ይሖዋ ላሳየን ፍቅር አመስጋኝ መሆን የሚያስገኛቸው በረከቶች —ክፍል 2
1 ባለፈው ወር በዚህ ርዕስ በቀረበው ትምህርት በአገልግሎቱ ለይሖዋ ፍቅር አመስጋኝነታችንን የምናሳይባቸውን አራት መንገዶች ተመልክተን ነበር። (1 ዮሐ. 4:9-11) አሁን ደግሞ አምስት ተጨማሪ መንገዶችን እናያለን። ሌሎችን በመንፈሳዊ በመርዳቱ ሥራ ሙሉ ተሳትፎ ስናደርግ እንባረካለን።
2 መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት:- ይህ ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ሰዎችን ለማግኘትና ጠቃሚ የሆኑ ጽሑፎችን ለማበርከት የሚያስችለን ውጤታማ መንገድ ነው። ‘ጊዜውን መዋጀትና’ ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ላገኘነው ማንኛውም ሰው መመሥከር ጠቃሚ ነው። (ኤፌ. 5:16) በዚህ መንገድ ለመመሥከር ድፍረት ይጠይቅብን ይሆናል፤ ቢሆንም ይሖዋ ያሳየንን ፍቅርና የሰዎችን ፍላጎት ከፍ አድርገን የምንመለከት ከሆነ በእያንዳንዱ አጋጣሚ ምሥክርነቱን እንሰጣለን።—2 ጢሞ. 1:7, 8
3 አንድ ሚስዮናዊ በታክሲ ውስጥ አብሮት ከሚጓዝ አንድ መንገደኛ ጋር ውይይት በመክፈቱ በእጅጉ ተባርኳል። ሰውየው ፍላጎት አሳየ። ተመላልሶ መጠየቅ ተደረገለትና መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረ። ይህ ሰው ወደ እውነት መጥቶ እድገት በማድረግ የጉባኤ ሽማግሌ እስከ መሆን ደርሷል!
4 ደብዳቤ መጻፍ:- ምናልባት በአንድ ዓይነት የአካል ጉዳት ወይም በአየሩ ሁኔታ አስቸጋሪነት የተነሳ ከቤት ወደ ቤት መሄድ አንችል ይሆናል። ደብዳቤ በመጻፍ ለምናውቃቸው፣ የሚወዱትን ሰው በሞት ላጡ ወይም በክልላችን ውስጥ ቤታቸው ላላገኘናቸው ሰዎች አጠር ያለ ምሥክርነት ልንሰጥ እንችላለን። ስሜት ቀስቃሽ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ከያዙት ትራክቶቻችን መካከል አንዱን ከደብዳቤው ጋር አያይዘን መላክና ተቀባዩ ጥያቄዎች ካሉት መልሶ እንዲጽፍልን ማበረታታት እንችላለን። እባካችሁ የራሳችሁን ወይም የመንግሥት አዳራሹን አድራሻ ተጠቀሙ እንጂ የቅርንጫፍ ቢሮውን አድራሻ አትጠቀሙ።
5 በስልክ መመሥከር:- ይህ ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት ልናገኛቸው ያልቻልናቸውን ሰዎች ማግኘት ጥሩ ዘዴ ነው። በዚህ መንገድ የምንሰጠው ምሥክርነት በጥንቃቄ፣ በደግነት፣ በብልሃትና በጥበብ ካደረግነው በጣም ግሩም ምላሽ ልናገኝ እንችላለን።
6 አንዲት እህት በስልክ ስትመሠክር አንዲትን ሴት ስለ ራሷም ሆነ ስለ ቤተሰቧ የወደፊት ሕይወት ትኩረት ሰታ አስባበት ታውቅ እንደሆነ ጠየቀቻት። ሴትዮዋም አስባበት እንደምታውቅ ተናገረች። የወደፊት ተስፋዋ ስለ ጨለመባት እቤት ውስጥ ብቻዋን ተገልላ እንደምትኖር ገለጸችላት። ሴትዮዋ እህት ባሳየቻት ልባዊ አሳቢነት ስለተነካች በአካባቢው በሚገኝ የገበያ ስፍራ ከእህት ጋር ለመገናኘት ተስማማች። በውጤቱም መጽሐፍ ቅዱስን እንድታጠና የቀረበላትን ግብዣ ምንም ሳታንገራግር ተቀበለች!
7 እንግዶችን በመቀበል:- ለጎረቤቶቻችን ፍቅር ካለን ወደ ስብሰባዎቻችን አንድ እንግዳ ሰው ሲመጣ ልብ ለማለትና በመምጣቱ እንደተደሰትን እንዲሰማው ለማድረግ ንቁ እንሆናለን። (ሮሜ 15:7) ለመንፈሳዊ ደህንነቱ ከልብ በሚያስቡ ሰዎች መሃል እንደሆነ እንዲሰማው አድርጉ። ከልብ የመነጨ አሳቢነታችንና መጽሐፍ ቅዱስን በግል እንዲያጠና የምናቀርብለት ግብዣ እርዳታችንን እንዲቀበል ሊያነሳሳው ይችላል።
8 በመልካም ምግባራችን:- በጥሩ ምግባራችን እውነት እንዲመሰገን እናደርጋለን። (ቲቶ 2:9, 10) በዓለም ያሉ ሰዎች ስለ እኛ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች መልካም ነገር ሲናገሩ አምላካችን ይከበራል። (1 ጴጥ. 2:12) ይህም ሌሎች በሕይወት መንገድ ላይ መጓዝ እንዲጀምሩ ሊረዳቸው ይችላል።
9 ይሖዋ ላሳየን ታላቅ ፍቅር አመስጋኝነታችንን የምንገልጽባቸውን እነዚህን አምስት መንገዶች በመከለስ ለምን ተግባራዊ አታደርጋቸውም። (1 ዮሐ. 4:16) እንዲህ ካደረግህ ብዙ በረከቶችን ታጭዳለህ።