አምላክን የሚያስከብር ምግባር
1. የይሖዋ ምሥክሮች በአውራጃ ስብሰባ ላይ ሲካፈሉ በቀላሉ በሰዎች ዓይን ውስጥ የሚገቡት ለምንድን ነው?
1 በአውራጃ ስብሰባ ላይ ስንካፈል በቀላሉ በሰዎች ዓይን ውስጥ እንገባለን። ስብሰባው በሚደረግባቸው በርካታ ከተሞች ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ሊያደርጉ እንደሆነ የሚገልጽ መረጃ ለማኅበረሰቡ ይሰጣሉ። በአብዛኛው ሆቴሎችና ምግብ ቤቶች ለስብሰባው በመጡ ልዑካን ይሞላሉ፤ የአካባቢው ነዋሪዎችም በርካታ ሰዎች የስብሰባ ባጅ እንዳደረጉ ያስተውላሉ። በመሆኑም የአውራጃ ስብሰባው በሚደረግበት ከተማ ውስጥ በምንቆይበት ጊዜ አምላክን የሚያስከብር ጥሩ ምግባር እንዴት ማሳየት እንደምንችል የሚገልጹ አንዳንድ ማሳሰቢያዎች ከዚህ ቀጥሎ ቀርበዋል።—1 ጴጥ. 2:12
2. የአውራጃ ስብሰባው በሚደረግበት ከተማ ውስጥ በምንቆይበት ጊዜ ልከኛ አለባበስ በመልበስ አምላክን ማስከበር የምንችለው እንዴት ነው?
2 ልከኛ አለባበስ፦ በስብሰባው ላይ ስንገኝ ልከኛ አለባበስ መልበሳችን ብዙዎችን እንደሚማርክ የታወቀ ነው። ይሁንና በሌሎች ጊዜያት ማለትም ሆቴል ስንይዝ፣ ወደ ምግብ ቤቶች ስንሄድ፣ ገበያ ስንወጣ ወይም ሌሎች ነገሮች ስናደርግ አለባበሳችን ሌሎች ለእኛ ባላቸው አመለካከት ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳድራል። በእነዚህ ወቅቶች ለስብሰባዎች እንደምንለብሰው ዓይነት ልብስ መልበስ ባያስፈልገንም አለባበሳችን ልከኛ፣ ክብር ያለውና ግዴለሽነት የማይንጸባረቅበት መሆን ይኖርበታል። የሚመለከቱን ሰዎች በእኛና ይሖዋን በማያመልኩ ሰዎች መካከል ልዩነት እንዳለ ማስተዋል መቻል ይኖርባቸዋል። (ሮም 12:2) በተጨማሪም የስብሰባውን ባጅ ማድረግ ይኖርብናል፤ እንዲህ ማድረጋችን ስለ ስብሰባው ለሰዎች ለማሳወቅ፣ የመመሥከር አጋጣሚ ለማግኘት አልፎ ተርፎም ሌሎች ልዑካን እንዲለዩን ያስችላል።
3. ትዕግሥትና ጥሩ ምግባር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
3 ትዕግሥትና ጥሩ ምግባር፦ በጊዜያችን በዓለም ላይ ያሉ ብዙ ሰዎች ስለ ራሳቸው ብቻ የሚያስቡና የማያመሰግኑ ናቸው። በመሆኑም ትዕግሥተኞች መሆናችንና ጥሩ ምግባር ማሳየታችን በሆቴል ወይም በምግብ ቤት ውስጥ የሚሠሩትን ጨምሮ ለሌሎች ሰዎች የእረፍት ምንጭ እንደሚሆንላቸው ምንም ጥርጥር የለውም! (2 ጢሞ. 3:1-5) ወንበር ስንይዝ ወይም አዲስ የወጡ ጽሑፎችን ለመቀበል ወረፋ ስንጠብቅ የራሳችንን ሳይሆን የሌላውን ሰው ጥቅም መፈለግ ይኖርብናል። (1 ቆሮ. 10:23, 24) አንድ ፍላጎት ያሳየ ሰው፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በአውራጃ ስብሰባ ላይ ከተገኘ በኋላ እንዲህ ብሏል፦ “በዚያን ቀን ከተሰጡት ንግግሮች መካከል አንዱንም አላስታውስም፤ ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮቹ ያሳዩት ምግባር ከአእምሮዬ ሊጠፋ አልቻለም።”
4. ሁኔታችን የሚፈቅድ ከሆነ በአውራጃ ስብሰባው ላይ ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆነን ለማገልገል ማሰብ ያለብን ለምንድን ነው?
4 ፈቃደኛ ሠራተኞች፦ ራስን በፈቃደኝነት የማቅረብ መንፈስ እውነተኛ ክርስቲያኖች ከሚታወቁባቸው ባሕርያት አንዱ ነው። (መዝ. 110:3) በአውራጃ ስብሰባው ላይ ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆነህ ማገልገል ትችል ይሆን? በአንድ አውራጃ ስብሰባ ላይ ወደ 600 የሚጠጉ ወንድሞችና እህቶች ከስብሰባው በፊት በፈቃደኝነት የመሰብሰቢያ ቦታውን አጽድተው ነበር። የድርጅቱ ሠራተኞች “እንዲህ ዓይነት ነገር አይተን አናውቅም! ይህ ሁሉ ሰው ፈቃደኛ ሠራተኛ ነው ብሎ ማሰብ የሚከብድ ነገር ነው” ብለዋል። የ2013 የአውራጃ ስብሰባን በጉጉት እንጠብቃለን፤ ይህ ወቅት ለመስማትና ከአምላክ ለመማር ብቻ ሳይሆን እሱን የሚያስከብር ምግባር ለማሳየትም አጋጣሚ ስለሚሰጠን ስብሰባውን በጉጉት መጠበቃችን የተገባ ነው።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የ2013 የአውራጃ ስብሰባ ማሳሰቢያዎች
◼ የስብሰባው ሰዓት፦ በመሰብሰቢያ ቦታው ወንበር መያዝ የሚቻለው ከጠዋቱ 2:00 ሰዓት ጀምሮ ነው። በሦስቱም ቀናት የመክፈቻው ሙዚቃ የሚጀምረው ከጠዋቱ 3:20 ላይ ነው። በዚህ ጊዜ ሁላችንም ቦታ ቦታችንን መያዝ ይኖርብናል፤ ይህም ፕሮግራሙን ክብር ባለው መንገድ ለማስጀመር ያስችላል። የመደምደሚያው መዝሙርና ጸሎት የሚተዋወቁት ዓርብና ቅዳሜ 10:50 እንዲሁም እሁድ 9:35 ላይ ይሆናል።
◼ መኪና ማቆሚያ፦ አውራጃ ስብሰባ በሚደረግባቸው በሁሉም ቦታዎች ላይ የመኪና ማቆሚያው በእኛ ሥር ከሆነ ተሰብሳቢዎቹ በሙሉ እንደ አመጣጣቸው ያለምንም ክፍያ ይስተናገዳሉ። ያለው የመኪና ማቆሚያ አብዛኛውን ጊዜ ውስን ስለሚሆን በተቻለ መጠን መኪናችሁን በመተው ከሌላው ጋር ተዳብላችሁ የምትሄዱ ከሆነ የመኪናዎችን ቁጥር መቀነስ ይቻላል። በተጨማሪም ጉባኤያችሁ በተመደበበት የአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት እባካችሁ ጥረት አድርጉ።
◼ ወንበር መያዝ፦ ወንበር መያዝ የሚቻለው ከእናንተ ጋር በመኪና ለሚመጡ፣ በአንድ ቤት አብረዋችሁ ለሚኖሩ እንዲሁም ከእናንተ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ላይ ለሚገኙ ሰዎች ብቻ መሆኑን አስታውሱ።—1 ቆሮ. 13:5
◼ ምሳ፦ በእረፍት ሰዓት ምግብ ፍለጋ ከስብሰባው ቦታ ወጥታችሁ ከመሄድ ይልቅ እባካችሁ ቀለል ያለ ምሳ ይዛችሁ ኑ። ወንበራችሁ ሥር ሊቀመጥ የሚችል የምግብ መያዣ ዕቃ መጠቀም ይቻላል። ትላልቅ የምግብ መያዣ ዕቃዎችንና ጠርሙስ ነክ ዕቃዎችን ወደ ስብሰባው ቦታ ማምጣት አይፈቀድም።
◼ መዋጮ፦ በአውራጃ ስብሰባ ላይ ለዓለም አቀፉ ሥራ በፈቃደኝነት መዋጮ በማድረግ ለዝግጅቱ ያለንን አድናቆት መግለጽ እንችላለን። ቼኮች ሁሉ ለ“የይሖዋ ምሥክሮች” የሚከፈሉ መሆናቸው መገለጽ አለበት።
◼ መድኃኒቶች፦ በሐኪም ትእዛዝ የምትወስዱት መድኃኒት ካለ እንዲህ ዓይነት መድኃኒቶች በስብሰባው ቦታ ስለማይኖሩ እባካችሁ የምትወስዷቸውን መድኃኒቶች በበቂ መጠን መያዛችሁን አረጋግጡ።
◼ ጫማ፦ በየዓመቱ ከጫማ በተለይም ከታኮ ጫማ ጋር በተያያዘ ጉዳት ይደርሳል። በመሆኑም ሊያንሸራትቱ በሚችሉ ስፍራዎች፣ በደረጃዎች፣ የሚያሾልኩ ቀዳዳዎች ባሉት ወለል ላይና እነዚህ በመሳሰሉ ቦታዎች ስትራመዱ ጉዳት እንዳይደርስባችሁ ልከኛና ምቹ የሆነ ጫማ እንድታደርጉ እናበረታታችኋለን።
◼ የመስማት ችግር ያለባቸው፦ በአንዳንድ ቦታዎች ስብሰባው በኤፍኤም የሬዲዮ ሞገድ ይተላለፋል። በዚህ ዝግጅት መጠቀም እንድትችሉ በባትሪ የሚሠራ የኤፍኤም መቀበያና የጆሮ ማዳመጫ ይዛችሁ መምጣት ያስፈልጋችኋል።
◼ የሕፃናት ጋሪዎችና የመናፈሻ ወንበሮች፦ የሕፃናት ጋሪዎችንና የመናፈሻ ወንበሮችን ወደ ስብሰባው ቦታ ይዞ መምጣት ተገቢ አይደለም። ይሁን እንጂ ከወላጆች አጠገብ ባለ ወንበር ላይ ሊታሰሩ የሚችሉ ለልጆች ደህንነት ተብለው የሚዘጋጁ ወንበሮችን (ቻይልድ ሴፍቲ ሲትስ) ይዞ መምጣት ይቻላል።
◼ እባካችሁ ተከታትላችሁ እርዱት (S-43) የተባለው ቅጽ፦ እባካችሁ ተከታትላችሁ እርዱት የሚለው ቅጽ በስብሰባው ላይ መደበኛ ባልሆነ መንገድ መሥክረንለት ፍላጎት ያሳየን ሰው በሚመለከት መረጃ ለመስጠት ያገለግላል። ቅጹን ከሞላችሁ በኋላ ለአውራጃ ስብሰባው የጽሑፍ ክፍል አሊያም ወደ ጉባኤያችሁ ስትመለሱ ለጉባኤው ጸሐፊ ልትሰጡት ትችላላችሁ።
◼ ምግብ ቤቶች፦ ምግብ ቤት በምትመገቡበት ጊዜ መልካም ምግባር በማሳየት የይሖዋን ስም አስከብሩ። ከአንድ ክርስቲያን የሚጠበቅ አለባበስ ይኑራችሁ። በአካባቢው የተለመደ ከሆነ ለአስተናጋጆች ጉርሻ ወይም ቲፕ ስጡ።
◼ መንግሥት አዳራሾችን መጠቀም፦ የመንግሥት አዳራሾችን ለማደሪያነት ባንጠቀምባቸው እንመርጣለን። መንግሥት አዳራሾችን ለዚህ ዓላማ መጠቀም የግድ ከሆነ ግን ሁሉም ሰው የመንግሥት አዳራሹን ምንጊዜም ንጹሕና ሥርዓታማ በሆነ መንገድ የመያዝ ኃላፊነት እንዳለበት ሊሰማው ይገባል። መተኛዎቹ በሥርዓት ተጣጥፈው መቀመጥ ይኖርባቸዋል፤ የፈሰሰ ነገር ካለ ወዲያውኑ መወልወል ይገባዋል፤ እንዲሁም ወረቀቶችና ሌሎች ቆሻሻዎች በቅርጫት ወይም በሌላ ነገር ውስጥ መሰብሰብ ይኖርባቸዋል።
◼ ሆቴሎች፦
(1) የምትችሉ ከሆነ ሆቴል ውስጥ ማረፋችሁ የተሻለ ነው። እባካችሁ ከሚያስፈልጋችሁ በላይ ብዙ ክፍሎችን አትያዙ፤ እንዲሁም ሆቴሉ ከሚፈቅደው በላይ ሰዎችን በክፍላችሁ አታሳድሩ።
(2) ከአቅም በላይ የሆነ ነገር ካላጋጠማችሁ በስተቀር የያዛችሁትን ሆቴል አትሰርዙ፤ ይሁንና መሰረዝ ካስፈጋችሁ በአፋጣኝ ለሆቴሉ አሳውቁ። እንዲህ ማድረጋችሁ ሌሎች ክፍል ማግኘት እንዲችሉ ይረዳል።—ማቴ. 5:37
(3) በአገራችሁ የተለመደ ከሆነ የሆቴሉ ሠራተኞች ሻንጣ ሲሸከሙላችሁ ጉርሻ ስጧቸው፤ የሆቴል ክፍላችሁን ለሚያጸዳው ግለሰብም በየዕለቱ እንዲህ ማድረጋችሁን አትርሱ።
(4) በክፍላችሁ ውስጥ ምግብ ማብሰል የማይፈቀድ ከሆነ እንደዚያ አታድርጉ።
(5) ከሆቴሉ ሠራተኞች ጋር ባላችሁ ግንኙነት ምንጊዜም የመንፈስ ፍሬን አንጸባርቁ። ሠራተኞቹ ብዙ ሰዎችን ስለሚያስተናግዱ ደግነትና ትዕግሥት ብናሳያቸው እንዲሁም ምክንያታዊ ብንሆን ደስ ይላቸዋል።
(6) ወላጆች ልጆቻቸው በሆቴሉ ውስጥ የሚያደርጉትን ነገር ምንጊዜም መቆጣጠር ይገባቸዋል፤ ይህ ደግሞ ልጆቻቸው በአሳንሰር አጠቃቀም እንዲሁም በመዋኛ ቦታ፣ በእንግዳ መቀበያው አካባቢ፣ በጂምናዝየምና በሌሎች አካባቢዎች የሚያሳዩትን ባሕርይ መከታተልን ይጨምራል።
◼ ጽዳት፦ የንጽሕና ክፍል የመሰብሰቢያ ቦታው በፕሮግራም እንዲጸዳ ዝግጅት የሚያደርግ ቢሆንም ሁላችንም ይሖዋ ከሕዝቦቹ የሚፈልገውን የንጽሕና መሥፈርት ለመጠበቅ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት እንችላለን። በመሆኑም በአዳራሹ ወለል ላይም ይሁን በግቢው ውስጥ ወረቀት ወይም ሌላ ቆሻሻ መጣል ተገቢ አይደለም። ቆሻሻዎች ለዚያ ዓላማ በተዘጋጁ ቅርጫቶች ውስጥ መጣል ይኖርባቸዋል። እንዲህ የሚደረግ ከሆነ የአውራጃ ስብሰባው የሚካሄድበት ቦታ በፕሮግራሙ ወቅትም ሆነ በእረፍት ሰዓት የተዝረከረከ አይሆንም። በተጨማሪም ከተቀመጥንበት ቦታ ስንነሳ የወደቀ ነገር ካለ ለማንሳት ዞር ዞር ብለን አካባቢውን መመልከታችን የሚያስመሰግን ነው።
◼ የፈቃደኛ አገልግሎት፦ ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆነው ማገልገል የሚፈልጉ ሁሉ በስብሰባው ቦታ ለሚገኘው የፈቃደኛ አገልግሎት ክፍል ማሳወቅ ይኖርባቸዋል። ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች በወላጅ አሊያም ወላጅ በሚመድብላቸው ሞግዚት ወይም ሌላ ትልቅ ሰው ሥር በመሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ።