እምነታችን ለመልካም ሥራ ያነሳሳናል
1 ኖኅን፣ ሙሴንና ረዓብን ለድርጊት ያነሳሳቸው እምነት ነው። ኖህ መርከብ ሠርቷል። ሙሴ በፈርዖን ቤተ መንግሥት ውስጥ መኖር የሚያስገኛቸውን ጊዜያዊ ጥቅሞች ትቷል። ረዓብ ሰላዮቹን ደብቃለች፤ ከዚያም ትእዛዛቸውን በመጠበቅ የቤተሰቧን ሕይወት አድናለች። (ዕብ. 11:7, 24-26, 31) በዛሬው ጊዜስ እምነታችን የሚያነሳሳን ምን ዓይነት መልካም ሥራዎችን እንድንሠራ ነው?
2 መመሥከር፦ እምነት ታላቅ ስለሆነው አምላካችንና ዘላለማዊ ደስታ እንድናገኝ ሲል ስላደረጋቸው ዝግጅቶች እንድንናገር ይገፋፋናል። (2 ቆሮ. 4:13) አንዳንድ ጊዜ ከመመሥከር ወደ ኋላ እንል ይሆናል። ይሁን እንጂ ‘ሁልጊዜ ይሖዋ የሚታየን’ ከሆነ ጥንካሬ እናገኛለን፤ ፍርሃታችንም ሁሉ ይጠፋል። (መዝ. 16:8) በዚህ መንገድ እምነታችን ተስማሚ ሆኖ ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ለዘመዶቻችን፣ ለጎረቤቶቻችን፣ ለሥራ ባልደረባዎቻችን፣ አብረውን ለሚማሩትና ለሌሎችም ምሥራቹን እንድናካፍል ይገፋፋናል።—ሮሜ 1:14-16
3 አብሮ መሰብሰብ፦ ከእምነት የሚመነጨው ሌላው መልካም ሥራ አዘውትሮ በስብሰባ ላይ መገኘት ነው። እንዴት? በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘታችን ኢየሱስ በአምላክ ቅዱስ መንፈስ አማካኝነት በመካከላችን እንደሚሆን ያለንን ጽኑ እምነት ያሳያል። (ማቴ. 18:20) “መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን” መስማት እንደምንፈልግ ያሳያል። (ራእይ 3:6) እያስተማረን ያለው ታላቁ አስተማሪያችን ይሖዋ መሆኑን በእምነት ዓይናችን ስለምንመለከት የሚሰጠንን ትምህርት በቁም ነገር እንመለከተዋለን።—ኢሳ. 30:20
4 የምናደርጋቸው ውሳኔዎች፦ በዓይናችን ስለማናያቸው ነገሮች ያለን ጽኑ እምነት በሕይወታችን ውስጥ ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ እንድንሰጥ ይገፋፋናል። (ዕብ. 11:1) ይህ አብዛኛውን ጊዜ ቁሳዊ ጥቅማችንን መሥዋዕት ማድረግን ይጠይቃል። ለምሳሌ ያህል አንድ ሽማግሌ ከስብሰባዎች እንዲቀር፣ ከቤተሰቡ እንዲራራቅና የአቅኚነት አገልግሎቱን እንዲያቋርጥ የሚያደርገው ሆኖ ስላገኘው በሰብዓዊ ሥራው የደረጃ እድገት ሊያሰጠው የሚችለውን አጋጣሚ ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። እኛም በተመሳሳይ ‘መንግሥቱንና ጽድቁን ማስቀደማቸውን’ ለሚቀጥሉ ሁሉ ይሖዋ የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንደሚያሟላላቸው መጽሐፍ ቅዱስ በሚሰጠው ማረጋገጫ ላይ ሙሉ እምነት ይኑረን።—ማቴ. 6:33
5 እምነት በሕይወታችን ላይ ምን ያህል በጎ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ሌሎችም መመልከታቸው አይቀርም። ደግሞም እምነታችን በዓለም ዙሪያ የታወቀ ነው። (ሮሜ 1:8) እንግዲያውስ ሁላችንም ሕያው የሆነ እምነት እንዳለን በመልካም ሥራዎቻችን እናሳይ።—ያዕ. 2:26