“ደስተኛ አወዳሾች” የ1995 የአውራጃ ስብሰባ
1 ደስተኛ የምንሆንባቸው ምን ያህል ምክንያቶች አሉን? አብዛኞቻችን ሁሉንም መዘርዘር አንችልም። የምንኖረው ሰዎች ግራ በተጋቡበትና ምን ማድረግ እንዳለባቸው በማያውቁበት ዓለም ውስጥ ቢሆንም እንኳ ደስተኛ የምንሆንባቸው በጣም ብዙ ምክንያቶች አሉን። ስለዚህ “ደስተኛ አወዳሾች” ለ1995 የአውራጃ ስብሰባዎች የተሰጠ የሚያበረታታ አጠቃላይ መልእክት ነው።
2 እውነትን ስላስተማረን ይሖዋን እናወድሰዋለን። (ኢሳ. 54:13፤ ዮሐ. 8:32) ከዚህም በተጨማሪ ደህንነትንና ደስታን በመፈለግ ላይ ላሉ ሰዎች ሁሉ እውነትን በደስታ እንነግራቸዋለን። (ሕዝ. 9:4፤ ሥራ 20:35) ክርስቲያናዊ ወንድማማችነታችንም ያስደስተናል። አፍቃሪ መንፈሳዊ ቤተሰብ እርካታና ደስታ ያመጣል። እነዚህ ይሖዋን ለማወደስ የሚገፋፋንን ደስታ ካስገኙልን ምክንያቶች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። በስብሰባው ላይ የሚቀርቡት ንግግሮችና ሠርቶ ማሳያዎች በእነዚህ አስጨናቂ የመጨረሻ ቀናት ውስጥ የምንደሰትባቸውን ተጨማሪ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያቶች እንድናጤን ያደርጉናል።
3 የሦስት ቀናት ስብሰባ፦ በሦስቱም የስብሰባ ቀናት ላይ ለመገኘት አሠሪህ ፈቃድ እንዲሰጥህ ቅድመ ዝግጅት አድርገሃልን? አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ወላጆች በትምህርት ወቅት በስብሰባው ላይ የሚካፈሉ ልጆች ካሏቸው ከሃይማኖታዊ አምልኮታቸው ዐብይ ክፍል አንዱ በሆነው በዚህ ፕሮግራም ላይ ለመገኘት ልጆቻቸው ዐርብ ዕለት በትምህርት ገበታቸው ላይ እንደማይኖሩ ለአስተማሪዎቻቸው በአክብሮት ማሳወቅ ይኖርባቸዋል።
4 ፕሮግራሙ ዐርብ ከጠዋቱ 3:40 ላይ ይጀምርና እሁድ ከሰዓት በኋላ 9:50 ገደማ ይደመደማል። ቅዳሜና እሑድ ፕሮግራሙ ከጠዋቱ 3:30 ላይ ይጀመራል። ከጠዋቱ 2:00 በሮች ይከፈታሉ። ከዚህ ቀደም ብለው እንዲገቡ የሚፈቀድላቸው የሥራ ኃላፊነት ያለባቸው ብቻ ናቸው።
5 በስብሰባው ላይ ትገኛለህን?፦ ስብሰባው በሚደረግባቸው በሦስቱም ቀናት ላይ እንድንገኝ ጥብቅ ማሳሰቢያ ተሰጥቶናል። ይህ ማሳሰቢያ የተሰጠው ለምንድን ነው? ይሖዋ እዚያ እንድንገኝ ስለሚፈልግ ነው። በዛሬው ጊዜ እምነታችንና መንፈሳዊ ጤንነታችን ኃይለኛ ጥቃት እየደረሰበት ነው። ጳውሎስ በይሁዳ የሚገኙ ክርስቲያኖችን “መሰብሰባችንን አንተው” በማለት የመከራቸው ከባድ ተጽዕኖ እየደረሰባቸው በነበረበት ጊዜ ነው። (ዕብ. 3:12, 13፤ 10:25) የፊልጵስዩስ ሰዎች “በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል” ይኖሩ ነበር። ቢሆንም ‘በዓለም ውስጥ ብርሃን አብሪዎች’ ነበሩ። (ፊልጵ. 2:14, 15) እነዚህ የመጀመሪያ መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ከሌሎች የተለዩ የሆኑት ለምን ነበር? ‘ለፍቅርና ለመልካም ሥራ ለመነቃቃት’ እንዲሰበሰቡ የተሰጣቸውን የመንፈስ ቅዱስ አመራር በታዛዥነት ስለተከተሉ ነው።— ዕብ. 10:24
6 ዓለም ከዚህ ተቃራኒ የሆነ ተጽዕኖ ያሳድርብናል። ከወንድሞቻችን ጋር ተገናኝተን ይሖዋን ለማወደስ ያለንን ፍላጎት ያዳክምብናል። ራሳችንን ለይሖዋ መንፈስ እንድናስገዛና በሦስቱም የስብሰባ ቀናት እንድንገኝ ተጋብዘናል። ከመላው ቤተሰባችን ጋር ለመገኘት ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል? ፍቅራችንንና እምነታችንን ዘወትር ማጠናከር ያስፈልገናል። ይሖዋ በዚህ ረገድ እኛን ለመርዳት ትልልቅ ዓመታዊ ስብሰባዎችን አዘጋጅቷል።
7 ወደ ቤትህ ውድ ሀብት ይዘህ ተመለስ፦ ከስብሰባው ይበልጥ ተጠቃሚ መሆን የምትችለው እንዴት ነው? የዚህ መልስ ባጭሩ “ሐሳብን ሰብሰብ አድርጎ መከታተል” ነው። ዛሬ ባለው ልቡ የተሰቀለና የተዋከበ ኅብረተሰብ ውስጥ እንዲህ ማድረጉ ቀላል አይደለም። በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች በትኩረት መከታተል አስቸጋሪ ሊሆንባቸው ይችላል፤ ሆኖም ይህ ሁኔታ ሁላችንም በአውራጃ ስብሰባ ላይ ስንገኝ የሚያጋጥመን ፈታኝ ችግር ነው። አስቀድመን ካሰብንበት ሐሳብን ሰብሰብ አድርጎ በትኩረት መከታተል ቀላል ይሆንልናል። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘የስብሰባው ጭብጥ ምንድን ነው?’ በጭብጡ ላይ አሰላስል! ‘ወደ ስብሰባው የምሄደው ለምንድን ነው? በሦስቱ ቀናት ውስጥ የማከናውናቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? ስብሰባው በሚደረግባቸው ቀናት ያሉትን ምሽቶች ለመዝናኛ አውላቸዋለሁ ወይስ እረፍት ለማድረግና የስብሰባውን ጎላ ጎላ ያሉ ነጥቦች ለመከለስ በቂ ጊዜ መድቤአለሁ?’
8 በ24–108 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣው “ታሰላስላለህ ወይስ የቀን ህልም ታልማለህ?” የሚለው ርዕስ ከስብሰባዎች የተሻለ ጥቅም እንዴት እንደምናገኝ ብዙ ምክር ከሰጠ በኋላ “ከሁሉ አስፈላጊ የሆነው ግን አእምሮን መገሰጹ ነው” በማለት ይደመድማል። ብዙውን ጊዜ አንድ ተናጋሪ ንግግሩን ሲጀምር ንቁዎች ነን፤ ቢሆንም የንግግሩን የተወሰነ ክፍል ካዳመጥን በኋላ አእምሯችን ቀስ እያለ ወደ ሌላ ሐሳብ እንዲሄድ እንፈቅድለታለን። ይህ እንዳይከሰት ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
9 ባለፉት ጊዜያት የተሰጡ ምክሮችን መድገሙ ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም እነዚህ ምክሮች ውጤታማ ናቸው። በተቻለ መጠን በእያንዳንዱ ምሽት በቂ እረፍት ለማግኘት ጥረት አድርግ። አጫጭር ማስታወሻ መውሰድ በትኩረት ለመከታተል እንደሚያግዝ ተረጋግጧል። ብዙ ነገር ለመጻፍ የምትሞክር ከሆነ አንዳንድ ጠቃሚ ነጥቦች ሙሉ በሙሉ ሊያመልጡህ ይችላሉ። የፕሮግራሙን አስተዋጽኦ ለአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ወይም ለማያምኑ የቤተሰብ አባላት መደበኛ ባልሆነ መንገድ ስትመሠክር እንደምታካፍላቸው አድርገህ ማስታወሻ እንድትወስድ ሐሳብ እናቀርብልሃለን። ማስታወሻ ስትወስድና የሰማኸውን ለሌሎች ስታካፍል ትምህርቱን ቶሎ አትረሳውም። ሐሳብን በንግግር፣ በጽሑፍ ወይም በሌላ መንገድ መግለጽ ነገሩ ይበልጥ ከአእምሯችን እንዳይጠፋ ያደርጋል።
10 ለስብሰባው የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለመከራየት ከፍተኛ ወጪ ይወጣል። እነዚህ ወጪዎች የሚሸፈኑት እንዴት ነው? በጥሬ ገንዘብ ወይም “ለይሖዋ ምሥክሮች” በሚከፈል ቼክ አማካኝነት በፈቃደኝነት በምናደርገው መዋጮዎች ነው። ይህም የሚደረገው ከመዝሙር 96:8 እና ከ2 ዜና መዋዕል 31:12 ጋር በመስማማት ነው።
11 ደስተኛ አወዳሾች አምላካዊ ጠባይ በማሳየት ይሖዋን ያስከብራሉ፦ ባለፈው ዓመት ለስብሰባው ተካፋዮች የተለያዩ አገልግሎት በሚሰጡ ድርጅቶች ውስጥ ከሚሠሩ ሠራተኞችና ከአጠቃላዩ ሕዝብ ጠባያችንን በተመለከተ የሚያበረታቱና ገንቢ የሆኑ ሐሳቦች ደርሶናል። አንድ የሆቴል አስተዳዳሪ እንዲህ በማለት ተናግረዋል:- “የይሖዋ ምሥክሮችን ማስተናገድ ምንጊዜም አስደሳች ነው። ምክንያቱም ታጋሽና ተባባሪዎች ከመሆናቸውም በተጨማሪ ልጆቻቸውን ይቆጣጠራሉ።” ለአንዳንዶች ማሳሰቢያ መስጠት ተገቢ ይመስላል። አንዳንድ ጊዜ ሆቴሎች ውስጥ ወይም መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ያረፉ ወንድሞች ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ሲስቁና ሲያወኩ እንደሚያመሹ ለማወቅ ተችሏል። ይህ ሌሎቹን እንግዶች ይረብሻል። አንዳንድ ልጆች በኮሪደሮች ውስጥ ወዲያና ወዲህ ይሯሯጣሉ፣ ከአንዱ ክፍል ወደ ሌላኛው ሲሄዱ በሮችን በኃይል ይዘጋሉ እንዲሁም ቤቱ ውስጥ ሆነው ድምፃቸውን በጣም ከፍ አድርገው ያወራሉ። ለሌሎች አሳቢነት ማሳየትን እንዳንዘነጋ አንዳችን ሌላውን እናሳስብ።
12 አለባበስህና የፀጉር አበጣጠርህ ስለ አንተ ይናገራል፦ በ1 ሳሙኤል 16:7 ላይ “ሰው ፊትን ያያል፣ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል” የሚል ማሳሰቢያ ተሰጥቶናል። ስለዚህ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ማንነታችንን የሚገመግሙት በውጪያዊ አቋማችን ነው። በተለይ አምልኮታችንን ለማከናወንና ለክርስቲያናዊ ሕይወት የሚሆን መመሪያ ለማግኘት በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ ሰዎች አለባበሳችንና የፀጉር አበጣጠራችንን ይበልጥ ይመለከቱታል። ተማሪ ከሆንክ ወይም ሥራህ ዓለማዊ ፋሽኖችን ከሚከተሉ ሰዎች ጋር የሚያቀራርብህ ከሆነ በልከኛ አለባበስ ረገድ ክርስቲያናዊ የአቋም ደረጃዎችን መጠበቅ ፈታኝ ሊሆንብህ ይችላል።
13 የአለባበስና የፀጉር አበጣጠር ሁኔታ ከአገር ወደ አገር ይለያያል። ክርስቲያኖች ልከኛና ሥርዓታማ አለባበስ እንዲኖራቸው ይጠበቅባቸዋል። ይህንን መወሰን ያለበት ማን ነው? ወላጆች በአሥራዎቹ ዕድሜዎች የሚገኙ ልጆቻቸው በትምህርት ቤት እንዳሉት ዓለማዊ ወጣቶች እንደማይለብሱ እርግጠኛ መሆን አለባቸው። በዚህ ጥንቃቄ በሚጠይቅ ነገር ላይ ትክክለኛ ውሳኔ ለማድረግ የሚያስችሉ ጠቃሚ መመሪያዎች ቀርበውልናል። በየካቲት 8, 1987 የእንግሊዝኛ ንቁ! መጽሔት ላይ የወጣውን “ስለ ልብስ ያለህ አመለካከት ምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ እንድትከልሱ እናበረታታችኋለን።
14 አብዛኞቹ ወንድሞችና እህቶች በስብሰባ ቦታ ላይ የሚያስከብር ልከኛ ልብስ ይለብሳሉ። ቢሆንም አልፎ አልፎ አንዳንዶች ለአምልኮታዊ ሥነ ሥርዓት የማይስማማ ጅንስ ወይም ዓለማዊ መፈክሮች የተጻፉባቸው ቲ— ሸርቶች የመሳሰሉ በእንዲህ ዓይነቱ ስብሰባ ላይ መለበስ የማይገባቸውን ልብሶች ለብሰው ይመጣሉ። ሌሎች ደግሞ ልብሶቻቸው ያልታጠቡና ያልተተኮሱ ናቸው። ሽማግሌዎች አንዳንዶች እንዲህ ዓይነት አለባበስ እንዳላቸው ካስተዋሉ ይህ ዓይነቱ አለባበስ በተለይ ደግሞ ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባ ስንሄድ ተገቢ እንዳልሆነ ከስብሰባው በፊት ደግነት የተሞላበት ምክር መስጠቱ ተገቢ ይሆናል። እባካችሁ ጠባይንና አለባበስን በተመለከተ ከላይ የተዘረዙትን መመሪያዎች ስብሰባው ላይ ከሚገኙ እድገት እያደረጉ ካሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችሁ ጋር ተወያዩባቸው፤ በምትወያዩበት ጊዜ ሁኔታቸውን ግምት ውስጥ አስገቡ።
15 የምስልና የድምፅ መቅረጫ መሣሪያዎች፦ የምስልና የድምፅ መቅረጫ መሣሪያዎችን በተመለከተ ደግነት የተሞላበት ማሳሰቢያዎችን ማቅረቡ ተገቢ ነው። እባካችሁ በካሜራ ወይም በማንኛውም የመቅረጫ መሣሪያዎች ለመጠቀም እቅድ ካላችሁ በአካባቢያችሁ ላሉት ሰዎች አሳቢነት ማሳየታችሁን አትርሱ። በፕሮግራሙ ወቅት እየተዟዟራችሁ ብትቀርጹ፣ ሌላው ቀርቶ መቀመጫችሁ ላይ ሆናችሁ እንኳ ፕሮግራሙን ብትቀርጹ የሌሎችን ሐሳብ ሊከፋፍል ይችላል። የትኛውም ዓይነት የመቅረጫ መሣሪያ በስብሰባው ቦታ ካለው የኤሌክትሪክ መስመር ወይም የድምፅ ማስተላለፊያ መሣሪያ ጋር እንዲያያዝ የማይፈቀድ ከመሆኑም በላይ ክፍት የተተዉ መተላለፊያዎች ወይም መንገዶች መዘጋት የለባቸውም። ፎቶ ማንሳት ወይም ፕሮግራሙን በቪዲዮ መቅረጽና አለመቅረጽ የግል ውሳኔ ነው። እንደነዚህ ያሉ መሣሪያዎች ሁሉ የሌሎችን ሐሳብ በማይከፋፍል ወይም እናንተን ከፕሮግራሙ የተሻለ ጥቅም ከማግኘት በማያግዳችሁ መንገድ በጥንቃቄ መጠቀም ይገባል። ወደ ቤታችሁ ከተመለሳችሁ በኋላ የቀረጻችሁትን ለማየት የሚያስችል ጊዜ ታገኙ ይሆን? ማስታወሻ መውሰዱ ብቻ በቂ ሆኖ ልታገኙት ትችላላችሁ።
16 መቀመጫዎች፦ እባካችሁ የሚከተለውን ማሳሰቢያ ልብ በሉ:- መቀመጫ መያዝ የሚቻለው ለቤተሰባችሁ አባሎችና በመኪናችሁ አብሮ ለሚጓዝ ሰው ብቻ ነው። በስብሰባው ላይ የምንገኘው የማኅበሩ እንግዶች በመሆን ነው። የመሰብሰቢያው ቦታ ኪራይ የሚከፈለው በፈቃደኝነት በሚለገሱ መዋጮዎች ነው። ገና ለገና እከሌ ሊቀመጥበት ይችላል ብለን መቀመጫ መያዝ አፍቃሪነትና አሳቢነት ይሆናልን?
17 ለስብሰባው የሚያስፈልጋችሁን ምግብ ማዘጋጀት፦ በ1995 ከሚደረጉት የአውራጃ ስብሰባዎችና ከመስከረም 1995 በኋላ በሚደረጉ የወረዳና የልዩ ስብሰባ ቀኖች የሚኖረው የምግብ አቅርቦት በጣም አነስተኛ ይሆናል፤ ወይም ደግሞ ጭራሹኑ አይኖርም። እያንዳንዱ ሰው የራሱን ምግብ ማምጣት ይኖርበታል። በስብሰባው ላይ የሚገኙ ሁሉ የራሳቸውን ምግብ ማምጣት እንደሚኖርባቸው ለመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችሁ መንገር አስፈላጊ ነው። ሰዎች ብዙውን ጊዜ ወደ ሥራ ቦታቸው ሲሄዱ ይዘውት የሚሄዱት ዓይነት ምግብ ይኸውም ለሰውነት የማይከብዱ፣ በቀላሉ የተዘጋጁና ሰውነትን የሚገነቡ እንደ ሳንድዊች፣ ፍራፍሬ፣ የተቀቀለ እንቁላል፣ አምባሻ ወይም ሌሎች የተጋገሩ የምግብ ዓይነቶችን መውሰድ ይቻላል። ማንኛውም ሰው ቡና፣ ሻይ ወይም አምቦ ውኃ ተሰባሪ ባልሆነ ዕቃ ወይም በፔርሙዝ ይዞ መምጣት ይችላል። ነገር ግን ምንም ዓይነት የአልኮል መጠጦች ወይም ተሰባሪ ጠርሙሶች ወደ ስብሰባው ቦታ ማምጣት የለብንም። ስብሰባው በሚደረግበት ቦታ ዕቃዎቹን የማስቀመጫ፣ ሳህኖቹን የማጠቢያና የመመገቢያ ቦታ ችግር ስለሚፈጥር፤ እንዲሁም ከንጽሕና ጉድለት የሚመጡ ችግሮችን ስለሚያስከትል ማታ እቤት ልትመገቡት የምትችሉትን እንጀራ በወጥ ወይም በሥጋ የተሠራ ስጎ ይዛችሁ ባትመጡ ጥሩ ነው። ፕሮግራሙ እየተካሄደ ሳለ መመገብ አይኖርብንም። እንዲህ ማድረጉ እየቀረበ ያለውን መንፈሳዊ ምግብ በአክብሮት አለመመልከት ይሆናል።
18 ለምሳ እረፍት የተመደበው ጊዜ ቀለል ያሉ ምግቦችን ተመግበን ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ቲኦክራሲያዊ ወዳጅነት እንድንመሠርት ታስቦ መሆኑን መዘንጋት የለብንም። የይሖዋ ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን በስብሰባዎች ላይ የሚቀርቡት መንፈሳዊ ምግቦች ከሰብዓዊ ነገሮች ጋር ሲወዳደሩ መጀመሪያ ደረጃ የሚሰጣቸው እንደሆኑ እንገነዘባለን፤ በመሆኑም ከዚህ ጋር የሚስማማ ዕቅድ ማውጣት አለብን።
19 የመጀመሪያው “ደስተኛ አወዳሾች” የአውራጃ ስብሰባ በመስከረም 1995 ይደረጋል። ዝግጅቶችህን አጠናቅቀሃልን? ሦስቱን ቀናት ደስተኛ ጓደኞችና ማራኪ መንፈሳዊ ነገሮች አግኝተህ ለመደሰት ዝግጁ ነህን? ይሖዋን በደስታ ማወደስ የሚቻልበትን መንገድ እያሰላሰልን በዚህ ዓመት ስብሰባ ላይ ከወንድሞችህና ከእህቶችህ ጋር ለመገኘት የምታደርጋቸውን ጥረቶች ይሖዋ እንዲባርክልህ ከልብ እንጸልያለን።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የአውራጃ ስብሰባ ማሳሰቢያዎች
ጥምቀት፦ ቅዳሜ ጠዋት ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት የጥምቀት እጩዎች በተመደበላቸው ቦታ መቀመጥ አለባቸው። አንዳንዶች የሚለብሷቸው ልብሶች ለሁኔታው ክብርና ክብደት የማይሰጡ እንደሆኑ ተስተውሏል። እያንዳንዱ ተጠማቂ ልከኛ ልብስና ፎጣ ይዞ መምጣት አለበት (እንደ ፖሊስተር ያለ ሲረጥብ ሰውነትን የሚያሳይ ልብስ መጠቀም ተገቢ አይሆንም)። ተናጋሪው የጥምቀት ንግግርና ጸሎት ካቀረበ በኋላ የመድረኩ ሊቀመንበር ለጥምቀት እጩዎቹ አጠር ያለ መመሪያ ይሰጥና መዝሙር እንዲዘመር ይጋብዛል። የመጨረሻው ስንኝ ከተዘመረ በኋላ አስተናጋጆች እጩዎችን ጥምቀቱ ወደሚከናወንበት ቦታ ይወስዷቸዋል። ጥምቀት አንድ ሰው ራሱን መወሰኑን የሚያሳይበት ምልክት ከመሆኑም በተጨማሪ በግለሰቡና በይሖዋ መካከል ብቻ ያለ የግል ጉዳይ ስለሆነ ለፎቶግራፍ እያመቻቹ ማጥመቅ አይገባም።
ደረት ላይ የሚለጠፉ ካርዶች፦ እባካችሁ በስብሰባው ላይ እንዲሁም ወደ ስብሰባው ስትሄዱና ስትመለሱ ለ1995 የተዘጋጀውን ባጅ ደረታችሁ ላይ ለጥፉ። እንዲህ ማድረጋችን ብዙውን ጊዜ በጉዞ ላይ ጥሩ ምሥክርነት ለመስጠት ያስችለናል። ደረት ላይ የሚለጠፉት ካርዶችና መያዣቸው በስብሰባው ላይ ስለማይገኙ በጉባኤያችሁ በኩል ማግኘት ይኖርባችኋል። የወቅቱን በቅድሚያ የተሰጠ የሕክምና መመሪያ/የሕክምና ባለሙያዎችን ከኃላፊነት ነፃ የሚያደርገውን ሰነዳችሁን መያዝ አትርሱ። የቤቴል ቤተሰብ አባሎችና አቅኚዎች የመታወቂያ ካርዳቸውን መያዝ አለባቸው።
መስተንግዶ፦ የጉባኤ ጸሐፊዎች የማረፊያ ቦታ ጥያቄዎችን በፍጥነት ወደ ትክክለኛው የስብሰባ አድራሻ መላካቸውን ማረጋገጥ አለባቸው። በዚህ መንገድ የተያዘላችሁን ማረፊያ መጠቀም የማትችሉበት ሁኔታ ካጋጠማችሁ ክፍሉን ሌላ ሰው እንዲጠቀምበት ለሆቴሉ ወይም ለቤቱ ባለቤት እንዲሁም ለስብሰባው መስተንግዶ ክፍል ወዲያውኑ ማሳወቅ ይኖርባችኋል።
መተላለፊያዎችን ክፍት ማድረግ፦ የሥርዓታማነት፣ የአክብሮትና የአርቆ አሳቢነት መግለጫ እንደመሆኑ መጠን መውጫዎች፣ ደረጃዎችና መተላለፊያዎች እንዳይዘጉ ጥረት ማድረግ አለብን። አስተናጋጆች የስታዲየሙን ደንቦች በማክበር ለመተላለፊያነት በሚያገለግሉ ደረጃዎች ላይ ማንንም ሰው እንዳያስቀምጡ መመሪያ ይሰጣቸዋል።
የፈቃደኝነት አገልግሎት፦ በስብሰባው ላይ ካሉት ዲፓርትመንቶች በአንዱ ውስጥ ለማገልገል ጊዜ ልትመድቡ ትችላላችሁን? ለጥቂት ሰዓታት ብቻ ቢሆንም እንኳ ወንድሞቻችንን ማገልገሉ ትልቅ እገዛ ሊያበረክት ይችላል፤ ከፍተኛ እርካታም ያመጣል። እርዳታ ማበርከት የምትችሉ ከሆነ በስብሰባው ቦታ ለሚገኘው ለፈቃደኛ አገልግሎት ማስተባበሪያ ክፍል አስታውቁ። ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች ከወላጆቻቸው ወይም ኃላፊነት ሊወስድ ከሚችል ሌላ ትልቅ ሰው ጋር በመሆን አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ።
የማስጠንቀቂያ ምክር፦ ችግር ሊፈጥሩ የሚችሉትን ነገሮች ንቁ ሆነን በመጠባበቅ ከጥንቃቄ ጉድለት ከሚመጣ ችግር ራሳችንን ማዳን እንችላለን። ብዙውን ጊዜ ሌቦችና አንዳንድ ይሉኝታ የሌላቸው ሰዎች ከአካባቢያቸው ርቀው በመጡ ሰዎች ላይ ዝርፊያ ይፈጽማሉ። የተሽከርካሪዎቻችሁ በሮች ሁልጊዜ መቆለፋቸውንና አንድ ሰው መኪናውን ሰብሮ እንዲዘርፍ የሚጋብዘው ከውጭ ሊታይ የሚችል ነገር ትታችሁ አለመሄዳችሁን አረጋግጡ። ሌቦችና ኪስ አውላቂዎች በተጓዦችና በብዛት በተሰባሰቡ ሰዎች ላይ ትኩረታቸውን ያነጣጥራሉ። ውድ ዋጋ ያላቸውን ማናቸውንም ነገሮች መቀመጫችሁ ላይ ትታችሁ መሄዱ ጥበብ አይሆንም። ዙሪያችሁ ያለው ሁሉ ክርስቲያን ስለመሆኑ እርግጠኛ መሆን አትችሉም። ሌሎች ለምን እንዲፈተኑ እናደርጋለን? ከውጭ የገቡ ሰዎች ልጆችን አባብለው ለመውሰድ ወይም ባጃቸውን ለመስረቅ ሙከራ እንዳደረጉ የሚገልጹ ሪፖርቶች ደርሰውናል። ልጆቻችሁን በማንኛውም ጊዜ ከዓይናችሁ አታርቋቸው።