የቅርብ ዘመድ ሲወገድ ክርስቲያናዊ ታማኝነት አሳዩ
1. አንድ ክርስቲያን ታማኝነቱ በምን ሊፈተን ይችላል?
1 በቤተሰብ አባላት መካከል ያለው ትስስር በጣም የጠበቀ ነው። ይህም አንድ ክርስቲያን የትዳር ጓደኛው፣ ልጁ፣ ወላጁ ወይም ሌላ የቅርብ ዘመዱ ሲወገድ ወይም ራሱን ከጉባኤው ሲያገልል ፈተና ይሆንበታል። (ማቴ. 10:37) ታማኝ ክርስቲያኖች እንዲህ ካለው ዘመድ ጋር ሊኖራቸው የሚገባው ግንኙነት ምን ዓይነት ነው? ግለሰቡ በቤታችሁ የሚኖር ቢሆን ልዩነት ያመጣል? በመጀመሪያ መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን እንደሚል እንመልከት። ይህን በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈሩት መሠረታዊ ሥርዓቶች ለተወገዱም ሆነ ራሳቸውን ላገለሉ ሰዎች በእኩል ደረጃ ይሠራሉ።
2. በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ክርስቲያኖች ከጉባኤ የተወገዱ ሰዎችን መመልከት የሚኖርባቸው እንዴት ነው?
2 ከተወገዱ ሰዎች ጋር ሊኖረን የሚገባው ግንኙነት ምን ዓይነት ነው? ክርስቲያኖች ከጉባኤ ከተወገደ ሰው ጋር ጓደኝነት ወይም ወዳጅነት እንዳይመሠርቱ የአምላክ ቃል እንዲህ በማለት ያዛቸዋል:- “ወንድሞች ከሚባሉት አንዱ ሴሰኛ ወይም ገንዘብን የሚመኝ ወይም ጣዖትን የሚያመልክ ወይም ተሳዳቢ ወይም ሰካር ወይም ነጣቂ ቢሆን ከእርሱ ጋር እንዳትተባበሩ እጽፍላችኋለሁ፤ እንደነዚህ ካለው ጋር መብል እንኳን አትብሉ። . . . ክፉውን ከመካከላችሁ አውጡት።” (1 ቆሮ. 5:11, 13) በማቴዎስ 18:17 ላይ ተመዝግበው የሚገኙት “እንደ አረመኔና [“አሕዛብ፣” አ.መ.ት ] እንደ ቀራጭ ይሁንልህ” የሚሉት የኢየሱስ ቃላትም ለዚህ ሐሳብ ተጨማሪ ድጋፍ ይሰጣሉ። የኢየሱስ አድማጮች በወቅቱ የነበሩት አይሁዳውያን ከአሕዛብ ጋር እንደማይወዳጁና ቀረጥ ሰብሳቢዎችን እንደሚያገልሏቸው አበክረው ያውቁ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ ተከታዮቹን ከተወገዱ ሰዎች ጋር ምንም ዓይነት ቅርርብ እንዳይፈጥሩ እያስተማራቸው ነበር።—መጠበቂያ ግንብ 9-102 ገጽ 9ና 10ን (የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ መስከረም 15, 1981 ገጽ 18-20ን) ተመልከት።
3, 4. ከተወገደና ራሱን ካገለለ ሰው ጋር ምን ዓይነት ቅርርብ መመሥረት የለብንም?
3 ይህ ማለት ታማኝ የሆኑ ክርስቲያኖች ከጉባኤ ከተወገደ ከማንኛውም ግለሰብ ጋር ምንም ዓይነት መንፈሳዊ ግንኙነት አይኖራቸውም ማለት ነው። ይሁን እንጂ ጉዳዩ በዚህ ብቻ አያበቃም። የአምላክ ቃል ‘እንደዚህ ካለው ጋር መብል እንኳን መብላት’ እንደሌለብን ይናገራል። (1 ቆሮ. 5:11) ስለዚህ ከተወገደ ሰው ጋር ማኅበራዊ ግንኙነታችንንም ጭምር እናቋርጣለን ማለት ነው። በሌላ አባባል ከተወገደው ሰው ጋር ሽርሽር አንሄድም፣ ግብዣ ላይ አንገኝም፣ ኳስ አንጫወትም፣ ወደ ገበያ ወይም ወደ ቲያትር ቤት አብረን አንሄድም እንዲሁም በቤትም ሆነ በምግብ ቤት አብረን አንመገብም ማለት ነው።
4 ከተወገደ ሰው ጋር መነጋገርን በተመለከተስ? መጽሐፍ ቅዱስ እያንዳንዱን ሁኔታ እየጠቀሰ መመሪያ ባይሰጥም በ2 ዮሐንስ 10 ላይ ያለው ሐሳብ ይሖዋ ስለ ጉዳዩ ያለውን አመለካከት እንድናውቅ ይረዳናል። “ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ ይህንም ትምህርት ባያመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት ሰላምም አትበሉት።” ይህን በተመለከተ መጠበቂያ ግንብ 9-102 ገጽ 13 (የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ መስከረም 15, 1981 ገጽ 25) ላይ እንዲህ ይላል:- “አጭር የሰላምታ ቃል ወደ ሌላ ንግግር ወይም ወደ ጓደኝነት የሚመራ የመጀመሪያ እርምጃ ነው። የተወገደን ሰው ሰላም በማለት ይህንን የመጀመሪያ እርምጃ ለመውሰድ እንፈልጋለንን?”
5. አንድ ሰው ሲወገድ ምን ነገሮችን ያጣል?
5 በዚሁ መጠበቂያ ግንብ ገጽ 16 (በእንግሊዝኛው መጠበቂያ ግንብ ገጽ 31) ላይ የሚከተለው ሐሳብ ተጠቅሷል:- “አንድ ክርስቲያን በኃጢአት ቢሸነፍና ቢወገድ ብዙ ነገር ያጣል። [በአምላክ] ፊት የነበረውን ጥሩ አቋም፣ . . . ከወንድሞች ጋር አስደሳች ጊዜ የማሳለፍ መብቱንና ከክርስቲያን ዘመዶቹ ጋር የነበረውን ብዙውን ግንኙነት ያጣል።”
6. አንድ ክርስቲያን በአንድ ጣሪያ አብሮት ከሚኖር ከተወገደ ዘመዱ ጋር ያለውን ማንኛውንም ዓይነት ግንኙነት እንዲያቋርጥ ይጠበቅበታል? አብራራ።
6 በአንድ ቤት ውስጥ አብሮ የሚኖር ከሆነ፦ እንዲህ ሲባል ከተወገደ የቤተሰባቸው አባል ጋር በአንድ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ከእርሱ ጋር መነጋገር፣ አብሮ መብላትና ዕለታዊ እንቅስቃሴዎቻቸውን በጋራ ማከናወን የለባቸውም ማለት ነው? በሚያዝያ 15, 1991 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 22 ላይ ያለው የግርጌ ማስታወሻ እንዲህ ይላል:- “በክርስቲያን ቤት ውስጥ አንድ የተወገደ ዘመድ ካለ በተለመዱት የዕለት ተዕለት ግንኙነቶችና እንቅስቃሴዎች ተካፋይ ሆኖ ይቀጥላል።” ሆኖም የተወገደው የቤተሰቡ አባል አብሯቸው ምግብ መመገብ ወይም በሌሎች የቤት ውስጥ እንቅስቃሴዎች ውስጥ መካፈል የሚችለው እስከ ምን ድረስ እንደሆነ የመወሰኑ ኃላፊነት ለቤተሰቡ አባላት የተተወ ነው። ሆኖም ለቤተሰቡ ቅርበት ያላቸው ወንድሞች ቤተሰቡ ከግለሰቡ ጋር ባለው ግንኙነት ረገድ ምንም ለውጥ እንዳላደረገ እስኪሰማቸው ድረስ ግለሰቡ ከመወገዱ በፊት የነበራቸው ዓይነት ቅርርብ ይዘው ለመቀጠል አይፈልጉም።
7. አንድ የቤተሰብ አባል ሲወገድ በቤቱ ውስጥ የነበረው መንፈሳዊ ግንኙነት የሚለወጠው እንዴት ነው?
7 ይሁን እንጂ መጠበቂያ ግንብ 9-102 ገጽ 15 (የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ መስከረም 15, 1981 ገጽ 28) ላይ የተወገደን ወይም ራሱን ያገለለን ግለሰብ በሚመለከት እንዲህ ይላል:- “[በ]ፊት ከርሱ ጋር የነበረው መንፈሳዊ ግንኙነት ሁሉ ተቆርጧል። ይህ አባባል ለዘመዶቹና በቤተሰቡ ክልል ውስጥ ላሉትም ይሠራል። . . . ይህም ሲባል ከዚያ በፊት በቤቱ ውስጥ የነበረው መንፈሳዊ ግንኙነት ይለወጣል ማለት ነው። ለምሳሌ ባልየው ከተወገደ ሚስቱና ልጆቹ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ወይም ጸሎት እንዲያደርግላቸው ሊስማሙ አይችሉም። እቤቱ ውስጥ ለመጸለይ ከፈለገ (ለምሳሌ በምግብ ጊዜ) መብት አለው። ሚስቱና ልጆቹ ግን በልባቸው ወደ [አምላክ] ሊጸልዩ ይችላሉ። (ምሳሌ 28:9፤ መዝ. 119:145, 146) ቤተሰቡ መጽሐፍ ቅዱስ ለማንበብ ወይም ለማጥናት ሲሰበሰብ የተወገደው ሰው አብሮአቸው ሊሆን ቢፈልግስ? እነርሱን ለማስተማር ወይም ሃይማኖታዊ አስተሳሰቡን ወደ እነርሱ ለማስተላለፍ የማይሞክር ከሆነ ቁጭ ብሎ እንዲያዳምጥ ሊፈቅዱለት ይችላሉ።”
8. ክርስቲያን ወላጆች በቤታቸው ውስጥ የሚኖር ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅ ሲወገድ እርሱን በተመለከተ ምን ኃላፊነት አለባቸው?
8 በቤት ውስጥ የሚኖር አንድ ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅ ቢወገድ ክርስቲያን ወላጆች እርሱን ተንከባክቦ የማሳደግ ኃላፊነት አለባቸው። መጠበቂያ ግንብ 22-109 ገጽ 20 (የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ኅዳር 15, 1988 ገጽ 20) ላይ እንዲህ ይላል:- “ለእርሱ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ማቅረባቸውን እንደሚቀጥሉ ሁሉ እርሱን በአምላክ ቃል ማስተማርና መገሠጽም ያስፈልጋቸዋል። (ምሳሌ 6:20-22፤ 29:17) አፍቃሪ የሆኑ ወላጆች ልጁ የተወገደ ቢሆንም እንኳን ከእርሱ ጋር የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማድረግ ዝግጅት ያደርጋሉ። ምናልባትም ለብቻቸው ከእርሱ ጋር [በ]ማጥናታቸው እርሱ አስፈላጊውን እርማት በማግኘት ይጠቀም ይሆናል። ወይም በቤተሰቡ የጥናት ዝግጅት ላይ መካፈሉን ለመቀጠል እንደሚችል ይወስኑ ይሆናል።”—በተጨማሪም የጥቅምት 1, 2001 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 16-17ን ተመልከት።
9. ክርስቲያኖች ከቤት ውጭ ከሚኖር የተወገደ ዘመዳቸው ጋር ሊኖራቸው የሚገባው ግንኙነት እስከምን ድረስ ነው?
9 የተወገደው ዘመድ በሌላ ቤት የሚኖር ከሆነ፦ መጠበቂያ ግንብ 8-109 ገጽ 18 (የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ሚያዝያ 15, 1988 ገጽ 28) ላይ እንዲህ ይላል:- “የተወገደው ወይም የተገለለው ሰው ከቤተሰቡ ክልልና ከቤቱ ውጭ የሚኖር ዘመድ ከሆነ ሁኔታው የተለየ ነው። ከዚህ ዘመድ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ላለማድረግ ይቻል ይሆናል። መገናኘት የሚጠይቁ አንዳንድ የቤተሰብ ጉዳዮች ቢኖሩም እንኳን” ንስሐ ሳይገባ ኃጢአት መሥራቱን ከሚቀጥል ከማንም ሰው ‘ጋር እንዳንተባበር’ ከሚያዘው “መለኮታዊ ሥርዓት ጋር በመስማማት በጣም መጥበብ ይኖርበታል።” (1 ቆሮ. 5:11) ታማኝ ክርስቲያኖች ከእንዲህ ዓይነቱ ዘመድ ጋር አላስፈላጊ የሆኑ ግንኙነቶችን ማስወገድና ሌላው ቀርቶ የንግድ ጉዳዮችን እንኳን በጣም መቀነስ ይኖርባቸዋል።—በተጨማሪም መጠበቂያ ግንብ 9-102 ገጽ 15ና 16 (የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ መስከረም 15, 1981 ገጽ 29-30) ተመልከት።
10, 11. አንድ ክርስቲያን የተወገደ ዘመዱ ወደ ቤት ተመልሶ እንዲገባ ከመፍቀዱ በፊት ምን ነገሮችን ያመዛዝናል?
10 መጠበቂያ ግንብ 9-102 ገጽ 15 ላይ (የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ መስከረም 15, 1981 ገጽ 28-29) ሊያጋጥም የሚችል ሌላ ሁኔታን በተመለከተ እንዲህ ይላል:- “ነገር ግን አንድ የቅርብ ዘመድ ለምሳሌ በቤት ውስጥ አብሮ የማይኖር ልጅ ወይም ወላጅ ቢወገድና ወደ ቤቱ ተመልሶ አብሮ ለመኖር ቢፈልግስ? ቤተሰቡ እንደ ሁኔታው ሊወስን ይችላል። ለምሳሌ የተወገደ ወላጅ ሊታመም ይችላል። ገንዘብ ወይም የሰውነቱ ሁኔታ ራሱን ችሎ እንዲኖር ላይፈቅድለት ይችላል። ክርስቲያን ልጆቹ እርሱን ለመርዳት ቅዱስ ጽሑፋዊና ሞራላዊ ግዴታ አለባቸው። (1 ጢሞ. 5:8) . . . ውሳኔው በተለያዩ ሁኔታዎች ላይ የተመካ ነው። ለምሳሌ የሰውየው እውነተኛ ችግር፣ ዝንባሌውና የቤተሰቡ ራስ ስለ ቤተሰቡ መንፈሳዊ ደህንነት ያለው አሳቢነት ለሚወሰደው እርምጃ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።”
11 የተወገደ ልጅን በሚመለከት ደግሞ ይኸው መጠበቂያ ግንብ እንዲህ ይላል:- “አንዳንድ ጊዜ ክርስቲያን ወላጆች የአካል ወይም የአእምሮ ሕመም ያደረበትን የተወገደ ልጃቸው ለጊዜው ወደ ቤታቸው እንዲመጣ ፈቅደዋል። ይሁንና እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ በሚያጋጥምበት ጊዜ ወላጆች ሁኔታውን ሊያመዛዝኑ ይችላሉ። የተወገደው ሰው ራሱን ችሎ ይኖር ነበርን? አሁንስ በራሱ መኖር ያቅተዋልን? ወይስ ወደ ወላጆቹ ለመመለስ የፈለገበት ዋና ምክንያት ምቾት ለማግኘት ብሎ ነው? ሥነ ምግባሩና ዝንባሌውስ እንዴት ነው? ወደ ቤቱ ‘እርሾ’ ያመጣ ይሆን?—ገላ. 5:9”
12. ውገዳ ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
12 ለይሖዋ ታማኝ መሆን የሚያስገኛቸው ጥቅሞች፦ ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞችን እንድናስወግድና ከእነርሱ እንድንርቅ የሚያዘውን ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያ መከተል ጠቃሚ ነው። የጉባኤው ንጽሕና እንዲጠበቅ ከማድረጉም በላይ የመጽሐፍ ቅዱስን የላቁ የሥነ ምግባር ደረጃዎች የምንጠብቅ መሆናችንን ለይቶ ያሳውቃል። (1 ጴጥ. 1:14-16) ሊበክሉ ከሚችሉ ተጽዕኖዎች ይጠብቀናል። (ገላ. 5:7-9) እንዲሁም ኃጢአት የሠራው ሰው ከተሰጠው ተግሳጽ ሙሉ ጥቅም እንዲያገኝ የሚያስችለው ሲሆን ይህም ‘የሰላምን ፍሬ ማለትም ጽድቅን’ እንዲያፈራ ይረዳዋል።—ዕብ. 12:11
13. አንድ ቤተሰብ ምን ማስተካከያዎችን አደረገ? ይህስ ምን ውጤት አስገኘ?
13 አንድ ወንድምና እህቱ በወረዳ ስብሰባ ላይ አንድ ንግግር ከሰሙ በኋላ ለስድስት ዓመታት ተወግዳ ከነበረችውና ከእነርሱ ተለይታ ከምትኖረው እናታቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት ረገድ አንዳንድ ማስተካከያዎችን ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው ተገነዘቡ። ስብሰባው እንዳለቀ ወንድም ለእናቱ ስልክ ደወለላትና እሱም ሆነ እህቱ እንደሚወድዷት ሆኖም በጣም አስፈላጊ የሆኑ የቤተሰብ ጉዳዮች ካላጋጠሙ በቀር ከዚህ በኋላ እንደማያነጋግሯት ነገራት። ከጥቂት ጊዜ በኋላ እናትየው በስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመረችና በመጨረሻም ከውገዳ ተመለሰች። የማያምነው ባሏም ማጥናት ጀምሮ ከጊዜ በኋላ ተጠመቀ።
14. የውገዳ እርምጃን በታማኝነት መደገፍ ያለብን ለምንድን ነው?
14 ውገዳን አስመልክቶ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሠፈረውን መመሪያ በታማኝነት መደገፋችን ይሖዋን እንደምንወድድ የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ ለሚሰድበው መልስ ለመስጠት ያስችላል። (ምሳሌ 27:11) በምላሹም የይሖዋን በረከት እንደምናገኝ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ንጉሥ ዳዊት ይሖዋን በተመለከተ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ከሥርዓቱም ዘወር አላልሁም። ለታማኝ ሰው አንተም ታማኝ መሆንህን . . . ታሳያለህ።”—2 ሳሙ. 22:23, 26 አ.መ.ት