በጥድፊያ ስሜት ስበኩ!
1. በዛሬው ጊዜ ልብ ልንለው የሚገባን የትኛውን የጳውሎስ ምክር ነው?
1 “ቃሉን ስበክ፣ . . . በጥድፊያ ስሜት አገልግል።” (2 ጢሞ. 4:2) ጳውሎስ የሰጠው ምክር በዛሬው ጊዜ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ይህ ሐሳብ የእኛንም ሆነ የሌሎችን ሕይወት የሚነካው እንዴት ነው?
2. ምሥራቹን ያልሰሙ ሰዎችን ለማግኘት ትጋት የተሞላበት ጥረት የምናደርገው ለምንድን ነው?
2 የሕይወት ጉዳይ ነው፦ በዓለም ዙሪያ፣ መዳን የሚያስገኝላቸውን የምሥራች ገና ያልሰሙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። (ሮም 10:13-15፤ 1 ጢሞ. 4:16) ብዙ ጊዜ በተሠራባቸው ክልሎች ውስጥ በርካታ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች እየተገኙ ነው። ከቤት ወደ ቤት የምንሄድበትን ቀን ወይም ሰዓት ብንቀይር ቀደም ሲል ያላገኘነውን ሰው ልናገኝ እንችላለን። እንዲህ ያለ ትጋት የተሞላበት ጥረት ካደረግን ንጹሕ ሕሊና ይኖረናል እንዲሁም ከደም ዕዳ ነፃ እንሆናለን።—ሥራ 20:26
3. በአገልግሎት የምናሳልፈውን ጊዜ በጥበብ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው?
3 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ከባድ ተቃውሞ ቢደርስባቸውም ‘ኢየሩሳሌምን በትምህርታቸው ሞልተዋት’ ነበር። (ሥራ 5:28) እኛስ ልክ እንደ እነሱ “የተሟላ ምሥክርነት” ለመስጠት ቆርጠናል? (ሥራ 10:42) አገልግሎት ላይ ስንሆን ጊዜያችንን በጥበብ እንጠቀምበታለን? ከሁለት በላይ ሆነን እያገለገልን ከሆነና ሌሎቹ ተመላልሶ ሲያደርጉ መጠበቅ ካስፈለገን፣ በዚህ ጊዜ በመንገድ ላይ የሚያልፉ ሰዎችን ለማነጋገር ጥረት እናደርጋለን?
4. በጥድፊያ ስሜት መስበክ ምንጊዜም ነቅተን እንድንኖር የሚረዳን እንዴት ነው?
4 ንቁዎች እንድንሆን ያደርገናል፦ ይህ ሥርዓት የሚደመደምበት ጊዜ በጣም በመቅረቡ ምንጊዜም ነቅተን መኖር አለብን። (1 ተሰ. 5:1-6) ስለ መንግሥቱ ተስፋችን ዘወትር መናገራችን በዚህ ሥርዓት የኑሮ ውጣ ውረድ ከልክ በላይ እንዳንጨነቅ ይረዳናል። (ሉቃስ 21:34-36) በዚህ መንገድ የይሖዋን ቀን ‘በአእምሯችን አቅርበን ስንመለከት’ ሕይወት አድን በሆነው የስብከት ሥራ ላይ ያለንን ተሳትፎ ለመጨመር እንገፋፋለን።—2 ጴጥ. 3:11, 12
5. ለሕይወት ያለን አክብሮት በጥድፊያ ስሜት እንድናገለግል የሚያነሳሳን እንዴት ነው?
5 በጥድፊያ ስሜት ስንሰብክ ይሖዋ ለሕይወት ያለውን አመለካከት እናንጸባርቃለን። ይሖዋ “ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ እንጂ ማንም እንዲጠፋ [አይፈልግም]።” (2 ጴጥ. 3:9፤ ሕዝ. 33:11) እንግዲያው ለይሖዋ ውዳሴ ማምጣት እንድንችል በክልላችን ውስጥ በተቻለን መጠን ብዙ ሰዎችን ለማግኘት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ!—መዝ. 109:30