የግል የአገልግሎት ክልል ቢኖርህ ትጠቀማለህ
1. የግል የአገልግሎት ክልል ሲባል ምን ማለት ነው?
1 የግል የአገልግሎት ክልል ሲባል ምን ማለት ነው? ሰፊ የአገልግሎት ክልል ባለው ጉባኤ ውስጥ የምታገለግል ከሆነ ምናልባትም በመኖሪያህ አካባቢ የራስህን የአገልግሎት ክልል ትወስድ ይሆናል። የተደራጀ ሕዝብ የተባለው መጽሐፍ ገጽ 103 ላይ እንዲህ ይላል፦ “ለአንተ አመቺ የሆነ እንደዚህ ያለ የአገልግሎት ክልል ማግኘትህ በመስክ አገልግሎት የምታሳልፈውን ጊዜ በደንብ እንድትጠቀምበት ያስችልሃል። በተጨማሪም በአገልግሎት ክልልህ ውስጥ ሌላ አስፋፊ አብሮህ እንዲያገለግል ልትጋብዝ ትችላለህ።”
2. የግል የአገልግሎት ክልልህን ከቡድን ምሥክርነት በተጓዳኝ ልትጠቀምበት የምትችለው እንዴት ነው?
2 ከቡድን ምሥክርነት በተጓዳኝ፦ በመሥሪያ ቤትህ አካባቢ የግል የአገልግሎት ክልል ከወሰድክ በምሳ ሰዓት ወይም ወደ ቤት ስትመለስ ምናልባትም አቅራቢያህ ከሚሠራ ሌላ አስፋፊ ጋር ሆነህ ልታገለግል ትችላለህ። በቤትህ አቅራቢያ የሚገኝ ክልል ከወሰድክ ደግሞ ከቤተሰብህ ጋር ሆነህ ምሽት ላይ ለመመሥከር ልትጠቀምበት ትችላለህ። እርግጥ ነው፣ በመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ ላይ ካልተገኘህ መስበክ ከመጀመርህ በፊት የይሖዋን አመራር ለማግኘት መጸለይህ ተገቢ ነው። (ፊልጵ. 4:6) በተጨማሪም በግል የአገልግሎት ክልልህ ላይ መሥራትህ የመስክ አገልግሎት ቡድንህ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ከመካፈል ወደኋላ እንድትል ሊያደርግህ አይገባም። በተለይ በሳምንቱ መገባደጃ ላይ ቡድንህ የሚያደርገውን የስምሪት ስብሰባ መደገፍህ ተገቢ ነው።
3. የግል የአገልግሎት ክልል ወስዶ ማገልገል ምን ጥቅሞች አሉት?
3 ጥቅሞች፦ የግል የአገልግሎት ክልል ካለህ በተመቸህ ጊዜ ማገልገል የምትችልበት ቦታ አለህ ማለት ነው። በመሆኑም ረጅም መንገድ መጓዝ ስለማያስፈልግህ በስብከቱ ሥራ ረዘም ያለ ጊዜ ማሳለፍ ትችላለህ። ይህ ሁኔታ አንዳንዶች በረዳት ወይም በዘወትር አቅኚነት እንዲካፈሉ አስችሏቸዋል። የምታነጋግራቸው ሰዎች የሚኖሩት በቤትህ አቅራቢያ ስለሆነ ፍላጎት ካሳዩ ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግና ጥናት ማስጀመር ቀላል ይሆንልሃል። የግል የአገልግሎት ክልል ያላቸው ብዙ አስፋፊዎች በተለይ ክልሉን ከመመለሳቸው በፊት ከአንድ ጊዜ በላይ መሸፈናቸው ከቤቱ ባለቤቶች ጋር ለመቀራረብና የእነሱን አመኔታ ለማግኘት እንዳስቻላቸው ገልጸዋል። የግል የአገልግሎት ክልል ወስዶ መስበክ አንተም ሆንክ የቤተሰብህ አባላት አገልግሎታችሁን በተሟላ ሁኔታ ለመፈጸም ያስችላችሁ ይሆን?—2 ጢሞ. 4:5