ለማስተማር፣ ለማነቃቃትና ለማበርታት የሚረዱ መሣሪያዎች
1 ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስና ስለ ይሖዋ ምሥክሮች እንዲማሩ በመርዳት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አላቸው። ብዙዎች ለእውነት ጽኑ አቋም እንዲኖራቸው አነቃቅተዋል። ራሳቸውን የወሰኑ የአምላክ ሕዝቦች እምነት እንዲጠነክርና አድናቆታቸው ከፍ እንዲል አድርገዋል። እነዚህ ነገሮች ምንድን ናቸው? የይሖዋ ድርጅት የሚያዘጋጃቸው የቪዲዮ ክሮች ናቸው። አሥሩንም የቪዲዮ ክሮች አይታችኋቸዋል? ካያችኋቸው ቆይቷል? ለአገልግሎትስ ትጠቀሙባቸዋላችሁ? መላው የወንድማማች ማኅበር የሚል 11ኛ ቪዲዮ እንደወጣ በአውራጃ ስብሰባው ላይ ተነግሮ ነበር። እንዲመጣልህ አዝዘሃል? ግሩም ከሆኑት ከእነዚህ መሣሪያዎች ይበልጥ ጥቅም ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?
2 የሐምሌ 1, 1999 መጠበቂያ ግንብ “የአምላክን ቃል በቤተሰብ መልክ አዘውትራችሁ አጥኑ” በሚለው ርዕስ ሥር “ማኅበሩ ካዘጋጃቸው ትምህርት ሰጪ የቪዲዮ ክሮች መካከል ከአንዱ የተወሰነውን ክፍል ለማየት . . . ከዚያም ውይይት ለማድረግ የተወሰነውን የጥናታችሁን ጊዜ ልትጠቀሙበት ትችላላችሁ” ሲል ሐሳብ አቅርቦ ነበር። ይህን ጥሩ ምክር ተግባራዊ ለማድረግ በአገልግሎት ስብሰባ ላይ በሁለት ወር አንዴ ስለ አንድ ቪዲዮ ክፍል ይቀርባል። በአገልግሎት ስብሰባ ላይ ክፍሉ ከመቅረቡ በፊት ሁላችሁም ቪዲዮውን አይታችሁ እንድትመጡ እናበረታታችኋለን።
3 በዚህ ወር የምንጀምረው የይሖዋ ምሥክሮች —ከስሙ በስተጀርባ ያለ ድርጅት በሚል ርዕስ ያዘጋጀነውን የመጀመሪያ ቪዲዮ ይሆናል። ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ቪዲዮውን እያየህ አዳምጥ:-
◼ የይሖዋ ምሥክሮች ይበልጥ የሚታወቁት በምንድን ነው?
◼ በቤቴል የሚከናወነው ሥራ ሁሉ ከየትኛው ጥቅስ ጋር ይያያዛል?
◼ ጽሑፍ ላይ ከመውጣቱ በፊት ሲዘጋጅ፣ ፎቶ ሲነሳና ሲሳል ያየኸው የትኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ነው?
◼ ጽሑፎቻችን ከሚዘጋጁበት መንገድ አንተን የማረከህ የትኛው ነው?
◼ ማኅበሩ ከ1920 እስከ 1990 ምን ያህል ጽሑፎችን አትሟል?
◼ ከአምላክ ሕዝቦች መካከል ለቤቴል አገልግሎት ብቁ ለመሆን መጣር ያለባቸው በተለይ እነማን ናቸው?—ምሳሌ 20:29
◼ የቤቴል ቤተሰብ ለሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች የላቀ ምሳሌ የሚሆነው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
◼ ምሥራቹን በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች ለማዳረስ በሚደረገው ጥረት በቤቴል በመከናወን ላይ ካለው ሥራ የትኛው ይማርክሃል?
◼ ለዓለም አቀፉ ሥራ የገንዘብ ድጋፍ የሚገኘው እንዴት ነው?
◼ የትኛውን ሥራ በቅንዓት መደገፍ እንችላለን? በምንስ መንፈስ?—ዮሐ. 4:35፤ ሥራ 1:8
◼ ከስማችን በስተጀርባ ስላለው ድርጅት ምን ይሰማሃል?
◼ ይህን ቪዲዮ በአገልግሎት ላይ እንዴት ልትጠቀምበት ትችላለህ?
በታኅሣሥ ወር መጽሐፍ ቅዱስ—ትክክለኛ ታሪክና አስተማማኝ ትንቢት የሚለውን ቪዲዮ እንከልሳለን።