የአውራጃ ስብሰባዎቻችን ስለ እውነት ከፍተኛ ምሥክርነት ይሰጣሉ
1. እስራኤላውያን፣ በዓመታዊ በዓላት ላይ ስለ የትኞቹ መንፈሳዊ እውነቶች መወያየት እንዲሁም ማሰላሰል ይችሉ ነበር?
1 እስራኤላውያን የተለያዩ በዓላትን ለማክበር በዓመት ውስጥ ሦስት ጊዜ ይሰበሰቡ ነበር። በበዓሎቹ ላይ መገኘት የሚጠበቅባቸው ወንዶች ብቻ ቢሆኑም አብዛኛውን ጊዜ፣ በእነዚህ አስደሳች ዝግጅቶች ላይ ለመካፈል መላው ቤተሰብ ወደ ኢየሩሳሌም ይጓዝ ነበር። (ዘዳ. 16:15, 16) እነዚህ በዓላት፣ አስፈላጊ በሆኑ መንፈሳዊ እውነቶች ላይ ለማሰላሰልና ለመወያየት ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥራሉ። ከእነዚህ እውነቶች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? አንዱ ይሖዋ ለጋስና አፍቃሪ አምላክ መሆኑ ነው። (ዘዳ. 15:4, 5) ሌላው ደግሞ ይሖዋ፣ አመራርም ሆነ ጥበቃ ለማግኘት ልንታመንበት የምንችል አምላክ መሆኑ ነው። (ዘዳ. 32:9, 10) በተጨማሪም እስራኤላውያን የይሖዋን ስም የተሸከሙ እንደመሆናቸው መጠን የአምላክን የጽድቅ መንገድ በትክክል መከተላቸውን ማሳየት ስለሚችሉበት መንገድ የማሰላሰል አጋጣሚ ነበራቸው። (ዘዳ. 7:6, 11) በዛሬው ጊዜም ቢሆን በየዓመቱ ከምናደርጋቸው የአውራጃ ስብሰባዎች ተመሳሳይ ጥቅሞችን ማግኘት እንችላለን።
2. የአውራጃ ስብሰባው የእውነት ብርሃን እንዲበራ የሚያደርገው እንዴት ነው?
2 ስብሰባው የእውነት ብርሃን እንዲበራ ያደርጋል፦ በአውራጃ ስብሰባዎቻችን ላይ የሚቀርቡት ንግግሮች፣ ድራማዎች፣ ሠርቶ ማሳያዎች እንዲሁም ቃለ ምልልሶች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን በተሻለ ሁኔታ ለመረዳትና በሥራ ላይ ለማዋል ይረዱናል። (ዮሐ. 17:17) ከፊታችን የሚጠብቀንን የአውራጃ ስብሰባ ለማዘጋጀት ብዙ ሥራ እየተከናወነ ነው። የይሖዋ ድርጅት፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሰዎች በዚህ ወቅት በጣም በሚያስፈልጋቸው ነገር ላይ ትኩረት ያደረገ ፕሮግራም እያዘጋጀ ነው። (ማቴ. 24:45-47) ታዲያ የሚቀርቡትን ክፍሎች ለማዳመጥ አልጓጓህም?
3. ከፕሮግራሙ ጥቅም ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል?
3 እርግጥ ነው፣ ከሚቀርበው ትምህርት ብዙ ጥቅም ማግኘት የምንችለው ሦስቱንም ቀናት በስብሰባው ላይ ከተገኘንና በጥሞና ካዳመጥን ነው። እስከ አሁን ፈቃድ ካልጠየቃችሁ አሁኑኑ አሠሪያችሁን ማነጋገራችሁ አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም ስብሰባውን በንቃት መከታተል እንድትችሉ ማታ ማታ በቂ እረፍት ማድረጋችሁ አስፈላጊ ነው። ብዙዎች ተናጋሪውን መመልከታቸውና አጭር ማስታወሻ መያዛቸው ትኩረታቸው እንዳይከፋፈል እንደሚረዳቸው ተገንዝበዋል። እንዲሁም ሞባይላችሁ ወይም ፔጀራችሁ እናንተንም ሆነ ሌሎችን እንዳይረብሽ ጥንቃቄ አድርጉ። ስብሰባው በሚካሄድበት ወቅት ማውራት፣ በስልክ የጽሑፍ መልእክት መላላክ ብሎም መመገብ ተገቢ አይደለም።
4. ወላጆች ልጆቻቸው ከስብሰባው ጥቅም እንዲያገኙ ሊረዷቸው የሚችሉት እንዴት ነው?
4 እስራኤላውያን ቤተሰቦች የዳስ በዓልን ለማክበር በሰባት ዓመት አንዴ ሲሰበሰቡ ሕጉ ይነበብላቸው ነበር፤ በዚህ ጊዜ ‘ይሰሙና ይማሩ ዘንድ ልጆቻቸውን’ ወደ ስብሰባው ይዘው ይሄዱ ነበር። (ዘዳ. 31:12) ዛሬም፣ በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ቤተሰቦች አብረው ሲቀመጡ መመልከት እንዲሁም ትናንሽ ልጆች በጥሞና ሲያዳምጡ ማየት ምንኛ የሚያስደስት ነው! የእያንዳንዱ ቀን ስብሰባ ከተካሄደ በኋላ ምሽት ላይ ማስታወሻችሁን በመጠቀም በዕለቱ ከቀረበው ትምህርት ውስጥ የነካችሁን ሐሳብ ለምን አትወያዩም? መጽሐፍ ቅዱስ “ሞኝነት በሕፃን ልብ ታስሮአል” ይላል፤ በመሆኑም ወላጆች በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙትን ጨምሮ ሁሉም ልጆቻቸው ‘መረን እንዳይለቁ’ መቆጣጠራቸው አስፈላጊ ነው። ወላጆች በምሳ ሰዓትም ሆነ በሚያርፉበት ቦታ ይህን ማድረግ ይኖርባቸዋል።—ምሳሌ 22:15፤ 29:15
5. በምናርፍበት ሆቴል ውስጥ መልካም ምግባር ማሳየታችን እውነትን የሚያስውበው እንዴት ነው?
5 መልካም ምግባራችን እውነትን ያስውበዋል፦ የአውራጃ ስብሰባው በሚካሄድበት ከተማ የምናሳየው መልካም ምግባር እውነትን ያስውባል። (ቲቶ 2:10) የሆቴል ቤት ሠራተኞች፣ የሆቴሉን ደንብ ለሚያከብሩ ብሎም ሠራተኞችን በትዕግሥትና በአክብሮት ለሚይዙ ሰዎች አድናቆት አላቸው። (ቆላ. 4:6) አንዲት የሆቴል ቤት ኃላፊ እንዲህ ብላለች፦ “የእናንተ ሰዎች ጥሩ ስለሆኑ ወደ ሆቴላችን ሲመጡ ደስ ይለናል። መልካም ምግባር ያላቸውና ደጎች ናቸው፤ እንዲሁም ሆቴላችንንም ሆነ ሠራተኞቻችንን ምንጊዜም በአክብሮት ይይዛሉ።”
6. የአውራጃ ስብሰባው በሚደረግበት ከተማ ውስጥ በሚኖረን ቆይታ በአለባበሳችን እውነትን ማስዋብ የምንችለው እንዴት ነው?
6 የአውራጃ ስብሰባውን ባጅ ማድረጋችን ስብሰባውን ለማስተዋወቅ ብሎም ሌሎች ተሰብሳቢዎች ለይተው እንዲያውቁን የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ ለሚመለከቱን ሰዎች ምሥክርነት ይሰጣል። የአውራጃ ስብሰባው በሚደረግበት ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች የስብሰባውን ባጅ ያደረጉ ሰዎች ንጹሕና ልከኛ ልብስ እንደለበሱ እንዲሁም አለባበሳቸው በዓለም ከተለመደው ቅጥ ያጣና የፆታ ስሜትን የሚያነሳሳ አለባበስ የተለየ እንደሆነ ማስተዋላቸው አይቀርም። (1 ጢሞ. 2:9, 10) በመሆኑም የአውራጃ ስብሰባው በሚደረግበት ከተማ ውስጥ በምንቆይባቸው ቀናት ሁሉ ለአለባበሳችንና ለፀጉር አያያዛችን ትኩረት መስጠታችን የተገባ ነው። ስብሰባው የሚደረገው ክፍት በሆነ ስታዲየም ቢሆንና አካባቢው የሚሞቅ ቢሆንም እንኳ አለባበሳችን የሚያስከብር መሆን አለበት። እርግጥ ከስብሰባው በኋላ ልብሳችንን ቀይረን ምግብ ቤት መሄድ ብንፈልግ እንኳ በዚህ ወቅትም ቢሆን የአውራጃ ስብሰባው ልዑካን መሆናችንን ተገንዝበን የተዝረከረከና ግዴለሽነት የሚንጸባረቅበት ልብስ መልበስ ተገቢ እንዳልሆነ መዘንጋት የለብንም።
7. በአውራጃ ስብሰባ ወቅት ክርስቲያናዊ አንድነታችንን ለማጠናከር የሚያስችል ምን አጋጣሚ አለን?
7 እስራኤላውያን በሚያከብሯቸው ዓመታዊ በዓላት ላይ፣ ከሌሎች ከተሞችም ሆነ የዓለም ክፍሎች ከሚመጡ የእምነት አጋሮቻቸው ጋር በመቀራረብ የሚያንጽ ጊዜ ማሳለፍ ይችሉ ነበር፤ ይህ ደግሞ አንድነታቸውን ያጠናክርላቸዋል። (ሥራ 2:1, 5) በአውራጃ ስብሰባዎቻችን ላይ ልዩ የሆነው ክርስቲያናዊ ወንድማማችነታችን በግልጽ ይታያል። ግሩም የሆነው ይህ የመንፈሳዊው ገነት አንዱ ገጽታ ብዙውን ጊዜ ተመልካቾችን ይማርካል። (መዝ. 133:1) ምግብ ለመግዛት ከስብሰባው ቦታ ከመውጣት ይልቅ ቀለል ያለ ምሳ ይዘን በመምጣት አጋጣሚውን በአቅራቢያችን ከተቀመጡ ወንድሞችና እህቶች ጋር ለመተዋወቅና ለመጨዋወት መጠቀማችን ምንኛ የተሻለ ነው!
8. ሁኔታችን የሚፈቅድ ከሆነ በአውራጃ ስብሰባው ላይ ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆነን ማገልገላችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?
8 ብዙ ሰዎች በጥሩ ሁኔታ የተደራጁትን የአውራጃ ስብሰባዎቻችንን ሲመለከቱ በተለይ ደግሞ ሥራው በሙሉ የሚከናወነው በፈቃደኛ ሠራተኞች መሆኑን ሲያውቁ በጣም ይገረማሉ። በአውራጃ ስብሰባው ላይ ለሚከናወነው ሥራ ራስህን ‘በገዛ ፈቃድህ’ ማቅረብ ትችል ይሆን? (መዝ. 110:3) ብዙ ወላጆች ልጆቻቸው በገዛ ፈቃዳቸው ራሳቸውን እንዲያቀርቡ ለማሠልጠን ሲሉ መላው ቤተሰብ ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆኖ እንዲያገለግል ያደርጋሉ። ዓይን አፋር ነህ? ከሆነ በአውራጃ ስብሰባው ላይ ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆነህ ማገልገልህ ከሌሎች ጋር ለመተዋወቅ ያስችልሃል። አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “ከቤተሰቦቼና በጣት ከሚቆጠሩ አንዳንድ ሰዎች በስተቀር የማውቀው ሰው አልነበረም። በጽዳት ሥራ ስካፈል ግን ከበርካታ ወንድሞችና እህቶች ጋር መተዋወቅ ችያለሁ። በዚህም በጣም ተደስቻለሁ!” በአውራጃ ስብሰባው ወቅት በአንዳንድ ሥራዎች ላይ በመካፈል ልባችንን ማስፋታችንና ሌሎች ወዳጆችን ማፍራታችን ከፍተኛ ደስታ ያስገኝልናል። (2 ቆሮ. 6:12, 13) ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆነህ አገልግለህ የማታውቅ ከሆነ የጉባኤህን ሽማግሌዎች አነጋግራቸው፤ እርዳታ ማበርከት የምትችልበትን መንገድ ሊጠቁሙህ ይችላሉ።
9. ሰዎች በአውራጃ ስብሰባው ላይ እንዲገኙ ለመጋበዝ ምን ዝግጅት ተደርጓል?
9 ሌሎች እውነትን የመስማት አጋጣሚ እንዲያገኙ ወደ ስብሰባው መጋበዝ፦ ከዚህ ቀደም እናደርግ እንደነበረው የአውራጃ ስብሰባችን ከመጀመሩ ሦስት ሳምንት ቀደም ብለን ሌሎች በስብሰባው ላይ እንዲገኙ ለመጋበዝ በሚደረገው ዘመቻ ላይ እንካፈላለን። ጉባኤዎች የመጋበዣ ወረቀቱን በማሰራጨት በርካታ ክልሎችን ለመሸፈን ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። (“መጋበዣ ወረቀቱን ማሰራጨት የምንችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) የተረፋችሁን የመጋበዣ ወረቀት ወደ ስብሰባው ይዛችሁ መምጣት ይኖርባችኋል። እንዲህ ማድረጋችሁ ሌሎች ወንድሞች ስብሰባው በሚደረግበት ከተማ ውስጥ መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት ለመስጠት ያስችላቸዋል።
10. በየዓመቱ የምናሰራጫቸው መጋበዣዎች ውጤት እንደሚያስገኙ የሚያሳዩ ተሞክሮዎችን ተናገር።
10 እንዲህ ላሉ ዓመታዊ ዘመቻዎች ምላሽ የሚሰጡ ሰዎች አሉ? በአንድ የአውራጃ ስብሰባ ላይ በአስተናጋጅነት የሚያገለግል አንድ ወንድም ወደ ስብሰባው ለመጡ ባልና ሚስት የሚቀመጡበት ቦታ አሳያቸው። እነሱም መጋበዣ ወረቀት እንደደረሳቸውና “ስብሰባው ማራኪ ሊሆን እንደሚችል” ተሰምቷቸው እንደመጡ ነገሩት። እነዚህ ሰዎች በስብሰባው ላይ የተገኙት በመኪና ከ300 ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዘው ነበር! በሌላ ወቅት ደግሞ አንዲት ሴት ከቤት ወደ ቤት ስታገለግል ላገኘችው ሰው መጋበዣውን ሰጠችው፤ ሰውየው ስለ ስብሰባው የማወቅ ጉጉት ስላደረበት ቆም ብላ በመጋበዣው ላይ ያለውን ሐሳብ አወያየችው። ከተወሰኑ ቀናት በኋላ በተደረገው አውራጃ ስብሰባ ላይ ይህች እህት ሰውየውን ከአንድ ጓደኛው ጋር አየችው፤ ሁለቱም አዲስ ከወጡት ጽሑፎች መካከል አንዱን ይዘው ነበር!
11. በየዓመቱ በምናደርጋቸው የአውራጃ ስብሰባዎቻችን ላይ መገኘታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
11 እስራኤላውያን በየዓመቱ የሚያከብሯቸው በዓላት የይሖዋ ፍቅራዊ ዝግጅት የነበሩ ሲሆን ሕዝቡ ‘በፍጹምና በእውነተኛ ልብ’ ይሖዋን እንዲያመልክ አስችለዋል። (ኢያሱ 24:14 የ1954 ትርጉም) በተመሳሳይም በየዓመቱ የምናደርገው የአውራጃ ስብሰባ “በእውነት ውስጥ [መመላለሳችንን]” እንድንቀጥል የሚያግዘን ከመሆኑም በላይ የአምልኳችን ዋነኛ ክፍል ነው። (3 ዮሐ. 3) እውነት ወዳድ የሆኑ ሁሉ በስብሰባው ላይ ለመገኘትና ከስብሰባው ሙሉ ጥቅም ለማግኘት የሚያደርጉትን ጥረት ይሖዋ እንዲባርከው ምኞታችን ነው!
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
የአውራጃ ስብሰባው በሚካሄድበት ከተማ የምናሳየው መልካም ምግባር እውነትን ያስውባል
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
የአውራጃ ስብሰባችን ከመጀመሩ ሦስት ሳምንት ቀደም ብለን ሌሎች በስብሰባው ላይ እንዲገኙ ለመጋበዝ በሚደረገው ዘመቻ ላይ እንካፈላለን
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የ2012 የአውራጃ ስብሰባ ማሳሰቢያዎች
◼ የስብሰባው ሰዓት፦ ፕሮግራሙ በሦስቱም ቀናት ከጠዋቱ 3:20 ላይ ይጀምራል። በመሰብሰቢያ ቦታው ወንበር መያዝ የሚቻለው ከጠዋቱ 2:00 ሰዓት ጀምሮ ነው። የመክፈቻው ሙዚቃ ሊጀምር እንደሆነ የሚገልጽ ማስታወቂያ ሲነገር ሁላችንም ቦታ ቦታችንን መያዝ ይኖርብናል፤ ይህም ፕሮግራሙን ክብር ባለው መንገድ ለማስጀመር ያስችላል። ፕሮግራሙ ዓርብና ቅዳሜ 10:55 እንዲሁም እሁድ 9:40 ላይ ይደመደማል።
◼ መኪና ማቆሚያ፦ አብዛኛውን ጊዜ ያለው የመኪና ማቆሚያ ውስን በመሆኑ መኪና ካለው ሰው ጋር በመሄድ የመኪናዎቹን ቁጥር መቀነስ እንችላለን። በተጨማሪም ጉባኤያችሁ በተመደበበት የአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት እባካችሁ ጥረት አድርጉ።
◼ መቀመጫ መያዝ፦ መቀመጫ መያዝ የሚቻለው ከእናንተ ጋር በመኪና ለሚመጡ፣ በአንድ ቤት አብረዋችሁ ለሚኖሩ እንዲሁም ከእናንተ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ላይ ለሚገኙ ሰዎች ብቻ መሆኑን አስታውሱ።—1 ቆሮ. 13:5
◼ ምሳ፦ በእረፍት ሰዓት ምግብ ፍለጋ ከስብሰባው ቦታ ወጥታችሁ ከመሄድ ይልቅ እባካችሁ ምሳ ይዛችሁ ኑ። በመቀመጫችሁ ሥር ሊቀመጥ የሚችል መጠነኛ ዕቃ መጠቀም ይቻላል። ትላልቅ ዕቃዎችንና ጠርሙስ ነክ ዕቃዎችን ወደ ስብሰባው ቦታ ማምጣት አይፈቀድም።
◼ መዋጮ፦ በመንግሥት አዳራሽም ሆነ በአውራጃ ስብሰባ ላይ ለዓለም አቀፉ ሥራ በፈቃደኝነት መዋጮ በማድረግ ለስብሰባው የተሰማንን አድናቆት መግለጽ እንችላለን። በአውራጃ ስብሰባው ላይ መዋጮ የሚደረጉ ቼኮች ሁሉ ለ“የይሖዋ ምሥክሮች” የሚከፈሉ መሆናቸው መገለጽ አለበት።
◼ አደጋዎችና ድንገተኛ ሕመም፦ አንድ ሰው በስብሰባው ቦታ ላይ ድንገተኛ ሕመም ካጋጠመው የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ መስጫ ክፍል የሚገኝበትን ቦታ እንዲጠቁማችሁ በቅርብ ያለውን አስተናጋጅ አነጋግሩ።
◼ መድኃኒቶች፦ በሐኪም ትእዛዝ መድኃኒት እየወሰዳችሁ ከሆነ እንዲህ ዓይነት መድኃኒቶች በስብሰባው ቦታ ስለማይኖሩ እባካችሁ የምትወስዷቸውን መድኃኒቶች መያዛችሁን አረጋግጡ።
◼ ጫማ፦ በየዓመቱ ከጫማ ጋር በተያያዘ ብዙ ጉዳት ይደርሳል። በመሆኑም በደረጃዎችና እነዚህ በመሳሰሉ ቦታዎች ስትራመዱ ጉዳት እንዳይደርስባችሁ ልከኛና ምቹ የሆነ ጫማ እንድታደርጉ እናበረታታችኋለን።
◼ የመስማት ችግር ያለባቸው፦ ስብሰባው በአንዳንድ ቦታዎች በኤፍኤም የሬዲዮ ሞገድ ይተላለፋል። በዚህ ዝግጅት መጠቀም እንድትችሉ በባትሪ የሚሠራ የኤፍኤም መቀበያና የጆሮ ማዳመጫ ይዛችሁ መምጣት ያስፈልጋችኋል።
◼ የሕፃናት ጋሪዎችና የመናፈሻ ወንበሮች፦ የሕፃናት ጋሪዎችንና የመናፈሻ ወንበሮችን ወደ ስብሰባው ቦታ ይዞ መምጣት ተገቢ አይደለም። ይሁን እንጂ ከወላጆች አጠገብ ባለ ወንበር ላይ ሊታሰሩ የሚችሉ ለልጆች ደህንነት ተብለው የሚዘጋጁ ወንበሮችን (child-safety seats) ይዞ መምጣት ይቻላል።
◼ ምግብ ቤቶች፦ ምግብ ቤት በምትመገቡበት ጊዜ መልካም ምግባር በማሳየት የይሖዋን ስም አስከብሩ። በአካባቢው የተለመደ ከሆነ ለአስተናጋጆች ጉርሻ ወይም ቲፕ ስጡ።
◼ ሆቴሎች፦ የምትችሉ ከሆነ ሆቴል ውስጥ ማረፋችሁ የተሻለ ነው።
(1) እባካችሁ ከሚያስፈልጋችሁ በላይ ብዙ ክፍሎችን አትያዙ፤ እንዲሁም ሆቴሉ ከሚፈቅደው በላይ ሰዎችን በክፍላችሁ አታሳድሩ።
(2) ከአቅም በላይ የሆነ ነገር ካላጋጠማችሁ በስተቀር የያዛችሁትን ሆቴል አትሰርዙ፤ ይሁንና መሰረዝ ካስፈጋችሁ በአፋጣኝ ለሆቴሉ አሳውቁ።—ማቴ. 5:37
(3) በክፍላችሁ ውስጥ ምግብ ማብሰል የማይፈቀድ ከሆነ እንደዚያ አታድርጉ።
(4) ከሆቴሉ ሠራተኞች ጋር ባላችሁ ግንኙነት የመንፈስ ፍሬን አንጸባርቁ። ሠራተኞቹ ብዙ ሰዎችን ስለሚያስተናግዱ ደግነትና ትዕግሥት ብናሳያቸው እንዲሁም ምክንያታዊ ብንሆን ደስ ይላቸዋል።
(5) ወላጆች ልጆቻቸው በሆቴሉ ውስጥ የሚያደርጉትን ነገር ሊከታተሉ ይገባል፤ ይህ ደግሞ ልጆቻቸው በመዋኛ ቦታ፣ በእንግዳ መቆያው አካባቢ፣ በጂምናዝየም እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች የሚያሳዩትን ባሕርይ ይጨምራል።
◼ መንግሥት አዳራሾችን መጠቀም፦ የመንግሥት አዳራሾችን ለማደሪያነት ባትጠቀሙባቸው እንመርጣለን። መንግሥት አዳራሾችን ለዚህ ዓላማ መጠቀም የግድ ከሆነ ግን ሁሉም ሰው የመንግሥት አዳራሹን ምንጊዜም ንጹሕና ሥርዓታማ አድርጎ የመያዝ ኃላፊነት እንዳለበት ሊሰማው ይገባል። መተኛዎቹ በሥርዓት ተጣጥፈው መቀመጥ ይኖርባቸዋል፤ የፈሰሰ ነገር ካለ ወዲያውኑ መወልወል ይገባዋል፤ እንዲሁም ወረቀቶችና ሌሎች ቆሻሻዎች በቅርጫት ወይም በሌላ ነገር ውስጥ መሰብሰብ ይኖርባቸዋል።
◼ እባካችሁ ተከታትላችሁ እርዱት (S-43) የተባለው ቅጽ፦ እባካችሁ ተከታትላችሁ እርዱት የሚለው ቅጽ በስብሰባው ላይ መደበኛ ባልሆነ መንገድ መሥክረንለት ፍላጎት ያሳየን ሰው በሚመለከት መረጃ ለመስጠት ያገለግላል። ቅጹን ከሞላችሁ በኋላ ለአውራጃ ስብሰባው የጽሑፍ ክፍል አሊያም ወደ ጉባኤያችሁ ስትመለሱ ለጉባኤው ጸሐፊ ልትሰጡት ትችላላችሁ።—የግንቦት 2011 የመንግሥት አገልግሎታችን ገጽ 3ን ተመልከት።
◼ ጽዳት፦ የንጽሕና ክፍል የመሰብሰቢያ ቦታው በፕሮግራም እንዲጸዳ ዝግጅት የሚያደርግ ቢሆንም ሁላችንም ይሖዋ ከሕዝቦቹ የሚፈልገውን የንጽሕና መሥፈርት ለመጠበቅ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት እንችላለን። በመሆኑም በአዳራሹ ወለል ላይም ይሁን በግቢው ውስጥ ወረቀት ወይም ሌላ ቆሻሻ መጣል ተገቢ አይደለም። ቆሻሻዎች ለዚያ ዓላማ በተዘጋጁ ቅርጫቶች ውስጥ መጣል ይኖርባቸዋል። እንዲህ የሚደረግ ከሆነ የአውራጃ ስብሰባው የሚካሄድበት ቦታ በፕሮግራሙ ወቅትም ሆነ በእረፍት ሰዓት የተዝረከረከ አይሆንም። በተጨማሪም ከተቀመጥንበት ቦታ ስንነሳ የወደቀ ነገር ካለ ለማንሳት ዞር ዞር ብለን አካባቢውን መመልከታችን የሚያስመሰግን ነው።
◼ የፈቃደኛ አገልግሎት፦ ፈቃደኛ ሠራተኞች ሆነን አስፈላጊ ሥራዎች የምናከናውን ከሆነ በአውራጃ ስብሰባው ላይ የምናገኘው ደስታ እጥፍ ድርብ ይሆናል። (ሥራ 20:35) ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆነው ማገልገል የሚፈልጉ ሁሉ በስብሰባው ቦታ ለሚገኘው የፈቃደኛ አገልግሎት ክፍል ማሳወቅ ይኖርባቸዋል። ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች በወላጅ አሊያም ወላጅ በሚመድብላቸው ሞግዚት ወይም ሌላ ትልቅ ሰው ሥር በመሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መጋበዣ ወረቀቱን ማሰራጨት የምንችለው እንዴት ነው?
ክልላችንን መሸፈን እንድንችል መግቢያችንን አጭር ማድረግ ያስፈልገናል። እንዲህ ማለት እንችላለን፦ “ጤና ይስጥልኝ። ይህን የመጋበዣ ወረቀት በዓለም ዙሪያ እያሰራጨን ነው። ይህ የእርስዎ ቅጂ ነው። ተጨማሪ ማብራሪያዎችን በመጋበዣ ወረቀቱ ላይ ያገኛሉ።” ስትናገር ግለት ይኑርህ። በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት መጋበዣውን ስታሰራጭ ሁኔታው የሚያመች ከሆነ መጽሔቶችንም አብረህ ማበርከት ይኖርብሃል።