በተደጋጋሚ የምንሄደው ለምንድን ነው?
1. የስብከት ሥራችንን አስመልክቶ ምን ጥያቄ ይነሳል?
1 በብዙ ቦታዎች የአገልግሎት ክልላችንን በተደጋጋሚ እንሸፍናለን። የቤቱ ባለቤት ፍላጎት እንደሌለው ነግሮንም እንኳ ተመልሰን ወደዚያ ቤት በተደጋጋሚ ከመሄድ ወደኋላ አንልም። ታዲያ ቀደም ሲል ጥሩ ምላሽ ያልሰጡን ሰዎች ቤት መሄዳችንን የማናቋርጠው ለምንድን ነው?
2. ከአገልግሎታችን ወደኋላ የማንልበት ዋነኛው ምክንያት ምንድን ነው?
2 ለይሖዋና ለሰዎች ያለን ፍቅር፦ ከአገልግሎታችን ወደኋላ የማንልበት ዋነኛው ምክንያት ለይሖዋ ያለን ፍቅር ነው። ልባችን ስለ ታላቁ አምላካችን መናገራችንን እንድንቀጥል ይገፋፋናል። (ሉቃስ 6:45) ለይሖዋ ያለን ፍቅር ሕጎቹን እንድንታዘዝና ሌሎችም ተመሳሳይ ነገር ማድረግ እንዲችሉ እንድንረዳቸው ግድ ይለናል። (ምሳሌ 27:11፤ 1 ዮሐ. 5:3) በዚህ ሥራ በታማኝነት መጽናታችን የተመካው ሰዎች በሚሰጡት ምላሽ ላይ አይደለም። የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ስደት ባጋጠማቸው ጊዜም እንኳ “ያለማሰለስ” መስበካቸውን ቀጥለዋል። (ሥራ 5:42 NW) ሰዎች መልእክታችንን ለማዳመጥ ፈቃደኛ አለመሆናቸው ተስፋ እንዲያስቆርጠን ከመፍቀድ ይልቅ በጽናት ማገልገላችንን በመቀጠል ለይሖዋ ያለንን ጥልቅ ፍቅር እናሳያለን።
3. ለሰዎች ያለን ፍቅር በስብከቱ ሥራችን እንድንቀጥል የሚረዳን እንዴት ነው?
3 ከአገልግሎታችን ወደኋላ የማንልበት ሌላው ምክንያት ደግሞ ለሰዎች ያለን ፍቅር ነው። (ሉቃስ 10:27) ይሖዋ ማንም እንዲጠፋ አይፈልግም። (2 ጴጥ. 3:9) በተደጋጋሚ በተሸፈኑ ክልሎች ውስጥ እንኳ ይሖዋን ማገልገል የሚፈልጉ ሰዎችን እያገኘን ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ከ56 ሰዎች መካከል አንዱ የይሖዋ ምሥክር በሆነባት በጓዴሎፕ ባለፈው ዓመት 214 ሰዎች ተጠምቀዋል። በመታሰቢያው በዓል ላይ 20,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች የተገኙ ሲሆን ይህ ማለት በጓዴሎፕ ውስጥ ከሚገኙ 22 ሰዎች መካከል አንዱ በበዓሉ ላይ ተገኝቶ ነበር!
4. በክልላችን ውስጥ ምን ዓይነት ለውጦች ሊከሰቱ ይችላሉ?
4 በክልላችን ውስጥ የሚከሰቱ ለውጦች፦ የክልላችን ሁኔታ በየጊዜው ይለዋወጣል። ከዚህ በፊት ጥሩ ምላሽ ወዳላገኘንበት አንድ ቤት ተመልሰን ስንሄድ ምናልባት በሩን የሚከፍተው ከዚህ በፊት መልእክታችንን በጭራሽ ሰምቶ የማያውቅ ሌላ የቤተሰቡ አባል ይሆናል። አሊያም ፍላጎት ያላቸው አዳዲስ ነዋሪዎችን እናገኝ ይሆናል። ተቃዋሚ ወላጆች ያሏቸው ልጆች አድገው ራሳቸውን ችለው መኖር ይጀምራሉ። እነዚህ ሰዎች ደግሞ የመንግሥቱን መልእክት ለመስማት ፈቃደኛ ሊሆኑ ይችላሉ።
5. ሰዎች መልእክታችንን እንዲቀበሉ ሊያደርጓቸው የሚችሉ ምን ሁኔታዎች ይፈጠራሉ?
5 የሰዎች ባሕርይም ይለወጣል። ሐዋርያው ጳውሎስ በአንድ ወቅት “ተሳዳቢ፣ አሳዳጅና ዐመፀኛ” ነበር። (1 ጢሞ. 1:13) በተመሳሳይም በአሁኑ ጊዜ ይሖዋን የሚያገለግሉ ብዙ ሰዎች በአንድ ወቅት ለእውነት ፍላጎት ያልነበራቸው ናቸው። ምናልባትም አንዳንዶቹ በአንድ ወቅት ምሥራቹን ተቃውመው ሊሆን ይችላል። የዓለም ሁኔታዎች መለዋወጣቸው አንዳንድ ተቃዋሚዎች ወይም ግዴለሽ የነበሩ ሰዎች እኛን እንዲያዳምጡን ይገፋፋቸው ይሆናል። አንዳንዶች ደግሞ አንድ አሳዛኝ ሁኔታ ካጋጠማቸው ለምሳሌ ከቤተሰባቸው አባላት አንዱ ከሞተ፣ ከሥራቸው ከተፈናቀሉ፣ የኢኮኖሚ አሊያም የጤና ችግር ከደረሰባቸው በኋላ ለመልእክታችን ጥሩ ምላሽ ሊሰጡ ይችላሉ።
6. በቅንዓት መስበካችንን መቀጠል ያለብን ለምንድን ነው?
6 ይህ ሥርዓት ወደ መጠናቀቁ እየተቃረበ ቢሆንም የስብከቱና የማስተማሩ ሥራችን ወደፊት እየገፋ ነው። (ኢሳ. 60:22) በመሆኑም በቅንዓት መስበካችንንና አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ ጥረት ማድረጋችንን እንቀጥላለን። ቀጥሎ የምናነጋግረው ሰው መልእክታችንን ያዳምጥ ይሆናል። መናገራችንን መቀጠል ይኖርብናል! ‘ይህንንም በማድረግ ራሳችንንም ሆነ የሚሰሙንን እናድናለን።’—1 ጢሞ. 4:16