ይበልጥ እርዳታ ወደሚያስፈልግበት ቦታ ሄደህ ማገልገል ትችላለህ?
1 የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄደህ ስለ ማገልገል አስበህ ታውቃለህ? አንተም “ተሻገርና እርዳን” የሚል ግብዣ ቢቀርብልህ ሐዋርያው ጳውሎስ የሰጠውን ዓይነት ምላሽ ትሰጥ ነበር? (ሥራ 16:9, 10) በብዙ ጉባኤዎችና ቡድኖች ውስጥ በመንፈሳዊ የጎለመሱ ቤተሰቦች፣ የአገልግሎት ክልሉን በመሸፈን የሚያግዙ አቅኚዎች፣ አመራር የሚሰጡ ብቃት ያላቸው ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች ያስፈልጋሉ። የአገልግሎት ክልሉ በአንድ ሰፊ የገጠር ክልል ውስጥ ያሉ ተራርቀው የሚገኙ ትናንሽ ገለልተኛ ከተማዎችን የሚያካትት ሊሆን ይችላል። ከሌሎች የተሻለ ቅርበት አለው የሚባለው የመንግሥት አዳራሽ ራቅ ብሎ የሚገኝ ሊሆን ይችላል። ሥራ እንደልብ አይገኝ ይሆናል። የአየሩ ጠባይ ሁልጊዜ ተስማሚ ላይሆን ይችላል። እንዲህ ያለውን ተፈታታኝ ሁኔታ ለመጋፈጥ ፈቃደኛ ነህ? እንዲህ ያለውን ሁኔታ ተቋቁመህ ስኬታማ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?
2 እምነትና በአምላክ መታመን ያስፈልጋል:- አብራም አምላክ በሰጠው መመሪያ መሠረት ከሚስቱ፣ ከወንድሙ ልጅና አዛውንት ከነበረው አባቱ ከታራ ጋር የተወለደባትን የዑር ከተማ ትቶ በ1, 000 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ወደ ካራን ሄደ። (ዘፍ. 11:31, 32፤ ነህ. 9:7) ታራ ከሞተ በኋላ፣ ይሖዋ የ75 ዓመቱ አብራም ከዘመድ አዝማዶቹ ተለይቶ ከካራን በመውጣት እርሱ ወደሚያሳየው ምድር እንዲሄድ አዘዘው። አብራም፣ ሦራ እና ሎጥ ‘ከካራን ወጡ።’ (ዘፍ. 12:1, 4, 5) እርግጥ ነው፣ አብራም አካባቢ የቀየረው ይበልጥ እርዳታ ወደሚያስፈልግበት ቦታ ሄዶ ለማገልገል አልነበረም። ሆኖም ይህን ማድረግ አንድ ነገር ጠይቆበታል። ምን ይሆን?
3 አብርሃም እንዲህ ዓይነቱን እርምጃ መውሰድ እምነትና በይሖዋ መተማመን ጠይቆበታል። የአስተሳሰብና የአኗኗር ለውጥ ማድረግ ነበረበት። በዘመዶቹ መካከል በመኖር የሚያገኘውን የደህንነት ስሜት መሠዋት ነበረበት። ሆኖም ይሖዋ እርሱንም ሆነ ቤተሰቡን እንደማይተዋቸው ተማምኗል። ዛሬም ብዙዎች በተመሳሳይ መንገድ በይሖዋ እንደሚተማመኑ አሳይተዋል።
4 የአጭር ጊዜ የአገልግሎት ምድብ:- ለየትኛውም ጉባኤ ባልተመደቡ የአገልግሎት ክልሎች ውስጥ በመሥራት የሚገኘውን በረከት ቀምሰህ ታውቃለህ? ብዙ ጊዜያዊ ልዩ አቅኚዎችና ሌሎችም ይህን በረከት ቀምሰዋል። ይህ ለአንዳንዶች ረጅም ርቀት መጓዝ ጠይቆባቸዋል። የሚያስቆጭ ነበር? አንድ ወንድም እንዲህ በማለት ጽፏል:- “እምብዛም ወዳልተሠራበት የአገልግሎት ክልል እንድሄድ ግብዣ ሲቀርብልኝ መጀመሪያ ላይ ለመቀበል አመንትቼ ነበር። ሆኖም በኋላ ለመሄድ ወሰንኩ። እንዲህ ያለ ውሳኔ በማድረጌ አንድም ቀን ቆጭቶኝ የማያውቅ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ውሳኔው ሕይወቴን ለውጦታል። እንደዚህ ያለ መብት በማግኘቴ ይሖዋን ዘወትር አመሰግነዋለሁ።” ብዙ አስፋፊዎች ይበልጥ እርዳታ ወደሚያስፈልግበት ቦታ ሄዶ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ማገልገል ለአገልግሎት ያላቸውን አድናቆት እንዳሳደገላቸው ይናገራሉ። ይህን አጋጣሚ ያገኙትን አነጋግር። በመንፈሳዊ እንደተነቃቁና አሁንም ሌላ አጋጣሚ ቢያገኙ መሄድ እንደሚፈልጉ ትረዳለህ።
5 እርዳታ ይበልጥ ወደሚያስፈልግበት ቦታ ሄዶ ለአጭር ጊዜ ማገልገል ሌላም ጥቅም አለው። እንዲህ የሚያደርጉ ወንድሞችና እህቶች ወደ ሌላው የአገሪቱ ክፍል መዛወር የሚያስከትለውን ‘ኪሳራ ለማስላት’ የሚያስችል ጠቃሚ መረጃ ያገኛሉ።—ሉቃስ 14:28
6 ይሖዋ መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት የመንግሥቱ ምሥራች “በዓለም ሁሉ” እንዲሰበክ ወስኗል። (ማቴ. 24:14) ይህን ከግንዛቤ በማስገባት የምትችል ከሆነ ይበልጥ እርዳታ ወደሚያስፈልግበት ቦታ ለመሄድ ፈቃደኛ ነህን? በሚልዮን የሚቆጠር ሕዝብ በሰፈረባቸው ብዙ አካባቢዎች ከፍተኛ የመንግሥቱ ሰባኪዎች እጥረት አለ።
7 እርዳታ ይበልጥ ወደሚያስፈልግበት ቦታ መዛወር:- ጡረታ ወጥተሃል? ቋሚ ገቢ አለህ? ካልሆነ የራስህን ሥራ ለመሥራት ሁኔታውን ማመቻቸት ትችላለህ? አንተ መሄድ የማትችል ከሆነ ከቤተሰብህ አንዱ ወደ ሌላ ቦታ ሄዶ እንዲያገለግል መርዳት ትችላለህ?
8 ሁኔታውን በጸሎት ካሰብክበት በኋላ ይበልጥ አስፈላጊ ወደሆነበት ቦታ ሄደህ ለማገልገል እንደምትችል ከተሰማህ ጉዳዩን ከቤተሰብህና ከጉባኤህ ሽማግሌዎች ጋር ተወያይበት። ከዚያም ደብዳቤ ጻፍና ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው ከመላኩ በፊት አስተያየትና የድጋፍ ሐሳብ እንዲያክሉበት ለሽማግሌዎቹ ስጣቸው።
9 በደብዳቤው ላይ ምን ምን መጥቀስ ይኖርብሃል? ዕድሜህን፣ የተጠመቅክበትን ዕለት፣ በጉባኤው ውስጥ ያለህን ኃላፊነት፣ የጋብቻ ሁኔታህን እንዲሁም ትንንሽ ልጆች ያለህ መሆን አለመሆኑን ጥቀስ። እንደ ሁኔታህ ሄደህ ለማገልገል የምትመርጠውን አካባቢ ለይተህ ተናገር። ለምሳሌ ያህል ሞቃታማ በሆነና ወበቅ ባለበት አካባቢ መኖር ትችላለህ? ሌላ ቋንቋ መናገር ትችላለህ?
10 ለመሄድ ቅንዓትና ተነሳሽነት አለህን? ይበልጥ እርዳታ ወደሚያስፈልግበት ቦታ ሄደህ ለማገልገል የሚያስችል ሁኔታ አለህ? ከሆነ ይሖዋ የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ በማሳየት በእርሱ የሚታመኑትን ምንጊዜም እንደሚባርክ አስተውል!—መዝ. 34:8፤ ሚል. 3:10