ጥናት ለማስጀመር አምላክ ከእኛ የሚፈልገው በተባለው ብሮሹር እየተጠቀምክ ነው?
1 ፍላጎት ያለው አንድ ሰው አግኝተህ አዘውትረህ በመሄድ ቅደም ተከተሉን በጠበቀ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጠናት ከተዘጋጁት ጽሑፎች ለጥቂት ደቂቃም ቢሆን የምታወያየው ከሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እየመራህለት እንደሆነ ታውቃለህ? ጥናቱ የተከናወነው በር ላይ ቆማችሁም ሆነ በስልክ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተብሎ ሪፖርት ይደረጋል። በግንቦትና በሰኔ ወር አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለውን ብሮሹር ተጠቅመህ ይህን ዓይነት ጥናት ለማስጀመር ለምን ጥረት አታደርግም?
2 ውጤት ለማግኘት ዝግጅት አድርግ፦ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለውን ብሮሹር ስታበረክት በምን ርዕሰ ጉዳይ ላይ መወያየት እንደምትፈልግ አስቀድመህ አስብ። ተመላልሶ መጠየቅ የምታደርግ ከሆነ በመጀመሪያው ጉብኝትህ ወቅት ያደረጋችሁትን ውይይት አስታውስ። ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ:- ‘ባለፈው ያደረግነውን ውይይት ለመቀጠልና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር የሚያስችሉኝ የብሮሹሩ አንቀጾች የትኞቹ ናቸው?’ ከቤት ወደ ቤት የምታገለግል ከሆነ በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ለሚገኝ ልጅ፣ በእድሜ ለገፉ ሰዎች፣ ለወንዶች ወይም ለሴቶች ተስማሚ ሊሆን የሚችለው የትኛው ርዕስ እንደሆነ አስብ። በብሮሹሩ ውስጥ የቀረቡትን ርዕሶች ከልስና ትኩረታቸውን ሊስብ የሚችል ርዕሰ ጉዳይ ምረጥ። ምን ዓይነት አቀራረብ እንደምትጠቀም ከወሰንክ በኋላ በተደጋጋሚ ተለማመደው። ይህ ውጤታማ ለመሆን ከሚያስችሉት ቁልፎች መካከል አንዱ ነው።
3 የጥር 2002 የመንግሥት አገልግሎታችን አባሪ “አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለውን ብሮሹር ለማስተዋወቅ የሚረዱ” ስምንት አቀራረቦችን ይዟል። “ቀጥተኛ አቀራረብ” የሚለው ሣጥን ብሮሹሩን ተጠቅሞ ጥናት ማስጀመር የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ይጠቁማል። የመጀመሪያውን አቀራረብ ተስማሚ ጥያቄዎች በማንሳት በሚከተለው መንገድ ልትጠቀምበት ትችል ይሆናል:-
◼ “ጥቂት ደቂቃዎችን ብቻ መሥዋዕት በማድረግ አስፈላጊ ለሆነ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄ መልስ ማግኘት እንደሚችሉ ያውቃሉ? ለምሳሌ ያህል ዛሬ ክርስቲያን ነን የሚሉ ብዙ ሃይማኖቶች ያሉት ለምንድን ነው? ስለዚህ ጉዳይ አስበው ያውቃሉ?” ሰውዬው መልስ ከሰጠህ በኋላ ትምህርት 13ን አውጣና የመጀመሪያዎቹን ሁለት አንቀጾች ተወያዩባቸው። ጊዜ በፈቀደልህ መጠን አንድ ወይም ሁለት ጥቅሶችን አንብብና በጥቅሶቹ ላይ ተወያዩ። ከዚያም በገጹ አናት ላይ ከሚገኙት ጥያቄዎች የመጨረሻውን አንብብና እንዲህ በል:- “የትምህርቱ ቀሪ አንቀጾች እውነተኛው ሃይማኖት ተለይቶ የሚታወቅባቸውን አምስት ነጥቦች ያብራራሉ። በሌላ ጊዜ ተመልሼ መጥቼ አብረን ብንወያይባቸው ደስ ይለኛል።”
4 ሳታሰልስ ጥረት አድርግ፦ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው በተባለው ብሮሹር አማካኝነት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዴት እንደሚካሄድ ለሰዎች ለማሳየት እያንዳንዱን አጋጣሚ ተጠቀምበት። ይሖዋ እንዲባርክህ ጸልይ። (ማቴ. 21:22) በጥረትህ ከገፋህበት ሰዎች ለምሥራቹ ቀና ምላሽ እንዲሰጡ መርዳት የሚያስገኘውን ደስታ ልታጣጥም ትችላለህ!