በአገልግሎት ረገድ ክህሎታችንን ማዳበር—በንግድ አካባቢዎች መመሥከር
አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ብዙ ሰዎች ለረጅም ሰዓት ስለሚሠሩ የመንግሥቱን ምሥራች እንዲሰሙ ከተፈለገ ሥራ ቦታቸው ድረስ ሄደን መመሥከር ይኖርብናል። በንግድ አካባቢዎች መመሥከር አስደሳች ብሎም ውጤታማ ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም ሰዎች ቤታቸው ላይገኙ ይችላሉ ብለን አንሰጋም፤ ደግሞም ደንበኛቸው ልንሆን እንደምንችል በማሰብ አብዛኛውን ጊዜ በትሕትና ሊያነጋግሩን ይችላሉ። አስፋፊዎች ውጤታማ ለመሆን ከፈለጉ ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ መጠቀም እንዲሁም በአለባበሳቸውና በአጋጌጣቸው ምሳሌ መሆን አለባቸው። (2 ቆሮ. 6:3) በመሆኑም የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ ንግድ የሚካሄድባቸው ክልሎች ምን ያህል በተደጋጋሚ እንደተሠራባቸውና በእነዚህ ክልሎች ማን እንዳገለገለ መከታተል ይኖርበታል።
በዚህ ወር እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦
በቀጣዩ ጊዜ በምታደርጉት የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችሁ ላይ በንግድ አካባቢዎች ስታገለግሉ ልትጠቀሙበት የምትችሉትን አጠር ያለ አቀራረብ ተለማመዱ።