በዓለም ላይ ታይቶ የማይታወቅ ታላቅ የስብከት ዘመቻ!
የይሖዋ ምሥክሮች ወንጌሉን ወይም ምሥራቹን ለሌሎች ለማዳረስ ከ100 ለሚበልጡ ዓመታት ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል። (1 ቆሮ. 9:23) በዓለም ላይ ታይቶ በማይታወቀው በዚህ ታላቅ የስብከት ዘመቻ አማካኝነት ምሥራቹን ከ230 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ በመቶዎች በሚቆጠሩ ቋንቋዎች ለሰዎች እናዳርሳለን። (ማቴ. 24:14) ይሁን እንጂ ሥራው ይህን ያህል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተከናወነ ያለውስ እንዴት ነው?
ምሥራቹን ለመስበክ የተደራጁት የይሖዋ ምሥክሮች የተባለው ቪዲዮ የዓለም አቀፉ ሥራችንን በርካታ ገጽታዎች በማንሳት ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል። ይህንን ፊልም በምትመለከትበት ጊዜ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር:- (1) የስብከቱ እንቅስቃሴያችን የተደራጀውና አመራር የሚያገኘው እንዴት ነው? (2) የጽሑፍ ዝግጅት፣ የትርጉም አገልግሎት፣ የአርት እና የኦዲዮ/ቪዲዮ አገልግሎት ክፍሎች ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱት እንዴት ነው? (3) መጠነ ሰፊ የሆነው ጽሑፎችን የማተሙና የማጓጓዙ ሥራችን ዓላማ ምንድን ነው? (ዮሐ. 17:3) (4) በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ምን ያህል ጽሑፎች ይታተማሉ? (5) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱት ጽሑፎቻችን ምን ዓላማ አከናውነዋል? (ዕብ. 4:12) (6) ማየት ወይም መስማት የተሳናቸውን ሰዎች በመንፈሳዊ ለመርዳት ምን እየተደረገ ነው? (7) ለሥራችን የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ የምናገኘው እንዴት ነው? (8) የሆስፒታል መረጃ አገልግሎት ክፍል፣ የአገልግሎት ዘርፍና የአውራጃ ስብሰባ ዲፓርትመንት ከሚያከናውኑት አገልግሎት ጥቅም የምናገኘው እንዴት ነው? (9) የይሖዋ ምሥክር እንደመሆንህ መጠን ይህ ፊልም ለሚከተሉት ነገሮች ያለህን አድናቆት የጨመረልህ እንዴት ነው? (ሀ) የይሖዋ ድርጅት ምሥራቹን ለመስበክ እያደረገ ስላለው ጥረት፣ (ለ) በዓለም ዙሪያ ከ100 በላይ በሆኑ አገሮች ውስጥ ስለሚገኙት የቤቴል ቤተሰቦች፣ (ሐ) ለበላይ ተመልካቾችና ለሚስዮናውያን ስለሚሰጠው ሥልጠና፣ (መ) እያንዳንዱን ዕለት በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ ምርምር በማድረግ መጀመርና በየሳምንቱ ለጉባኤ ስብሰባዎች መዘጋጀት ስላለው ጠቀሜታ፣ (ሠ) በክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ላይ መገኘት ስላለው ጥቅም፣ (ረ) ምድር ገነት ስትሆን ስለሚኖረው ለውጥ (ኢሳ. 11:9)፣ (ሰ) እየተካሄደ ባለው የመከር ሥራ ላይ በግለሰብ ደረጃ ስለመካፈል።—ዮሐ. 4:35
ይህንን ፊልም ለዘመዶችህ፣ ተመላልሶ መጠየቅ ለምታደርግላቸውና ለምታውቃቸው ሰዎች እንዲሁም ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችህ ስታሳይ ምን በጎ ምላሽ አገኘህ? ጊዜ ሳታጠፋ ይህን ፊልም ሌሎችም እንዲያዩት ለማድረግና ምሥራቹን ለማካፈል ለምን አትሞክርም?—ማቴ. 28:19, 20