በመለኮታዊ ትምህርት አንድ መሆን —እውነተኛ የወንድማማችነት አንድነት ሲቃኝ
አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ገና መገኘት ካልጀመረች አንዲት ሴት ጋር በሚደረግ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተካፈለ። በመለኮታዊ ትምህርት አንድ መሆን የተሰኘውን ቪዲዮ እንድትመለከት ጋበዛት። በዚያው ሳምንት በስብሰባ ላይ የተገኘች ሲሆን በስብሰባው ላይ በመገኘቷ በጣም እንደተደሰተች ተናግራለች። ይህ ቪዲዮ እንዲህ ዓይነት ፈጣን ውጤት ያስገኘው ለምንድን ነው? በዚህ ዓመፀኛ በሆነና በጥላቻ በተሞላ ዓለም ውስጥ በተግባር ሲገለጽ ባየችው ውድ የሆነ የወንድማማች አንድነት ስለተነካች ነው።—ዮሐ. 13:35
በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች መካከል ያለውን ሰላምና ፍቅር ለማየት ይህንን ቪዲዮ ተመልከት። ከዚያም በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ አሰላስል:-
(1) ከ1993-94 ለተደረጉት ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች “መለኮታዊ ትምህርት” የሚለው ጭብጥ ተስማሚ የነበረው ለምንድን ነው?—ሚክ. 4:2
(2) የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ለአንዳንድ ቤተሰቦች ምን ትርጉም አለው? ለአንተስ?
(3) ከይሖዋ መማር አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?—መዝ. 143:10
(4) ትልልቅ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን ለማዘጋጀት ምን ውጣ ውረዶችን መወጣት ይጠይቃል?
(5) በተካፈልክባቸው ትልልቅ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መዝሙር 133:1 እና ማቴዎስ 5:3 እውን ሆነው ያገኘሃቸው እንዴት ነው?
(6) መለኮታዊ ትምህርት ሰዎችን የመለወጥ ኃይል እንዳለው በይፋ የሚያሳየው የትኛው የስብሰባው ዓቢይ ገጽታ ነው?—ራእይ 7:9
(7) እስከ ዛሬ ከተከናወኑት የእውነተኛ ክርስቲያኖች ጥምቀት ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የቱ ነው?
(8) በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ፍጻሜያቸውን እያገኙ ያሉት የትኞቹ የሚክያስ፣ የጴጥሮስና የኢየሱስ ቃላት ናቸው?
(9) አንድነት ያለው ደስተኛ ሰብዓዊ ቤተሰብ እንዲያው ሕልም ብቻ እንዳልሆነ የሚያረጋግጥልህ ምንድን ነው?
(10) ይሄን ቪዲዮ ለማን ለማሳየት አስበሃል? ለምን?
አንዲት እህት ይህን ቪዲዮ ከተመለከተች በኋላ እንዲህ ስትል ጠቅለል አድርጋ በጥሩ ሁኔታ አስቀምጣዋለች:- “ቪዲዮው በዓለም ዙሪያ በጣም ብዙ ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች በዚህ ቅጽበት ይሖዋን በታማኝነት እያገለገሉ መሆናቸውን እንዳስታውስ ይበልጥ ይረዳኛል። . . . የወንድማማች አንድነታችን ምንኛ ውድ ነው!”—ኤፌ. 4:3