“የአገልግሎት ክልላችንን ደጋግመን ሸፍነናል!”
1 የአገልግሎት ክልላችሁ በተደጋጋሚ ከመሸፈኑ የተነሳ በግ መሰል ሰው እንደማይገኝበት ተሰምቷችሁ ያውቃል? ምናልባት ‘ሰዎች ምን እንደሚሉ አውቀዋለሁ። ፍላጎት ወደ ሌላቸው ሰዎች ለምን ደጋግሜ እሄዳለሁ?’ ብላችሁ ታስቡ ይሆናል። ብዙ የአገልግሎት ክልሎች በተደጋጋሚ የተሠራባቸው መሆኑ የማይካድ ነው። ይሁን እንጂ ይህን ሁኔታ አዎንታዊ በሆነ እንጂ አሉታዊ በሆነ መንገድ ልናየው አይገባም። ለምን? ቀጥሎ የቀረቡትን አራት ምክንያቶች ተመልከት።
2 ጸሎታችን መልስ አግኝቷል:- ኢየሱስ “መከሩስ ብዙ ነው፣ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ እንግዴህ የመከሩን ጌታ ለመከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት” ብሎ ነበር። (ሉቃስ 10:2) ተጨማሪ ሠራተኞች ለማግኘት ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ይሖዋን ስንለምን ቆይተናል። ዛሬ በብዙ ቦታዎች በቂ ቁጥር ያላቸው ተጨማሪ ሠራተኞች በመገኘታቸው የአገልግሎት ክልላችንን በተደጋጋሚ እየሸፈንን ነው። ይሖዋ ጸሎታችንን መስማቱ ሊያስደስተን አይገባም?
3 ጽናት መልካም ፍሬ ያስገኛል:- በተደጋጋሚ በተሠራባቸው የአገልግሎት ክልሎች ሳይቀር ሰዎች ለመንግሥቱ መልእክት በጎ ምላሽ በመስጠት ወደ እውነት እውቀት እየመጡ ነው። ስለሆነም ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች እንደምናገኝ ተስፋ በማድረግ ደጋግመን መሄድ ይገባናል። (ኢሳ. 6:8-11) ጥንት የነበሩት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንዳደረጉት ሁሉ ሌሎች ለአምላክ መንግሥት ያላቸውን ፍላጎት ለመቀስቀስ በአገልግሎት ክልላችሁ ውስጥ ወደሚገኙት ሰዎች ‘ደጋግማችሁ ሂዱ።’—ማቴ. 10:6, 7 NW
4 በፖርቱጋል ብዙ ጉባኤዎች በየሳምንቱ የአገልግሎት ክልላቸውን ይሸፍናሉ፤ ሆኖም አሁንም ቢሆን በግ መሰል ሰዎችን እያገኙ ነው። በተለይ አንዲት እህት ለየት ያለ አዎንታዊ አመለካከት አላት። ይህች እህት “ጠዋት ጠዋት አገልግሎት ከመሄዴ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የሚፈልግ ሰው ማግኘት እንድችል እንዲረዳኝ ወደ ይሖዋ እጸልያለሁ” ትላለች። አንድ ቀን ከፀጉር ቤት ሠራተኞች ጋር ጥናት ለመጀመር ዝግጅት አደረገች። ሆኖም በሌላ ቀን አንዷ ብቻ በጥናቱ ላይ ተገኘች። ይህች ሴት “ሌሎቹ ማጥናት አልፈለጉም፤ እኔ ግን እፈልጋለሁ” ብላለች። በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሴትየዋ ራሷ ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች መርታለች። ብዙም ሳትቆይ ተጠምቃ ከጊዜ በኋላ የአቅኚነት አገልግሎት ጀመረች!
5 ሥራው እየተሠራ ነው:- ኢየሱስ ይሆናል ብሎ በትንቢት እንደተናገረው ምሥራቹ በመሰበክ ላይ ነው። (ማቴ. 24:14) ‘እኛን መስማት በማይፈልጉባቸው’ ቦታዎች እንኳ በስብከቱ እንቅስቃሴ ማስጠንቀቂያ እየተሰጣቸው ነው። አንዳንዶች እንደማይቀበሉን አልፎ ተርፎ እውነትን እንደሚቃወሙ እንጠብቃለን። ሆኖም እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ስለ መጪው የይሖዋ የቅጣት ፍርድ የሚሰጠው ማስጠንቀቂያ ሊደርሳቸው ይገባል።—ሕዝ. 2:4, 5፤ 3:7, 8, 19
6 ገና አላበቃም:- የስብከቱ ሥራ መቼ ማቆም እንዳለበት የምንወስነው እኛ አይደለንም። የሚቆምበትን ትክክለኛ ጊዜ የሚያውቀው ይሖዋ ነው። እሱ በአገልግሎት ክልላችን ውስጥ ገና ለምሥራቹ በጎ ምላሽ የሚሰጡ ሰዎች መኖር አለመኖራቸውን ያውቃል። በዛሬው ጊዜ አንዳንድ ሰዎች ፍላጎት እንደሌላቸው ይናገራሉ። ሆኖም በሕይወታቸው ውስጥ ከሥራ መፈናቀል፣ ከባድ ሕመም፣ የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት የመሳሰሉ ድንገተኛ ለውጦች ሲያጋጥሟቸው በሌላ ጊዜ ምሥራቹን ይቀበሉ ይሆናል። ብዙ ሰዎች በጭፍን ጥላቻ ምክንያት ወይም ጊዜ ከማጣታቸው የተነሳ ምን እንደምንሰብክ እንኳ ፈጽሞ ሰምተው አያውቁም። የወዳጅነት መንፈስ በማሳየት በተደጋጋሚ ማነጋገሩ ትኩረት ሰጥተው እንዲያዳምጡ ያደርጋቸው ይሆናል።
7 ከቅርብ ዓመታት በፊት ልጆች የነበሩና አሁን አድገው የራሳቸውን ቤተሰብ የመሠረቱ ሰዎች ስለ ሕይወት በቁም ነገር ማሰብና ከአምላክ ቃል ውጪ መልስ የማይገኝላቸውን ጥያቄዎች መጠየቅ ይጀምራሉ። አንዲት ወጣት እናት ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤት እንዲገቡ ጋበዘቻቸውና እንዲህ አለች:- “ትንሽ ልጅ ሳለሁ የይሖዋ ምሥክሮች መናገር የሚፈልጉት ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ሆኖ ሳለ እናቴ ፍላጎት እንደሌላት ተናግራ ለምን እንደምትመልሳቸው አይገባኝም ነበር። አድጌ፣ ትዳር ይዤ የራሴን ቤተሰብ ከመሠረትኩ በኋላ ግን ወደ ቤት ገብተው መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያብራሩልኝ እጠይቃቸዋለሁ ብዬ ለራሴ ቃል ገብቼ ነበር።” የሚገርመው የይሖዋ ምሥክሮች ቤቷን ሲያንኳኩ ተግባራዊ ያደረገችው ይህንኑ በመሆኑ ምሥክሮቹ ተደስተዋል።
8 ይበልጥ ውጤታማ መሆን ትችል ይሆን? የአገልግሎት ክልላችንን በተደጋጋሚ መሸፈኑን አስቸጋሪ የሚያስመስለው የምናነጋግራቸው ሰዎች ብቻ ናቸው ማለት አይቻል ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ የችግሩ መንስዔ እኛው ራሳችን ነን። አፍራሽ አስተሳሰብ ይዘን አገልግሎት እንጀምራለንን? ይህ በስሜታችን፣ በድምፃችን ቃና እና ፊታችን ላይ በሚነበበው ስሜት ይገለጣል። አዎንታዊ መንፈስና ደስተኛ ፊት ይኑራችሁ። አዲስ አቀራረብ ለመጠቀም ሞክሩ። አቀራረባችሁን ለመለዋወጥ እንዲሁም ለማሻሻል ጥረት አድርጉ። ምናልባትም በመግቢያችሁ ላይ የምትጠቀሙበትን ጥያቄ መለወጥ ወይም በውይይቱ ጣልቃ ሌላ ጥቅስ መጠቀም ትችላላችሁ። ሌሎች ወንድሞችና እህቶች በአገልግሎት ክልላቸው ውስጥ ሲሠሩ ውጤታማ ሆኖ ያገኙት ነገር ምን እንደሆነ ጠይቋቸው። ከተለያዩ አስፋፊዎችና አቅኚዎች ጋር በማገልገል በአገልግሎት ውጤታማ ያደረጋቸው ምን እንደሆነ አስተውሉ።
9 የመንግሥቱ የስብከት ሥራ የይሖዋ ድጋፍና በረከት የማይለየው ሲሆን እኛም በሥራው ተሳትፎ ማድረጋችን ለይሖዋና ለጎረቤቶቻችን ፍቅር እንዳለን ያረጋግጣል። (ማቴ. 22:37-39) እንግዲያው በአገልግሎት ክልላችን ውስጥ ሳንታክት ደግመን ደጋግመን ከቤት ወደ ቤት በማገልገል እስከ መጨረሻው በሥራችን እንግፋ።