ያለማቋረጥ ተመልሰን የምንሄደው ለምንድን ነው?
1 ለዕለቱ ለምታደርገው አገልግሎት ዝግጅት እያደረግህ ሳለ ከላይ ያለውን ጥያቄ ራስህን ጠይቀህ ታውቃለህ? የአገልግሎት ክልላችን በተደጋጋሚ በተሠራባቸው አካባቢዎች ሲሆን የቤት ባለቤቶች በቀላሉ ስለሚለዩን ወዲያውኑ ፍላጎት እንደሌላቸው ይገልጹልናል። ጥቂት ሰዎች ጥሩ ምላሽ ይሰጡን ይሆናል። ሆኖም ያለማቋረጥ ከቤት ወደ ቤት እንድንሄድ የሚያደርጉን ብዙ ጠንካራ ምክንያቶች አሉ።
2 በመጀመሪያ ደረጃ መጨረሻው እስኪመጣ ድረስ የመንግሥቱን መልእክት መስበካችንን እንደንቀጥል ታዘናል። (ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20) ነቢዩ ኢሳይያስ የስብከት ሥራውን እስከ መቼ መቀጠል እንዳለበት ጠይቆ ነበር። የተሰጠው መልስ ኢሳይያስ 6:11 ላይ ተመዝግቦ ይገኛል። በተደጋጋሚ የአምላክን መልእክት ለሕዝቡ መናገርህን ቀጥል ተብሎ እንደተነገረው ምንም ጥርጥር የለውም። በተመሳሳይም ዛሬ ሰዎች ሊሰሙን እንደማይፈልጉ ቢናገሩም በአገልግሎት ክልላችን ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን ማነጋገራችንን እንድንቀጥል ይሖዋ ይጠብቅብናል። (ሕዝ. 3:10, 11) በአደራ የተሰጠን ቅዱስ ኃላፊነት ነው።— 1 ቆሮ. 9:17
3 ያለማቋረጥ ከቤት ወደ ቤት እንድንሄድ የሚያደርገን ሌላው ምክንያት ለይሖዋ የጠለቀ ፍቅር እንዳለን ለማሳየት አጋጣሚ የሚሰጠን መሆኑ ነው። (1 ዮሐ. 5:3) ከዚህም ሌላ የወደፊቱ ጊዜ ለሰው ዘሮች ምን እንደያዘላቸው በምናሰላስልበት ጊዜ ጎረቤቶቻችንን በፍቅር ከማስጠንቀቅ እንዴት ወደኋላ ልንል እንችላለን? (2 ጢሞ. 4:2፤ ያዕ. 2:8) የተሰጠንን ሥራ ለመፈጸም ታማኝ ሆነን መገኘታችን ለአምላክ የመዳን መልእክት ጥሩ ምላሽ እንዲሰጡ በተደጋጋሚ አጋጣሚ ይከፍትላቸዋል። በዚህም የተነሳ ማስጠንቀቂያው አልደረሰንም ብለው ለመናገር አይችሉም።— ሕዝ. 5:13
4 በተጨማሪም አንዳንድ ሰዎች መቼ የልብ ለውጥ እንደሚያደርጉ አናውቅም። በግል ሕይወታቸው ላይ የገጠማቸው አንድ ሁኔታ፣ በቤተሰባቸው ውስጥ የተከሰተ አሳዛኝ መከራ ወይም ስለ ወደፊቱ ጊዜ በጥንቃቄ እንዲያስቡ ያደረጋቸው የዓለም ሁኔታ ለውጥ አንዲያደርጉ ሊያደርጋቸው ይችላል። በሌላም በኩል በራቸው ላይ ሆነን የምንናገረው ነገር ያልተጠበቀ ጥሩ ውጤት ሊያመጣ ይችላል። (መክ. 9:11፤ 1 ቆሮ. 7:31) እንዲሁም ሰዎች የመኖሪያ ቦታቸውን ይቀያይራሉ። በአገልግሎት ክልላችን ውስጥ ለምሥራቹ ጥሩ ምላሽ የሚሰጡ ምናልባትም የመኖር ዓላማቸው ምን እንደሆነ አጥብቀው እያሰቡ ያሉ አሁን ራሳቸውን ችለው የሚኖሩ ወጣት አዳዲስ ነዋሪዎችን ልናገኝ እንችላለን።
5 ታዲያ ያለማቋረጥ ከቤት ወደ ቤት መሄድ ይኖርብናል? እንዴታ! ቅዱሳን ጽሑፎች ወደ ሰዎች ዘንድ ደግመን ደጋግመን እንድንሄድ በደግነት ማበረታቻ ይሰጡናል። በመጨረሻም የስብከቱ ሥራ ሲጠናቀቅ ይሖዋ በአገልግሎቱ ላደረግነው ያልተቋረጠ ጥረት ይባርከናል እንዲሁም የመንግሥቱን ምሥራች በአድናቆት የተቀበሉትን ሰዎች ሁሉ ይባርካቸዋል።— 1 ጢሞ. 4:16