የበለጠ መሥራት ትፈልጋላችሁ?
1 ኢየሱስ የአምላክን መንግሥት በዋጋ ሊተመን ከማይችል መዝገብ ጋር አመሳስሎታል። (ማቴ. 13:44-46) የመንግሥቱን ምሥራች የማሰራጨት ሥራም እንዲሁ ውድ ዋጋ ያለው ሃብት ነው። በዚህ አገልግሎት ሙሉ ተሳትፎ ማድረግ በተወሰነ መጠን የራስን ፍላጎት መሥዋዕት ማድረግን የሚጠይቅ ቢሆንም በሕይወታችን ውስጥ የመጀመሪያውን ቦታ መያዝ ይገባዋል። (ማቴ. 6:19-21) በመንግሥቱ አገልግሎት የበለጠ መሥራት ትፈልጋላችሁ?
2 እነዚህን ወሳኝ ነገሮች ልብ በሉ:- በአገልግሎቱ በግል የምናደርገውን ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ የሚያስፈልጉ ነገሮች አሉ:- (1) የመንግሥቱን ፍላጎቶች በሕይወታችን ለማስቀደም ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ። (ማቴ. 6:33)፤ (2) እምነት ማሳየትና በይሖዋ መታመን። (2 ቆሮ. 4:1, 7)፤ (3) ያልተቋረጠ ልባዊ ጸሎት በማቅረብ የአምላክን እርዳታ መጠየቅ። (ሉቃስ 11:8-10)፤ (4) ጥረትና ከጸሎታችን ጋር የሚስማሙ ነገሮችን ማድረግ።—ያዕ. 2:14, 17
3 አገልግሎታችንን ማስፋት የምንችልባቸው መንገዶች:- ሁላችንም በየወሩ በአገልግሎት የተወሰነ ሰዓት ለማሳለፍ መሠረታዊ ግብ ማውጣት እንችላለን። ሆኖም መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን በሙሉ ለመጠቀም፣ ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት ዘወትር ለመካፈል፣ አቀራረባችሁ ይበልጥ ትርጉም ያለው እንዲሆን ጥረት ለማድረግ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ ለመጠቀም፣ ተመላልሶ መጠየቅ ስታደርጉ ውጤታማነታችሁን ከፍ ለማድረግና እድገት የሚያደርጉ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ለመምራት ጥረት ስለማድረግ አስባችሁ ታውቃላችሁ? ረዳት አቅኚ ወይም የዘወትር አቅኚ ሆናችሁ አሊያም ይበልጥ እርዳታ ወደሚያስፈልግበት ቦታ ሄዳችሁ ማገልገል ትችላላችሁ? የተጠመቅህ ወንድም ከሆንክ የጉባኤ አገልጋይ ወይም ሽማግሌ ለመሆን የሚያስችልህ ብቃት ላይ ለመድረስ እየጣርክ ነው? (1 ጢሞ. 3:1, 10) በቤቴል ለማገልገል፣ በአገልጋዮች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ለመግባት ወይም የልዩ አቅኚነት አገልግሎት ለመጀመር በማመልከት አገልግሎታችሁን ማስፋት ትችሉ ይሆን?—ሉቃስ 10:2
4 የሙሉ ቀን ሥራ የሚሠራና በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ብዙ ሰዓት የሚያጠፋ አንድ ወንድም የዘወትር አቅኚ እንዲሆን ማበረታቻ ተሰጠው። ረዳት አቅኚ ሆኖ ማገልገል ጀመረና የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመጀመር ሁኔታውን አስተካከለ። ከጊዜ በኋላ አሁን ላለበት የወረዳ የበላይ ተመልካችነት ሥራ እንዲዘጋጅ በረዳው በአገልጋዮች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ተካፈለ። የተሰጠውን ማበረታቻ በመቀበሉ በጣም የተደሰተ ሲሆን በመንግሥቱ አገልግሎት የበለጠ ለመካፈል ውሳኔ በማድረጉ ይበልጥ ደስተኛ እንደሆነ ተረድቷል።
5 ይሖዋ ራሳቸውን በፈቃደኝነት የሚያቀርቡ ሰዎችን ይባርካል። (ኢሳ. 6:8) አገልግሎትህን በማስፋት በአጸፋው ከፍተኛ እርካታና ደስታ ከማግኘት ምንም ነገር እንዲያግዳችሁ አትፍቀዱ።