በንግድ አካባቢዎች መስበክ የሚቻለው እንዴት ነው?
1 ሰዎች በአብዛኛው እንግዶችን በደስታ በሚቀበሉበትና ብዙዎች ቤታቸው በሚገኙበት አካባቢ መስበክ ያስደስትሃል? ከጉባኤህ ክልል ሳትወጣ እንደዚህ ማድረግ ትችል ይሆናል። እንዴት? በክልልህ ውስጥ በሚገኙት የንግድ ቦታዎች በመስበክ ነው። ብዙውን ጊዜ ኪዮስኮችንና የገበያ አዳራሾችን ጨምሮ በሱቆች ውስጥ የሚሰብኩ አስፋፊዎች ጥሩ ውጤቶች አግኝተዋል።
2 በአንዳንድ ጉባኤዎች የአገልግሎት ክልል ውስጥ የንግድ ቦታዎች ይገኛሉ። የክልል አገልጋይ የሆነው ወንድም ሰው በጣም ለሚበዛባቸው ለእነዚህ የንግድ አካባቢዎች ለየት ያለ የክልል ካርታ ሊያዘጋጅ ይችላል። በመኖሪያ አካባቢዎች የንግድ ቦታዎች በሚኖሩበት ጊዜ አስፋፊዎች የንግድ ቦታዎቹን ትተው መኖሪያ ቤቶቹን ብቻ ማንኳኳት እንዳለባቸው በአገልግሎት ክልል ካርታው ላይ በግልጽ ሊሠፍር ይገባል። በሌሎች ክልሎች ደግሞ የንግድ ቦታዎቹን ከመኖሪያ ቤቶቹ ጋር አብሮ ማንኳኳት ይቻል ይሆናል። በንግድ ቦታዎች አገልግለህ የማታውቅ ከሆነ አንዳንድ ትናንሽ ኪዮስኮችን በማንኳኳት ልትጀምር ትችላለህ።
3 ቀለል ያለ አቀራረብ ይኑርህ፦ በሱቆች ውስጥ ስናገለግል አለባበሳችን የሚያስከብር መሆን አለበት። ከዚህም በላይ ገበያተኞች የማይበዙበትን ሰዓት መምረጥ ያስፈልጋል። የሚቻል ከሆነ ሊስተናገዱ ተራ የሚጠብቁ ደንበኞች በሌሉበት ሰዓት ወደ ሱቁ መግባት ይመረጣል። በትላልቅ መደብሮች ውስጥ ሥራ አስኪያጁን ወይም ኃላፊነት የተሰጠውን ሰው ለማነጋገር እንደምትፈልግ ተናገር። መልእክትህ አጭርና ቀጥተኛ ይሁን። ምን ብለህ ልትጀምር ትችላለህ?
4 በሱቁ ውስጥ የሚሠራውን ሰው ወይም ሥራ አስኪያጁን በምታነጋግርበት ጊዜ እንዲህ ልትል ትችላለህ:- “ነጋዴዎች ሕይወታቸው በሥራ የተወጠረ በመሆኑ በአብዛኛው ቤታቸው አይገኙም። ወደ ሥራ ቦታችሁ የመጣሁት ለዚህ ነው። መጽሔቶቻችን በዓለም ዙሪያ የሚከናወኑ ወቅታዊ ጉዳዮችን ይዳስሳሉ።” ከዚያም ከአንድ መጽሔት ላይ አጠር ያለ ሐሳብ አሳየው።
5 ወይም ደግሞ የሚከተለውን ቀለል ያለ አቀራረብ ልትሞክር ትችላለህ:- “ብዙ ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የበለጠ ማወቅ ቢፈልጉም ጊዜ ግን የላቸውም። ይህ ትራክት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለተመሠረቱ ጥያቄዎችዎ መልስ ለማግኘት ስለሚያስችልዎት ነጻ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራም ይገልጻል።” ከዚያም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ ማወቅ ትፈልጋለህ? ከተባለው ትራክት ገጽ 4 እና 5 ላይ ያሉትን ነጥቦች አሳየው።
6 ባለሱቁ ሥራ የበዛበት ከመሰለህ አንድ ትራክት ከሰጠኸው በኋላ እንዲህ ልትለው ትችላለህ:- “ብዙም ሥራ በማይበዛብዎት ጊዜ ተመልሼ እመጣለሁ። ስለ ትራክቱ የሚሰማዎትን ሊነግሩኝ ይችላሉ።”
7 ፍላጎት ያሳዩትን ተመልሰህ ጠይቅ፦ በንግድ አካባቢዎች ጥናት መምራትም ትችል ይሆናል። አንድ ልዩ አቅኚ ለአንድ ነጋዴ አዘውትሮ መጽሔቶች ይወስድለት ነበር። ግለሰቡ ለሚያነባቸው ነገሮች አድናቆት እንዳለው ሲገልጽ አቅኚው አምላክ ከእኛ የሚፈልገው በተባለው ብሮሹር በመጠቀም መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት ማጥናት እንደሚቻል አሳየው። ሰውየው በሚሠራበት ቦታ ጥናት ተጀመረ። አቅኚው ሁኔታዎቹን ግምት ውስጥ በማስገባት ጥናቱ ከ10 ወይም ከ15 ደቂቃ በላይ እንዳይወስድ አደረገ። እኛም እንዲሁ በንግድ ቦታዎች በመስበክ ምስራቹ የሚገባቸውን ሰዎች መፈለጋችንን እንቀጥል።
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
1. በንግድ አካባቢዎች መስበክ ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
2. በንግድ ቦታዎች ለመስበክ ምን ዝግጅት ሊደረግ ይችላል?
3. በሱቆች ውስጥ በምናገለግልበት ጊዜ ውጤታማ እንድንሆን ምን ሊረዳን ይችላል?
4-6. ለባለሱቆች ወይም ለሥራ አስኪያጆች ስንመሰክር ምን ማለት እንችላለን?
7. በንግድ ቦታዎች ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ብናገኝ ምን ማድረግ እንችላለን?