መስበካችንን መቀጠል ያለብን ለምንድን ነው?
1 የመንግሥቱ ስብከት ሥራ እናንተ በምትኖሩበት አካባቢ ለረጅም ጊዜ ሲሠራ ቆይቷልን? (ማቴ. 24:14) እንደዚያ ከሆነ የጉባኤው ክልል በሚገባ እንደተሸፈነ ይሰማችሁ ይሆናል። ምናልባትም ስትሰብኩ የምታገኟቸው አብዛኞቹ ሰዎች ለመንግሥቱ መልእክት ግድ የለሾች ይሆናሉ። ቢሆንም የኢሳይያስ ትንቢት (እንግሊዝኛ) በተባለው መጽሐፍ ጥራዝ 2 ገጽ 141 ላይ ስለ ኢየሱስ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት የተገለጸውን ልብ በሉ:- “በአንዳንድ ቦታዎች በአገልግሎታቸው የሚያገኙት ውጤት ከድካማቸውና ከጥረታቸው ጋር ሲወዳደር ከቁጥር የማይገባ ይመስላል። እንደዚያም ሆኖ ይጸናሉ።” ይሁን እንጂ መስበካችንን መቀጠል ያለብን ለምንድን ነው?
2 ኤርምያስን አስታውሱ:- በስብከቱ ሥራ በታማኝነት መጽናታችን ሰዎች በሚሰጡን ምላሽ ላይ የተመካ መሆን የለበትም። ኤርምያስ ምንም እንኳን የሰሙት በጣም ጥቂቶች ቢሆኑና ብዙዎቹ መልእክቱን ይቃወሙ የነበረ ቢሆንም በዚያው ክልል ውስጥ ለ40 ዓመታት ሰብኳል። ኤርምያስ የጸናው ለምን ነበር? የሚሠራው አምላክ እንዲሠራ ያዘዘውን ሥራ በመሆኑና ከፊቱ ምን እንደሚመጣ ማወቁ መስበኩን እንዲቀጥል አስገድዶታል።—ኤር. 1:17፤ 20:9
3 የእኛም ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። ኢየሱስ “ለሕዝብም እንድንሰብክና በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ በእግዚአብሔር የተወሰነ እርሱ እንደ ሆነ እንመሰክር ዘንድ” አዝዞናል። (ሥራ 10:42) የያዝነው መልእክት ለሚሰሙት የሕይወትና የሞት ጉዳይ ነው። ሰዎች ፍርድ የሚሰጣቸው ለምሥራቹ በሚሰጡት ምላሽ መሠረት ነው። የእኛ ኃላፊነት ልክ እንደታዘዝነው ማድረግ ነው። ሰዎች ለመስማት ፈቃደኞች በማይሆኑበት ጊዜ እንኳን ማድረግ ያለብንን ማድረጋችንን በመቀጠል ለእነሱ ያለንን ጥልቅ ፍቅር እንዲሁም ከልብ ለይሖዋ ያደርን መሆናችንን ለማሳየት አጋጣሚ እናገኛለን። ይሁን እንጂ ሌላም ምክንያት አለን።
4 እኛም እንጠቀማለን:- በክልሉ ውስጥ ያለው ምላሽ ምንም ይሁን ምን የአምላክን ፈቃድ ማድረጋችን በሌላ በምንም መንገድ የማይገኝ ውስጣዊ ሰላም፣ እርካታና ደስታ ይሰጠናል። (መዝ. 40:8) ሕይወታችን እውነተኛ ትርጉምና ዓላማ ያለው ይሆናል። ይበልጥ በአገልግሎቱ በተካፈልን መጠን ልባችንና አእምሮአችንም የዚያኑ ያህል በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር ባለን ተስፋና በምናገኘው ደስታ ላይ ያተኮረ ይሆናል። በእነዚህ ቅዱስ ጽሑፋዊ ተስፋዎች ላይ ማሰላሰላችን መንፈሳዊነታችንን ያጎለብተዋል፣ ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድናም ያጠናክርልናል።
5 በስብከት እንቅስቃሴያችን ፈጣን ምላሽ ባናይም እንኳን ይሖዋ በፈቀደው ጊዜ የሚበቅል የእውነት ዘር በአንድ ሰው ልብ ውስጥ ተዘርቶ ይሆናል። (ዮሐ. 6:44፤ 1 ቆሮ. 3:6) ማናችንም ብንሆን ባለንበት አካባቢም ይሁን በዓለም ዙሪያ ገና ምን ያህል ሰዎች በይሖዋ ሕዝቦች ጥረት ስለ መንግሥቱ ሊማሩ እንደሚችሉ አናውቅም።
6 “ጊዜው መቼ እንዲሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ፤ ትጉ፤ ጸልዩም። ለእናንተም የምነግራችሁን ለሁሉ እላለሁ፤ ትጉ” የሚለውን የኢየሱስን መመሪያ ከምን ጊዜውም በላይ ተግባራዊ ልናደርገው ይገባል። (ማር. 13:33, 37) እንግዲያው ሁላችንም የመንግሥቱን ምሥራች መስበካችንን በመቀጠልና ታላቅና ቅዱስ የሆነውን ስሙን በመቀደሱ ሥራ በመካፈል የይሖዋን ልብ ደስ እናሰኝ።