የአውራጃ ስብሰባ ማሳሰቢያዎች
ጥምቀት፦ ቅዳሜ ጠዋት ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት የጥምቀት እጩዎች በተመደበላቸው ቦታ መቀመጥ አለባቸው። አንዳንዶች የሚለብሷቸው ልብሶች ለሁኔታው ክብርና ክብደት የማይሰጡ እንደሆኑ ተስተውሏል። እያንዳንዱ ተጠማቂ እንደ ፖሊስተር ያለ ሲረጥብ ሰውነትን የሚያሳይ ልብስ ሳይሆን ልከኛ ልብስና ፎጣ ይዞ መምጣት አለበት። ተናጋሪው የጥምቀት ንግግርና ጸሎት ካቀረበ በኋላ የመድረኩ ሊቀመንበር ለጥምቀት እጩዎቹ አጠር ያለ መመሪያ ይሰጥና መዝሙር እንዲዘመር ይጋብዛል። የመጨረሻው ስንኝ ከተዘመረ በኋላ አስተናጋጆች እጩዎችን ጥምቀቱ ወደሚከናወንበት ቦታ ይወስዷቸዋል። ጥምቀት አንድ ሰው ራሱን መወሰኑን የሚያሳይበት ምልክት ከመሆኑም በተጨማሪ በግለሰቡና በይሖዋ መካከል ብቻ ያለ የግል ጉዳይ ስለሆነ ለፎቶግራፍ ለማመቻቸት ሲባል መዘግየት አይገባም።
ደረት ላይ የሚለጠፉ ካርዶች፦ እባካችሁ በስብሰባው ላይ እንዲሁም ወደ ስብሰባው ስትሄዱና ስትመለሱ ለ1996 የተዘጋጀውን ባጅ ደረታችሁ ላይ ለጥፉ። እንዲህ ማድረጋችን ብዙውን ጊዜ በጉዞ ላይ ጥሩ ምሥክርነት ለመስጠት ያስችለናል። ደረት ላይ የሚለጠፉት ካርዶችና መያዣቸው በስብሰባው ላይ ስለማይገኙ በጉባኤያችሁ በኩል ማግኘት ይኖርባችኋል። ደረት ላይ የሚለጠፉትን ካርዶች ለእናንተና ለቤተሰቦቻችሁ ለመጠየቅ ስብሰባው የሚጀመርበት ቀን ሊደርስ ጥቂት ቀናት እስኪቀሩ ድረስ አትጠብቁ። የወቅቱን በቅድሚያ የተሰጠ የሕክምና መመሪያ/የሕክምና ባለሙያዎችን ከኃላፊነት ነፃ የሚያደርገውን ሰነዳችሁን መያዝ አትርሱ።
መስተንግዶ፦ የጉባኤ ጸሐፊዎች የማረፊያ ቦታ ጥያቄዎችን በፍጥነት ወደ ትክክለኛው የስብሰባ አድራሻ መላካቸውን ማረጋገጥ አለባቸው። በዚህ መንገድ የተያዘላችሁን ማረፊያ መጠቀም የማትችሉበት ሁኔታ ካጋጠማችሁ ክፍሉን ሌላ ሰው እንዲጠቀምበት ለሆቴሉ ወይም ለቤቱ ባለቤት እንዲሁም ለስብሰባው መስተንግዶ ክፍል ወዲያውኑ ማሳወቅ ይኖርባችኋል።
መተላለፊያዎችን ክፍት ማድረግ፦ የሥርዓታማነት፣ የአክብሮትና የአርቆ አሳቢነት መግለጫ እንደመሆኑ መጠን መውጫዎች፣ ደረጃዎችና መተላለፊያዎች እንዳይዘጉ ጥረት ማድረግ አለብን። አስተናጋጆች የስታዲየሙን ደንቦች በማክበር ለመተላለፊያነት በሚያገለግሉ ደረጃዎች ላይ ማንንም ሰው እንዳያስቀምጡ መመሪያ ይሰጣቸዋል።
የፈቃደኝነት አገልግሎት፦ የምግብ አገልግሎት መስጠት ስላቆመ ከዚህ በፊት በዚህ ክፍል ይሠሩ የነበሩ ብዙዎች በሌላ ቦታ በፈቃደኝነት ማገልገል ይችላሉ። በስብሰባው ላይ ካሉት የሥራ ክፍሎች በአንዱ ውስጥ ለምሳሌ በጽዳት ለማገልገል ጊዜ ልትመድቡ ትችላላችሁን? ለጥቂት ሰዓታት ብቻ ቢሆንም እንኳ ወንድሞቻችንን ማገልገሉ ትልቅ እገዛ ሊያበረክት ይችላል፤ ከፍተኛ እርካታም ያመጣል። እርዳታ ማበርከት የምትችሉ ከሆነ በስብሰባው ቦታ ለሚገኘው ለፈቃደኛ አገልግሎት ማስተባበሪያ ክፍል አስታውቁ። ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች ከወላጆቻቸው ወይም ኃላፊነት ሊወስድ ከሚችል ሌላ ትልቅ ሰው ጋር በመሆን አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ።
የማስጠንቀቂያ ምክር፦ ችግር ሊፈጥሩ የሚችሉትን ነገሮች ንቁ ሆኖ በመጠባበቅ ከጥንቃቄ ጉድለት የሚመጣ ችግሮችን ማስወገድ እንችላለን። ብዙዉን ጊዜ ሌቦችና አንዳንድ ይሉኝታ የሌላቸው ሰዎች ከአካባቢያቸው ርቀው በመጡ ሰዎች ላይ ዝርፊያ ይፈጽማሉ። የመኪናዎቻችሁ በሮች ሁልጊዜ መቆለፋቸውንና አንድ ሰው መኪናውን ሰብሮ እንዲዘርፍ የሚጋብዘው ከውጭ ሊታይ የሚችል ነገር ትታችሁ አለመሄዳችሁን አረጋግጡ። ሌቦችና ኪስ አውላቂዎች በብዛት በተሰባሰቡ ሰዎች ላይ ትኩረታቸውን ያነጣጥራሉ። ውድ ዋጋ ያላቸውን ማናቸውንም ነገሮች መቀመጫችሁ ላይ ትታችሁ መሄዱ ጥበብ አይሆንም። ዙሪያችሁ ያለው ሁሉ ክርስቲያን ስለመሆኑ እርግጠኛ መሆን አትችሉም። ሌሎች ለምን እንዲፈተኑ እናደርጋለን? ከውጭ የገቡ ሰዎች ልጆችን አባብለው ለመውሰድ ሙከራ እንዳደረጉ የሚገልጹ ሪፖርቶች ደርሰውናል። ልጆቻችሁን በማንኛውም ጊዜ ከዓይናችሁ አታርቋቸው።