የመንግሥቱ ስብከት ሥራ ሕይወት አድን ነው
1 በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ እየተከናወኑ ካሉት ሥራዎች ሁሉ የላቀ ነው። ይሖዋ አምላክ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሁም ስፍር ቁጥር የሌላቸው መላእክት ትኩረት ሰጥተው ይከታተሉታል። ይህ ሥራ ምንድን ነው? የግድ አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው? ሥራው የመንግሥቱ ስብከት ሲሆን ያን ያህል አስፈላጊ የሆነውም ሕይወት አድን ስለሆነ ነው!—ሮሜ 1:16፤ 10:13, 14
2 አንዳንዶች በዙሪያችን ያለውን ዓለም ለማሻሻል በሚደረጉ ጥረቶች ብንካፈል ሌሎችን በመርዳት ረገድ የበለጠ ማከናወን እንደምንችል ይሰማቸው ይሆናል። ብዙዎች ሰላም ለማምጣት፣ በሽታዎችን ለመፈወስ ወይም ኢኮኖሚን ለማሻሻል በሚደረጉ ጥረቶች ተጠምደዋል። ይሁን እንጂ ከሁሉ ይበልጥ ሰዎችን የሚጠቅመው የትኛው ሥራ ነው?
3 ከሁሉ የላቀ ሥራ:- የሕይወትን ዓላማ፣ በሰው ልጆች ላይ ሥቃይና መከራ የሚደርስበትን ምክንያት እንዲሁም ብቸኛው አስተማማኝ የወደፊት ተስፋ ምን እንደሆነ የሚያብራራው የመንግሥቱ መልእክት ብቻ ነው። ምሥራቹ ሰዎች የይሖዋ ወዳጆች እንዲሆኑና በዚህም ‘አእምሮን ሁሉ የሚያልፈውን የእግዚአብሔር ሰላም’ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። (ፊልጵ. 4:7) ሰዎች በአሁኑ ጊዜ በሕይወታቸው ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በተሳካ ሁኔታ ተቋቁመው እንዲያሸንፉ የሚያስችል ተግባራዊ መመሪያ የሚሰጠውና ክፉው ሥርዓት ወደፊት ሲጠፋ በሕይወት መትረፍ የሚቻልበትን መንገድ የሚያብራራው የመንግሥቱ መልእክት ብቻ ነው። (1 ዮሐ. 2:17) ታዲያ አቅማችን የፈቀደውን ያህል በመንግሥቱ የስብከት ሥራ ብንካፈል ተገቢ አይሆንም?
4 በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ ሊደረመስ በተቃረበ ግድብ አካባቢ የሚኖሩ በእንቅልፍ ላይ ያሉ የአንድን መንደር ነዋሪዎች ለመርዳት ከሁሉ የተሻለው አማራጭ ምንድን ነው? ከግድቡ ውኃውን እየቀዱ ማፍሰስ? አደጋ ያጠላበትን መንደር ማሳመር? በፍጹም! ነዋሪዎቹ ከእንቅልፋቸው ተቀስቅሰው እየቀረበ ስላለው አደጋ ሊነገራቸውና እንዲያመልጡ እርዳታ ሊደረግላቸው ይገባል! ዛሬም በመንፈሳዊ ሁኔታ ያንቀላፉ ሰዎች በጣም አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ። (ሉቃስ 21:34-36) ይህ የነገሮች ሥርዓት በቅርቡ ስለሚጠፋ የምንችለውን ያህል ለብዙ ሰዎች በጥድፊያ ስሜት ለመስበክ ጥረት እናድርግ!—2 ጢሞ. 4:2፤ 2 ጴጥ. 3:11, 12
5 በሥራው ጸንታችሁ ቀጥሉ፦ ቅን ልብ ያላቸውን ተጨማሪ ሰዎች በቤታቸው፣ በመንገድ ላይ፣ በስልክ እንዲሁም መደበኛ ባልሆነ መንገድ አግኝተን ምሥራቹን ለመንገር የምንችለውን ሁሉ እናድርግ። ይሖዋ እንድንሠራው የሰጠን ሥራ ልናከናውናቸው ከምንችላቸው ተግባራት ሁሉ የላቀ ነው። ይህንን ሥራ በቅንዓት ካከናወንን ‘ራሳችንንም የሚሰሙንንም እናድናለን’።—1 ጢሞ. 4:16