች ስሜት ምንም ግድ የማይሰጣቸው ሰዎች በሞሉበት በዚህ ጊዜ ሥርዓታማ ለመሆን ጥረት ከሚያደርጉ ክርስቲያን ባልንጀሮቻችን ጋር መሰብሰብ ምንኛ መንፈስን የሚያድስ ነው! (2 ጢሞ. 3:2) የመሰብሰቢያ ቦታው 2:00 ሰዓት ላይ ሲከፈት ተረጋግተን ሥርዓት ባለው መንገድ በመግባት እንዲሁም በቤታችን ለሚኖሩ፣ ከእኛ ጋር በመኪና ለሚጓዙ ወይም መጽሐፍ ቅዱስ እያስጠናናቸው ላሉ ሰዎች ብቻ መቀመጫ በመያዝ ሥርዓታማ መሆናችንን እናሳያለን። የመድረኩ ሊቀ መንበር ፕሮግራሙ ሊጀመር እንደሆነ የሚጠቁመውን ሙዚቃ እንድናዳምጥ በመጋበዝ ቦታ ቦታችንን እንድንይዝ ሲጠይቀን ይህን መመሪያ መከተል ይኖርብናል። የሞባይል ስልካችን ወይም ፔጀራችን በስብሰባው ወቅት ሌሎችን እንዳይረብሽ ጥንቃቄ ማድረጋችን ሥርዓት እንዳለን ያሳያል። ስብሰባው በመካሄድ ላይ እያለ ወሬ ማውራት፣ በሞባይል ስልኮች የጽሑፍ መልእክት መለዋወጥ፣ ምግብ መብላት አሊያም ወዲያ ወዲህ ማለት ሥርዓታማ እንደሆንን የሚያሳይ አይደለም።
7. ከወንድሞቻችን ጋር በምንሰበሰብበት ወቅት እኛም ሆንን ሌሎች ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
7 መንፈስን የሚያድስ ወዳጅነት፦ የአውራጃ ስብሰባዎች መንፈስን የሚያድሰው ክርስቲያናዊ አንድነታችንንና ወንድማማቻዊ ፍቅራችንን ለማጣጣም የሚያስችል ሰፊ አጋጣሚ ይከፍቱልናል። (መዝ. 133:1-3) ታዲያ ‘ልብህን ወለል አድርገህ በመክፈት’ ከሌሎች ጉባኤዎች የመጡ ወንድሞችንና እህቶችን ለምን አትተዋወቅም? (2 ቆሮ. 6:13) በየቀኑ ቢያንስ ከአንድ አዲስ ሰው ወይም ቤተሰብ ጋር ለመተዋወቅ ግብ ልታወጣ ትችላለህ። የምሳ ሰዓት እረፍታችን ይህን ለማድረግ የሚያስችል ጥሩ አጋጣሚ ይከፍትልናል። በመሆኑም በቅርብ ወዳለ ሆቴል ሄደህ ምግብ ከመግዛት ወይም እዚያው ከመብላት ይልቅ ቀለል ያለ ምግብ ይዘህ መምጣትህ በስብሰባው ቦታ ለመመገብና ከሌሎች ጋር ጥሩ ጊዜ ለማሳለፍ ያስችልሃል። ይህም አዲስና ዘላቂ ወዳጆች እንድታፈራ መንገድ ይከፍትልህ ይሆናል።
8. በስብሰባው ላይ ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆነን ለማገልገል ራሳችንን ማቅረብ ያለብን ለምንድን ነው? ይህን ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?
8 እንደ እኛ ይሖዋን ከሚያመልኩ ወንድሞች ጋር ቅዱስ በሆነ አገልግሎት መካፈል ምንኛ መንፈስን የሚያድስ ነው! አንተም ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆነህ ማገልገል ወይም ከጉባኤህ ጋር በጽዳት ሥራ መካፈል ትችል ይሆን? (መዝ. 110:3) እስከ አሁን ምንም የሥራ ምድብ ካልተሰጠህ እባክህ የስብሰባውን የፈቃደኛ አገልግሎት ክፍል ቀርበህ አነጋግር። በርካታ ወንድሞች ራሳቸውን ሲያቀርቡ ሥራው ቀላልና አስደሳች ይሆናል።
9. በስብሰባው ወቅት ለምናሳየው ምግባርና ለአለባበሳችን ለየት ያለ ትኩረት መስጠት ያለብን ለምንድን ነው?
9 ምግባራችን የሌሎች ሰዎችን መንፈስ ያድሳል፦ ስብሰባው በሚካሄድበት ሰዓት ብቻ ሳይሆን በሦስቱም ቀናት የአውራጃው ስብሰባ ልዑካን ነን። ስብሰባው በሚደረግበት ከተማ የሚያዩን ሰዎች በሙሉ በእኛና የይሖዋ ምሥክር ባልሆኑ ሰዎች መካከል ያለውን ልዩነት በግልጽ መመልከት መቻል አለባቸው። (1 ጴጥ. 2:12) በስብሰባው ላይ፣ ባረፍንበት ቦታ እንዲሁም በምግብ ቤቶች ውስጥ የምንለብሰው ልብስም ሆነ አጋጌጣችን ይሖዋን የሚያስከብር ዓይነት መሆን አለበት። (1 ጢሞ. 2:9, 10) የአውራጃ ስብሰባውን ባጅ ማድረጋችን ሌሎች ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችንን እንዲያውቁ ያስችላቸዋል። ይህ ደግሞ ስለ ስብሰባው ለመናገርና ተጨማሪ ምሥክርነት ለመስጠት አጋጣሚ ሊከፍትልን ይችላል።
10. የሆቴልና የምግብ ቤት ሠራተኞች ስለ ስብሰባችን ጥሩ አመለካከት እንዲኖራቸው ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
10 በሆቴሎችና በምግብ ቤቶች ውስጥ ከሚሠሩ ሠራተኞች ጋር መተባበር የምንችለው እንዴት ነው? ሆቴል ውስጥ ክፍል እንዲያዝልን በምንጠይቅበት ጊዜ ከምንጠቀምበት ቁጥር በላይ ማስያዝ አይኖርብንም፤ ምክንያቱም እንዲህ ማድረግ ሌሎች ወንድሞች ክፍል አጥተው እንዲቸገሩ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ ሆቴሉ ያገኝ የነበረውን ገቢ ያሳጣዋል። ወደ ሆቴሉ ስንገባ ወይም ሆቴሉን ለቅቀን ስንወጣ ቶሎ መስተንግዶ ሳናገኝ ብንቀር ትዕግሥት ማሳየት የሚኖርብን ከመሆኑም ሌላ ንግግራችን ለዛ ያለው ሊሆን ይገባል። (ቆላ. 4:6) ለምግብ ቤት አስተናጋጆች እንዲሁም ዕቃችንን ለሚያጓጉዙልን፣ ክፍላችንን ለሚያጸዱልንና ሌሎች አገልግሎቶችን ለሚሰጡን የሆቴል ሠራተኞች ጉርሻ ወይም ቲፕ መስጠት ይኖርብናል።
11. ክርስቲያናዊ ምግባር ማሳየት ጥሩ ምሥክርነት እንደሚሰጥ የሚያሳዩ ምን ተሞክሮዎች አሉ?
11 በስብሰባው ወቅት የምናሳየው መልካም ምግባር ሌሎች ምን ስሜት እንዲያድርባቸው ሊያደርግ ይችላል? አንድ ጋዜጣ፣ የአውራጃ ስብሰባ የተደረገበት የአንድ ሕንፃ ሥራ አስኪያጅ እንዲህ ማለታቸውን ዘግቧል፦ “ሰዎቹ በጣም ጨዋዎች ናቸው። በየዓመቱ እነሱን ማስተናገድ በመቻላችን ደስተኞች ነን።” የይሖዋ ምሥክር ያልሆነ አንድ ሰው ባለፈው ዓመት የአውራጃ ስብሰባው ልዑካን በተጠቀሙበት ሆቴል ውስጥ የኪስ ቦርሳውን ጥሎ ነበር። ቦርሳው ከውስጡ ምንም ሳይጎድል ለሆቴሉ ሥራ አስኪያጅ ሲመለስ፣ ሥራ አስኪያጁ ለባለ ንብረቱ እንዲህ አሉት፦ “የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ አካባቢ ስብሰባ እያደረጉ በመሆኑና ሆቴሉ በእነሱ በመሞላቱ እድለኛ ነህ። ይህ ባይሆን ኖሮ ምናልባት ቦርሳህን መልሰህ ላታገኘው ትችል ነበር።”
12. የአውራጃ ስብሰባው እየተቃረበ ሲሄድ ግባችን ምን ሊሆን ይገባል? ለምንስ?
12 በዚህ ዓመት የአውራጃ ስብሰባ የምናደርግበት ጊዜ እየቀረበ ነው። ትምህርቱም ሆነ ከስብሰባው ጋር የተያያዙት ሁኔታዎች በመንፈሳዊ የሚያድሱ እንዲሆኑ ለማድረግ ብዙ ጊዜና ከፍተኛ ጥረት ይጠይቃል። በሦስቱም ቀን ስብሰባ ላይ የመገኘት ግብ አውጣ፤ እንዲሁም ይሖዋና ድርጅቱ ባዘጋጁልህ መንፈሳዊ ድግስ ላይ ለመገኘት ዝግጅት አድርግ። ሥርዓታማ በመሆን፣ ከወንድሞች ጋር በመቀራረብ እንዲሁም መልካም ምግባር በማሳየት የሌሎችን መንፈስ ለማደስ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። እንዲህ ካደረግክ አንተም ሆንክ ሌሎች፣ ባለፈው ዓመት በአውራጃ ስብሰባ ላይ ከተካፈለች በኋላ “ከዚህ ቀደም እንዲህ ያለ አስደሳች ጊዜ አሳልፌ አላውቅም!” ብላ እንደተናገረችው እህት እንደሚሰማችሁ እሙን ነው።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ከዚህ ቀደም እናደርግ እንደነበረው የአውራጃ ስብሰባችን ከመጀመሩ ሦስት ሳምንታት ቀደም ብለን ሌሎች በስብሰባው ላይ እንዲገኙ ለመጋበዝ በሚደረገው ዘመቻ ላይ እንካፈላለን
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
በስብሰባው ላይ፣ ባረፍንበት ቦታ እንዲሁም በምግብ ቤቶች ውስጥ የምንለብሰው ልብስም ሆነ አጋጌጣችን ይሖዋን የሚያስከብር ዓይነት መሆን አለበት
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ሥርዓታማ በመሆን፣ ከወንድሞች ጋር በመቀራረብ እንዲሁም መልካም ምግባር በማሳየት የሌሎችን መንፈስ ለማደስ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ
[ከገጽ 4-7 የሚገኝ ሣጥን]
የ2011 የአውራጃ ስብሰባ ማሳሰቢያዎች
◼ የስብሰባው ሰዓት፦ ፕሮግራሙ በሦስቱም ቀናት ከጠዋቱ 3:20 ላይ ይጀምራል። በመሰብሰቢያ ቦታው ወንበር መያዝ የሚቻለው ከጠዋቱ 2:00 ሰዓት ጀምሮ ነው። የመክፈቻው ሙዚቃ ሊጀምር እንደሆነ የሚገልጽ ማስታወቂያ ሲነገር ሁላችንም ቦታ ቦታችንን መያዝ ይኖርብናል፤ ይህም ፕሮግራሙን ክብር ባለው መንገድ ለማስጀመር ያስችላል። ፕሮግራሙ ዓርብና ቅዳሜ 10:55 እንዲሁም እሁድ 9:40 ላይ ይደመደማል።
◼ መኪና ማቆሚያ፦ አብዛኛውን ጊዜ ያለው የመኪና ማቆሚያ ውስን በመሆኑ መኪና ካለው ሰው ጋር በመሄድ የመኪናዎቹን ቁጥር መቀነስ እንችላለን። በተጨማሪም በራሳችሁ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት እባካችሁ ጥረት አድርጉ።
◼ መቀመጫ መያዝ፦ መቀመጫ መያዝ የሚቻለው ከእናንተ ጋር በመኪና ለሚመጡ፣ በአንድ ቤት አብረዋችሁ ለሚኖሩ እንዲሁም ከእናንተ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ላይ ለሚገኙ ሰዎች ብቻ መሆኑን አስታውሱ።—1 ቆሮ. 13:5
◼ ምሳ፦ በእረፍት ሰዓት ምግብ ፍለጋ ከስብሰባው ቦታ ወጥታችሁ ከመሄድ ይልቅ እባካችሁ ምሳ ይዛችሁ ኑ። በመቀመጫችሁ ሥር ሊቀመጥ የሚችል መጠነኛ ዕቃ መጠቀም ይቻላል። ትላልቅ ዕቃዎችንና ጠርሙስ ነክ ዕቃዎችን ወደ ስብሰባው ቦታ ማምጣት አይፈቀድም።
◼ መዋጮ፦ በመንግሥት አዳራሽም ሆነ በአውራጃ ስብሰባ ላይ ለዓለም አቀፉ ሥራ በፈቃደኝነት መዋጮ በማድረግ ለስብሰባው የተሰማንን አድናቆት መግለጽ እንችላለን። በአውራጃ ስብሰባው ላይ መዋጮ የሚደረጉ ቼኮች ሁሉ ለ“የይሖዋ ምሥክሮች” የሚከፈሉ መሆናቸው መገለጽ አለበት።
◼ አደጋዎችና ድንገተኛ ሕመም፦ አንድ ሰው በስብሰባው ቦታ ላይ ድንገተኛ ሕመም ካጋጠመው የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ መስጫ ክፍል የሚገኝበትን ቦታ እንዲጠቁማችሁ በቅርብ ያለውን አስተናጋጅ አነጋግሩ።
◼ መድኃኒቶች፦ በሐኪም ትእዛዝ መድኃኒት እየወሰዳችሁ ከሆነ እንዲህ ዓይነት መድኃኒቶች በስብሰባው ቦታ ስለማይኖሩ እባካችሁ የምትወስዷቸውን መድኃኒቶች መያዛችሁን አረጋግጡ።
◼ ጫማ፦ በየዓመቱ ከጫማ ጋር በተያያዘ ብዙ ጉዳት ይደርሳል። በመሆኑም በደረጃዎችና እነዚህ በመሳሰሉ ቦታዎች ስትራመዱ ጉዳት እንዳይደርስባችሁ ልከኛና ምቹ የሆነ ጫማ እንድታደርጉ እናበረታታችኋለን።
◼ የመስማት ችግር ያለባቸው፦ ስብሰባው በአንዳንድ ቦታዎች በኤፍኤም የሬዲዮ ሞገድ ይተላለፋል። በዚህ ዝግጅት መጠቀም እንድትችሉ በባትሪ የሚሠራ የኤፍኤም መቀበያና የጆሮ ማዳመጫ ይዛችሁ መምጣት ያስፈልጋችኋል።
◼ የሕፃናት ጋሪዎችና የመናፈሻ ወንበሮች፦ የሕፃናት ጋሪዎችንና የመናፈሻ ወንበሮችን ወደ ስብሰባው ቦታ ይዞ መምጣት ተገቢ አይደለም። ይሁን እንጂ ከወላጆች አጠገብ ባለ ወንበር ላይ ሊታሰሩ የሚችሉ ለልጆች ደህንነት ተብለው የሚዘጋጁ ወንበሮችን (child-safety seats) ይዞ መምጣት ይቻላል።
◼ ምግብ ቤቶች፦ ምግብ ቤት በምትመገቡበት ጊዜ መልካም ምግባር በማሳየት የይሖዋን ስም አስከብሩ። በአካባቢው የተለመደ ከሆነ ለአስተናጋጆች ጉርሻ ስጡ።
◼ መንግሥት አዳራሾችን መጠቀም፦ የመንግሥት አዳራሾችን ለማደሪያነት ባትጠቀሙባቸው እንመርጣለን። መንግሥት አዳራሾችን ለዚህ ዓላማ መጠቀም የግድ ከሆነ ግን ሁሉም ሰው የመንግሥት አዳራሹን ምንጊዜም ንጹሕና ሥርዓታማ አድርጎ የመያዝ ኃላፊነት እንዳለበት ሊሰማው ይገባል። መተኛዎቹ በሥርዓት ተጣጥፈው መቀመጥ ይኖርባቸዋል፤ የፈሰሰ ነገር ካለ ወዲያውኑ መወልወል ይገባዋል፤ እንዲሁም ወረቀቶችና ሌሎች ቆሻሻዎች በቅርጫት ወይም በሌላ ነገር ውስጥ መሰብሰብ ይኖርባቸዋል።
◼ ጽዳት፦ የንጽሕና ክፍል የመሰብሰቢያ ቦታው በፕሮግራም እንዲጸዳ ዝግጅት የሚያደርግ ቢሆንም ሁላችንም ይሖዋ ከሕዝቦቹ የሚጠብቀውን የንጽሕና መሥፈርት ለመጠበቅ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት እንችላለን። በመሆኑም በአዳራሹ ወለል ላይም ይሁን በግቢው ውስጥ ወረቀት ወይም ሌላ ቆሻሻ መጣል ተገቢ አይደለም። ቆሻሻዎች ለዚያ ዓላማ በተዘጋጁ ቅርጫቶች ውስጥ መጣል ይኖርባቸዋል። እንዲህ የሚደረግ ከሆነ የአውራጃ ስብሰባው የሚካሄድበት ቦታ በፕሮግራሙ ወቅትም ሆነ በእረፍት ሰዓት የተዝረከረከ አይሆንም። በተጨማሪም ከተቀመጥንበት ቦታ ስንነሳ የወደቀ ነገር ካለ ለማንሳት ዞር ዞር ብለን አካባቢውን መመልከታችን የሚያስመሰግን ነው።
◼ እባካችሁ ተከታትላችሁ እርዱት (S-43) የተባለው ቅጽ፦ እባካችሁ ተከታትላችሁ እርዱት የሚለው ቅጽ በስብሰባው ላይ መደበኛ ባልሆነ መንገድ መሥክረንለት ፍላጎት ያሳየን ሰው በሚመለከት መረጃ ለመስጠት ያገለግላል። ቅጹን ከሞላችሁ በኋላ ለአውራጃ ስብሰባው የጽሑፍ ክፍል አሊያም ወደ ጉባኤያችሁ ስትመለሱ ለጉባኤው ጸሐፊ ልትሰጡት ትችላላችሁ።
◼ የፈቃደኛ አገልግሎት፦ ፈቃደኛ ሠራተኞች ሆነን አስፈላጊ ሥራዎች የምናከናውን ከሆነ በአውራጃ ስብሰባው ላይ የምናገኘው ደስታ እጥፍ ድርብ ይሆናል። (ሥራ 20:35) ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆነው ማገልገል የሚፈልጉ ሁሉ በስብሰባው ቦታ ለሚገኘው የፈቃደኛ አገልግሎት ክፍል ማሳወቅ ይኖርባቸዋል። ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች በወላጅ አሊያም ወላጅ በሚመድብላቸው ሞግዚት ወይም ሌላ ትልቅ ሰው ሥር በመሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
መጋበዣ ወረቀቱን ማሰራጨት የምንችለው እንዴት ነው?
ክልላችንን መሸፈን እንድንችል መግቢያችን አጠር ያለ መሆን ይኖርበታል። እንዲህ ማለት እንችላለን፦ “ጤና ይስጥልኝ። ይህን የመጋበዣ ወረቀት በዓለም ዙሪያ እያሰራጨን ነው። ይህ የእርስዎ ቅጂ ነው። ተጨማሪ ማብራሪያዎችን በመጋበዣ ወረቀቱ ላይ ያገኛሉ።” የመጋበዣ ወረቀቱ የመጀመሪያ ገጽ የተዘጋጀው የሰዎችን ትኩረት እንዲስብ ተደርጎ ስለሆነ የቤቱ ባለቤት እንዲያየው አድርገን መስጠት ይኖርብናል። ስትናገር ግለት ይኑርህ። በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት መጋበዣውን ስታሰራጭ ሁኔታው የሚያመች ከሆነ መጽሔቶችንም አብረህ ማበርከት ይኖርብሃል።