ምሥራቹን ለመስበክ የተደራጁት የይሖዋ ምሥክሮች
የይሖዋ ምሥክሮች ምሥራቹን ለሌሎች ለማዳረስ ከ100 ለሚበልጡ ዓመታት ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል። በዓለም ላይ ታይቶ በማይታወቅ ታላቅ የስብከት ዘመቻ አማካኝነት ምሥራቹን ከ230 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ በመቶዎች በሚቆጠሩ ቋንቋዎች ለሰዎች እናዳርሳለን። (ማቴ. 24:14) ሥራው ይህን ያህል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተከናወነ ያለውስ እንዴት ነው? ምሥራቹን ለመስበክ የተደራጁት የይሖዋ ምሥክሮች የተባለው ቪዲዮ በዓለም ዙሪያ እየተከናወነ ያለውን ሥራችንን በዝርዝር በማሳየት ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል። ይህን ፊልም ከተመለከታችሁ በኋላ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክሩ።
ይህ ፊልም ለሚከተሉት ነገሮች ያላችሁን ግንዛቤና አድናቆት የጨመረላችሁ እንዴት ነው? (1) የይሖዋ ድርጅት ምሥራቹን ለመስበክ እያደረገ ስላለው ጥረት (2 ጢሞ. 4:2)፣ (2) በዓለም ዙሪያ ስለሚገኙት የቤቴል ቤተሰቦች፣ (3) ለሚስዮናውያንና ለበላይ ተመልካቾች ስለሚሰጠው ሥልጠና (2 ጢሞ. 2:2)፣ (4) እያንዳንዱን ዕለት በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ ምርምር በማድረግ መጀመርና በየሳምንቱ ለጉባኤ ስብሰባዎች መዘጋጀት ስለሚያስገኘው ጥቅም (ሥራ 17:11)፣ (5) በክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ላይ መገኘት ስላለው ጥቅም (ዕብ. 10:24, 25)፣ (6) ምድር ገነት ስትሆን ስለምታገኟቸው በረከቶች (ኢሳ. 11:9) እና (7) እየተካሄደ ባለው የመከር ሥራ የበኩላችሁን አስተዋጽኦ በማበርከት ረገድ ስላገኛችሁት መብት።—ዮሐ. 4:35
ይህ ፊልም ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን የይሖዋ ምሥክሮች ከሚያከናውኑት ዓለም አቀፍ ሥራ ጋር ለማስተዋወቅ የሚረዳ ግሩም መሣሪያ ነው። (8) ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን፣ ለዘመዶቻችን እንዲሁም ለሌሎች ሰዎች ፊልሙን ማሳየት ጥሩ የሚሆነው መቼ ነው? (9) ፊልሙን ለሰዎች ስታሳዩ ያገኛችሁት በጎ ምላሽ አለ?
ይሖዋ እያከናወነ ባለው ነገር ላይ ማሰላሰላችን እኛም እንደ መዝሙራዊው “እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ አንተ ያደረግኸው ድንቅ ነገር ብዙ ነው፤ ለእኛ ያቀድኸውን፣ ሊዘረዝርልህ የሚችል ማንም የለም” ብለን እንድንናገር ይገፋፋናል። (መዝ. 40:5) በመሆኑም ሰዎች ለይሖዋና ለድርጅቱ አድናቆት እንዲያዳብሩ ለመርዳት ይህን ፊልም ጥሩ አድርገን እንጠቀምበት!