አገልግሎትህን ማስፋት የምትችልባቸው መንገዶች
1 ከ40 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት በጥር 15, 1955 መጠበቂያ ግንብ ላይ “የአቅምህን ያህል እየሠራህ ነውን?” በሚል ርዕስ አንድ ትምህርት ወጥቶ ነበር። መጠበቂያ ግንቡ የይሖዋ ሕዝቦች በመንግሥቱ ሥራ የሚያደርጉትን ተሳትፎ ማሳደግ እንዲችሉ በአገልግሎት የሚያደርጉትን የግል ጥረት እንዴት ማሻሻል እንደሚችሉ በፍቅራዊ መንገድ ጠቅሷል። ያን ጊዜ የተሰጠው ምክር ዛሬም እድገት ለማድረግ ጥረት ማድረጋችንን ስንቀጥል ተግባራዊ ሆኖ እናገኘዋለን።
2 ሁሉንም አገልግሎታችንን እንድንፈጽም የሚያነሳሳን “አንተም በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ” የሚለው ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ መሆን አለበት። (ማር. 12:30) የይሖዋን መንግሥት የማሳወቁን ሥራ ለማስፋፋት በሚያስችሉን አጋጣሚዎች ሙሉ በሙሉ በመጠቀም ለእርሱ ያለንን ፍጹም ፍቅር ማሳየት እንችላለን። አገልግሎትህን ማስፋት የምትችልባቸው የሚከተሉትን መንገዶች ተመልከት።
3 ኃላፊነትህን ተሸከም፦ ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ ወንድሞች የጉባኤ አገልጋዮች ከዚያም ሽማግሌዎች ሆነው ለማገልገል እድገት በማድረግ ብቃቱን ለማሟላት ጥረት ማድረግ ይችላሉ። “ብቃቱን ለማሟላት ትጣጣራለህን?” እና “ለማገልገል ብቃቱ አለህን?” በሚሉ ርዕሶች በመጠበቂያ ግንብ 17-111 ላይ የወጡት ትምህርቶች በርካታ ወንድሞች ራሳቸውን ለጉባኤ ኃላፊነቶች ለማቅረብ እንዲነሳሱ አድርጓቸዋል። የጉባኤ ሽማግሌዎችህ ብቃቱን ለማሟላት ምን ማድረግ እንዳለብህ አንዳንድ ሐሳቦች እንዲሰጡህ ጠይቃቸው።
4 ነጠላ የሆኑና እንግሊዝኛ የሚችሉ ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች በአገልጋዮች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት መካፈልን በቁም ነገር እንዲያስቡበት ተጋብዘዋል። ለ1986-1995, ለ1996 እና ለ1997 በተዘጋጁት የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ማውጫ ላይ “የአገልጋዮች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት” [Ministerial Training School] በሚለው ስር የቀረቡትን ጽሑፎች በማንበብ ራስህን ከትምህርት ቤቱ ጋር ማስተዋወቅ ትችላለህ። ከፊትህ “ሥራ የሞላበት ትልቅ በር” ተከፍቶ እንዳለ ይታይሃል? (1 ቆሮ. 16:9) በተከፈተው በር የገቡ ብዙ ወንድሞች ከትምህርት ቤቱ ከተመረቁ በኋላ አነዚያን ሁሉ የአገልግሎት መብቶች እናገኛለን ብለው አልጠበቁም ነበር። ዛሬ እነዚህ ወንድሞች በቤቴል ወይም በመስክ ላይ ልዩ አቅኚዎች፣ ሚስዮናውያን ወይም የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
5 የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመጀመር ተጣጣር፦ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ወጣቶች፣ የቤት እመቤቶችና ከሥራ በጡረታ የተገለሉ ሁሉ አቅኚነትን በቁም ነገር ሊያስቡበት ይገባል። የሐምሌ 1998 የመንግሥት አገልግሎታችንን አባሪ ከከለስክ በኋላ ከአንተ ሕይወት ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ ያላቸውን አቅኚዎች አማክር። እነርሱ እንዳደረጉት ሁሉ አንተም አቅኚ በመሆን አገልግሎትህን ለማስፋት ትነሳሳ ይሆናል። (1 ቆሮ. 11:1) የምታደርገውን ተሳትፎ በወር ወደ 70 ሰዓት ከፍ በማድረግ የዘወትር አቅኚ ሆነህ ማገልገል ትችል ይሆን?
6 በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ በቅርንጫፍ ቢሮዎችና በቤቴል ቤቶች የሚያገለግሉ ከ17,000 በላይ ወንድሞችና እህቶች አሉ። የመጋቢት 1995 የመንግሥት አገልግሎታችን (እንግሊዝኛ) በዚህ አገልግሎት ለመካፈል ማሟላት ያለብንን ብቃት አብራርቷል። ለቤቴል አገልግሎት መብት ብቁ መሆን አለመሆንህን ለምን አትመረምርም?
7 ይበልጥ እርዳታ በሚያስፈልግበት ቦታ አገልግል፦ የምትኖረው የአገልግሎት ክልሉ በተደጋጋሚ በተሸፈነበት ወይም ሸክሙን መጋራት የሚችሉ ብዙ ወንድሞች ባሉበት ቦታ ነው? ምንም እንኳ በዋና ከተማችንና በሌሎች ጥቂት ከተሞች ያለው ሬሾ አንድ አስፋፊ ለ1,000 እና ከዚያም ለሚያንሱ ሰዎች ቢሆንም በአገራችን በሚገኙ በአብዛኛዎቹ ቦታዎች ሬሾው አንድ አስፋፊ ከ20,000 በላይ ለሚሆን ሕዝብ ነው! ይበልጥ እርዳታ ወደሚያስፈልግበት ቦታ ተዛውረህ በአገልግሎት ያለህን ተሳትፎ ለማሳደግ አስበህ ታውቃለህ? ምናልባትም የምትሄድበት ቦታ ተጨማሪ ሠራተኞች የሚያስፈልጉበት ቅርብ የገጠር ከተማ ሊሆን ይችላል። (ማቴ. 9:37, 38) ይህ በችኮላ መደረግ የለበትም። በጸሎት ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው። (ሉቃስ 14:28-30) ሁኔታህን በተመለከተ ከጉባኤህ ሽማግሌዎችና ከወረዳ የበላይ ተመልካቹ ጋር ተወያይ። ጥበብ የሚሆነው እንዲህ ያለውን ለውጥ አሁን ማድረግህ ይሁን ወይም ወደፊት እንዲህ ለማድረግ መዘጋጀትህ ያወያዩሃል። የት ሄደህ ብታገለግል የተሻለ እንደሚሆን የሚጠቁም ሐሳብ ለማግኘት ወደ ማኅበሩ መጻፍ ከፈለግህ ከደብዳቤህ ጋር የጉባኤው የአገልግሎት ኮሚቴ ፊርማ የሰፈረበት ሌላ ደብዳቤ ተያይዞ መላክ አለበት።
8 የአገልግሎትህን ጥራት አሻሽል፦ ሁላችንም የመስክ አገልግሎታችንን ጥራት በማሻሻል በስብከቱ ሥራ ይበልጥ የተሟላ ተሳትፎ ማድረግ እንችል ይሆናል። አመቺ በሚሆንበት ቦታ ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ለመጠቀም ጥረት ታደርጋለህ? በተለይ ከመንገድ ወደ መንገድ ስታገለግል ከሰዎች ጋር ሳትነጋገር ብዙ ሰዓት እንዲባክን ባለመፍቀድ በመስኩ በትጋት ትሠራለህ? ከቤት ወደ ቤት መሄድን፣ መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት መስጠትን እንዲሁም ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግንና መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናትን ጨምሮ በሁሉም የሥራው ዘርፎች ትሳተፋለህ? ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ስታገኝ ጥሩ ማስታወሻ በመያዝ ረገድ ጠንቃቃ ነህ? ጥናት የምትመራ ከሆነ የማስተማር ችሎታህን ማሻሻል ትችላለህ? የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችህ ራሳቸውን እንዲወስኑና እንዲጠመቁ ለማነሳሳት ልትጠቀምባቸው የምትችልባቸውን ሐሳቦች ከሰኔ 1996 የመንግሥት አገልግሎታችን አባሪ ላይ መከለሱ ጥሩ ይሆናል።
9 በአገልግሎት የምናደርገውን ተሳትፎ ለማሳደግና ለማሻሻል የሚረዱ መንገዶችን በተመለከተ አገልግሎታችንን ለመፈጸም መደራጀት በተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 9 ላይ ይበልጥ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ተሰጥቷል። በእርግጥም ሁላችንም በአምላክ አገልግሎት የተቻለንን ያህል የመሥራት ፍላጎት ሊኖረን ይገባል። ለመንፈሳዊ ግቦችህ ለምን ክብደት ሰጥተህ አታስብባቸውም? አንደኛ ጢሞቴዎስ 4:15 “ማደግህ በነገር ሁሉ እንዲገለጥ ይህን አስብ፣ ይህንም አዘውትር” በማለት የሚሰጠውን ምክር ሥራ ላይ አውል።