የአንባቢያን ጥያቄዎች
የተወገደ ልጅ ያላቸው ክርስቲያን ወላጆች በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አብረውት ቢቀመጡ ተገቢ ነው?
የተወገደ ሰው በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ ስለሚቀመጥበት ቦታ ከሚገባው በላይ መጨነቅ አያስፈልግም። ክርስቲያን ወላጆች አብሯቸው የሚኖር የተወገደ ልጃቸውን በመንፈሳዊ መርዳት እንደሚያስፈልጋቸው ከተሰማቸው እንዲህ እንዲያደርጉ የሚያበረታቱ ሐሳቦች በጽሑፎቻችን ላይ ብዙ ጊዜ ወጥተዋል። እንዲያውም በጥቅምት 1, 2001 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 16 እስከ 18 ላይ እንደተገለጸው ወላጆች ለአካለ መጠን ያልደረሰ የተወገደ ልጃቸው አብሯቸው መኖሩን ከቀጠለ መጽሐፍ ቅዱስን ሊያስጠኑት ይችላሉ። እንዲህ ማድረጋቸው ልጁ አካሄዱን ለማስተካከል የሚያስፈልገውን ማበረታቻ እንዲያገኝ አጋጣሚ ሊከፍትለት ይችላል።a
ለአካለ መጠን ያልደረሰ አንድ የተወገደ ልጅ በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ የሚቀመጥበትን ቦታ በተመለከተ ወደተነሳው ጥያቄ ስንመጣ ደግሞ ልጁ ሌሎችን እስካልረበሸ ድረስ ከወላጆቹ ጋር መቀመጡ ምክንያታዊ ይመስላል። አንድ የተወገደ ሰው በአዳራሹ ውስጥ የግድ የኋላ ወንበር ላይ መቀመጥ እንደማይጠበቅበት ሁሉ አንድ የተወገደ ልጅም ወላጆቹ የትም ይቀመጡ የት ከጎናቸው ቢቀመጥ ምንም ችግር የለውም። ወላጆች ልጃቸውን በመንፈሳዊ መርዳት ስለሚፈልጉ ልጁ ስብሰባዎች ላይ በትኩረት ማዳመጡን መከታተል እንደሚፈልጉ ጥርጥር የለውም። ልጃቸው ብቻውን ሌላ ቦታ እንዲቀመጥ ከመተው ይልቅ አጠገባቸው እንዲቀመጥ ማድረጉ በዚህ ረገድ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።
ይሁንና የተወገደው ልጅ የሚኖረው ከወላጆቹ ጋር ባይሆንስ? እንዲህ ከሆነ ልጁ ከወላጆቹ ጋር መቀመጥ አይችልም ማለት ነው? አንድ ክርስቲያን አብሮት ከማይኖር የተወገደ የቤተሰቡ አባል ጋር ቅርርብ መፍጠርን በተመለከተ ሊኖረው ስለሚገባው ትክክለኛ አመለካከት ከዚህ ቀደም በጽሑፎቻችን ላይ ግልጽ ሐሳብ ወጥቷል።b ይሁን እንጂ አንድ የተወገደ ሰው በስብሰባ ወቅት ሌሎችን ሳይረብሽ ከቤተሰቡ አጠገብ መቀመጡ ቤተሰቡ ከእሱ ጋር አላስፈላጊ ቅርርብ ለመፍጠር ቢሞክሩ ከሚኖረው ሁኔታ ፈጽሞ የተለየ ነው። ታማኝ የሆኑት የቤተሰብ አባላት የተወገደውን ልጅ በተመለከተ ተገቢው አመለካከት ካላቸው እንዲሁም ከእሱ ጋር ሊኖራቸው ስለሚገባው ግንኙነት መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ምክር ለማክበር እየጣሩ ከሆነ አብሯቸው መቀመጡ ያን ያህል የሚያሳስብ ጉዳይ አይደለም።—1 ቆሮ. 5:11, 13፤ 2 ዮሐ. 11
አንድ የተወገደ ሰው በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ በሚገኝበት ጊዜ ተገቢ ያልሆነ ነገር እስካላደረገ ድረስ ከቤተሰቡም ሆነ ከሌሎች የጉባኤው አባላት አጠገብ ቢቀመጥ ጉባኤው ጉዳዩ ሊያሳስበው አይገባም። አንድ ሰው የት መቀመጥ እንዳለበት መወሰን እንደየሁኔታው የተለያዩ ችግሮች ሊፈጥር ይችላል። ታማኝ የሆኑትን የቤተሰቡን አባላት ጨምሮ በስብሰባ ላይ የሚገኙት ሁሉ ከውገዳ ጋር የተያያዙ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ለማክበር ጥረት እስካደረጉ እንዲሁም ጉዳዩ ወንድሞችን የማያሰናክል እስከሆነ ድረስ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የሚገኙ ሰዎች የሚቀመጡበትን ቦታ በተመለከተ መወዛገብ አስፈላጊ አይደለም።c
a በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ስለተወገዱ ልጆች ስንናገር በወንድ ፆታ የተጠቀምን ቢሆንም የቀረቡት ነጥቦች ለሴቶች ልጆችም ይሠራሉ።
b መስከረም 15, 1981 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 29 እና 30ን እንዲሁም ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’ የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 207-209 ተመልከት።
c ይህ ሐሳብ፣ በሚያዝያ 1, 1953 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 223 ላይ በወጣው ትምህርት ላይ የተደረገ ማስተካከያ ነው።