እንደ አንድ አካል ተባብራችሁ ሥሩ
1 ድንቅ የሆነው የሰው ልጅ አካል አፈጣጠር አያስገርምህም? (መዝ. 139:14) እያንዳንዱ የሰውነት ክፍል ከሌሎቹ ክፍሎች ጋር ተባብሮ ይሠራል። የአምላክ ቃል የክርስቲያን ጉባኤን በሚገባ ተቀናጅቶ ከሚሠራ አካል ጋር ያመሳስለዋል። ራስ በሆነው በክርስቶስ አመራር ሥር ያሉት ሁሉም የጉባኤው አባላት ‘በተሰጠለት በጅማት ሁሉ እየተጋጠመና እየተያያዘ በልክ እንደሚሠራ’ የሰው አካል ናቸው። (ኤፌ. 4:16) በመሆኑም ይሖዋ አንድነት ያለውን ሕዝቡን በመጠቀም ድንቅ ነገሮችን ማከናወን ይችላል።
2 የመጀመሪያው መቶ ዘመን ጉባኤ አባላት አንዳቸው የሌላውን መንፈሳዊና ሰብዓዊ ፍላጎት ለማሟላት “በአንድ ልብ” ይሠሩ ነበር። (ሥራ 2:44-47) በይሖዋ እርዳታ በመታገዝ የሚደርስባቸውን ከባድ ተቃውሞ አንድ ላይ ሆነው መጋፈጥና ማሸነፍ ችለዋል። (ሥራ 4:24-31) በሄዱበት ሁሉ የመንግሥቱን መልእክት በማወጅ ምሥራቹ ያን ጊዜ በነበረው ዓለም በሙሉ እንዲዳረስ አድርገዋል። (ቆላ. 1:23) በዘመናችንም የክርስቲያን ጉባኤ በአንድነት ይህንኑ ሥራ በስፋት አከናውኗል። ይህ አንድነት ሊገኝ የቻለው እንዴት ነው?
3 በመለኮታዊ ትምህርት አንድ መሆን፦ በዓለም ዙሪያ የአምልኮ አንድነት አለን። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? ይሖዋ መንፈሳዊ ‘ምግብ በጊዜው’ ለማቅረብ የሚጠቀምበትን ምድራዊ የመገናኛ መስመር አውቀናል። (ማቴ. 24:45) እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ እንዲያስተምሩን ‘ስጦታ አድርጎ የሰጠንን ወንዶች’ [NW ] እናደንቃለን። ይሖዋ እኛን በመንፈሳዊ ለመመገብ ያደረገውን ዝግጅት በትሕትና ስንቀበል ስለ አምላክ ቃል ያለን እውቀት እያደገ ይሄዳል፤ ይህም ልክ እንደ ደቀ መዛሙርቱ እኛም ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ የመከተል ፍላጎት በውስጣችን እንድናዳብር ይገፋፋናል። “በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት” ለመድረስ የአምላክን ቃል በትጋት ማጥናታችንን መቀጠል አለብን። (ኤፌ. 4:8, 11-13) መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ በማንበብ መንፈሳዊ አንድነታችን እንዲዳብር የበኩልህን አስተዋጽኦ እያደረግህ ነው?
4 በክርስቲያናዊ ስብሰባ አንድ መሆን፦ ፍቅር በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የጠበቀ ወዳጅነት እንድንመሠርት ያደርገናል። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ‘እርስ በእርስ እንተያያለን።’ (ዕብ. 10:24, 25) ይህ ከውጫዊ ገጽታቸው አልፈን ወንድሞቻችንን በሚገባ ማወቅንና ይሖዋ እነሱን በሚመለከታቸው መንገድ ማለትም እንደ ውድ ነገር አድርገን መመልከትን ይጨምራል። (ሐጌ 2:7) እምነታቸውን ሲገልጹ ስንሰማ ለእነሱ ያለን ፍቅር ይጨምራል፣ አንድነታችንም ይጠናከራል። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አዘውታሪ ተሰብሳቢ መሆንህ ይታወቃልን?
5 በአገልግሎት አንድ ላይ መሥራት፦ ከእምነት ባልደረቦቻችን ጋር ምሥራቹን መስበክ የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ረገድ አንድ ያደርገናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘በእግዚአብሔር መንግሥት ከእሱ ጋር አብረው ይሠሩ’ የነበሩትን ባልደረቦቹን ይወዳቸው ነበር። (ቆላ. 4:10, 11) በአገልግሎት ላይ ስንሆን ተሞክሮዎችን መለዋወጣችንና መተጋገዛችን የተሰጠንን ክርስቲያናዊ ተልዕኮ ለመፈጸምና አንድነታችንን ለማጠናከር ይረዳል።—ቆላ. 3:14
6 መንፈስ ቅዱስ አንድ ያደርገናል፦ የአምላክን ፈቃድ በትጋት ስንፈጽም ይሖዋ መንፈሱን በመስጠት ይባርከናል። ይህም አለመግባባቶችን ለመፍታትና በአንድነት አብረን እንድንኖር ያስችለናል። (መዝ. 133:1) ‘በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ እንድንተጋ’ ያነሳሳናል። (ኤፌ. 4:3) እርስ በእርስ ባለን ግንኙነት የመንፈስ ፍሬዎችን በማፍራት በአምላክ ሕዝቦች መካከል ያለው አንድነት ይበልጥ እንዲጠናከር ሁላችንም የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ እንችላለን።—ገላ. 5:22, 23
7 በክርስቶስ አመራር ሥር ሆኖ በአንድነት ማገልገል እያንዳንዱ ክፍል ‘ራሱን በፍቅር ለማነጽ አካሉን እንዲያሳድግ’ ያደርጋል። (ኤፌ. 4:16) ከዚህም በላይ “የሰላም አምላክ” የሆነውን ይሖዋን ያስመሰግናል።—ሮሜ 16:20