“ቀናተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች” ከተሰኘው የአውራጃ ስብሰባ የተሟላ ጥቅም ማግኘት
1 የሚያነቃቃ ፕሮግራም፦ በቅርቡ ባደረግነው የአውራጃ ስብሰባ ላይ የቀረበልን ፕሮግራም ምንኛ የሚያነቃቃ ነበር! በስብሰባው ላይ የተገኘነው ለአንድ የጋራ ዓላማ ማለትም የአምላክን መንግሥት በቅንዓት ለማወጅ በተሻለ ሁኔታ የታጠቅን ለመሆን ነው። የመጀመሪያው ተናጋሪ “ማወጅ” ለሚለው ቃል የሰጠውን ፍቺ ታስታውሳላችሁ? “ይሖዋ ከእኛ ጋር ስለሆነ አትፍሩ” በተባለው ንግግር ላይ ምን ምርምር እንድናደርግ ተበረታተን ነበር? እስካሁን የትኞቹን የሕይወት ታሪኮች አንብበሃል?
2 “የእምነታችን ጥንካሬ በተለያዩ መከራዎች ይፈተናል” በሚል ጭብጥ የቀረበው ሲምፖዚየም ይሖዋ ስደት እንዲደርስ የሚፈቅድባቸውን ሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች አቅርቦ ነበር። እነዚህን ምክንያቶች መዘርዘር ትችላለህ? ክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋማችንን ጠብቀን እንድንኖር የሚያደርጉን የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ናቸው? በገለልተኝነት አቋማችን ላይ የሚነሱ ፈተናዎችን መቋቋም እንችል ዘንድ ራሳችንን ከወዲሁ ለማዘጋጀት ምን እንድናደርግ ተበረታተናል? ፈተናዎችን በታማኝነት መወጣታችን ለይሖዋ ውዳሴ የሚያመጣለት እንዴት ነው?
3 “በአስቸጋሪ ጊዜያትም ጸንታችሁ ቁሙ” በሚል ርዕስ ከቀረበው ድራማ ውስጥ አንተን በግልህ ያበረታታህ የትኛው ትዕይንት ነው? እንደ ኤርምያስ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
4 “የዚህ ዓለም መልክ ተለዋዋጭ ነው” በሚለው የሕዝብ ንግግር ላይ የተገለጹት አስፈሪው የአምላክ ቀን ከመምጣቱ በፊት የሚፈጸሙ ከፊታችን የሚጠብቁን ወሳኝ ለውጦች የትኞቹ ናቸው? “ቀናተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በመሆን መልካም ሥራ ይብዛላችሁ” በሚል ጭብጥ የቀረበውን የመደምደሚያ ንግግር ስታዳምጥ ትምህርቱን በግልህ ከምታከናውነው አገልግሎት ጋር ያገናዘብከው እንዴት ነው?
5 ተግባራዊ ልናደርጋቸው የምንችላቸው ዋና ዋና ነጥቦች፦ “አመስጋኝ ሁኑ” በሚለው ንግግር ላይ እንደተብራራው ይሖዋን ከልብ በመነጨ ስሜት ማመስገን የምንችለው እንዴት ነው? “የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በከፍተኛ ቅንዓት ያገለግላሉ” በሚል ርዕስ በቀረበው በጭብጡ ቁልፍ ንግግር ላይ የእነማንን ቅንዓት እንድንኮርጅ ተበረታተናል? ራሳችንን ምን ብለን እንድንጠይቅ ተጋብዘናል?
6 “የሚክያስ ትንቢት በይሖዋ ስም እንድንሄድ ብርታት ይሰጠናል” በሚል ጭብጥ የቀረበው ሲምፖዚየም የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት ማሟላት የሚገቡንን የትኞቹን ሦስት ብቃቶች አብራርቷል? ብቃቶቹስ ልናሟላቸው የምንችላቸው ናቸው? (ሚክ. 6:8) “ልባችሁን በመጠበቅ በሥነ ምግባር ንጹሕ ሆናችሁ ኑሩ” በሚለው ንግግር መሠረት በሥነ ምግባር ንጹሕ እንድንሆን ከምን ነገሮች መራቅ አለብን? “ከመታለልም ሆነ ከማታለል ተጠበቁ” በሚል ርዕስ የቀረበው ንግግር በሌሎች እንዳንታለልና እኛም ሌሎችን እንዳናታልል ያስጠነቀቀን በየትኞቹ ዘርፎች ነው?
7 “አገልግሎታቸውን የሚያከብሩ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች” በሚል ርዕስ ከቀረበው ሲምፖዚየም የትኞቹን ጠቃሚ ነጥቦች በአገልግሎትህ ላይ ተግባራዊ ማድረግ ጀምረሃል? “ስለ መንፈሳዊ ነገሮች መወያየት ያንጻል” በሚለው ንግግር ላይ ፊልጵስዩስ 4:8 አንድ በአንድ ተብራርቶ ነበር። ጭውውቶቻችን በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ እንዲያተኩሩ ለማድረግ ይህ ጥቅስ የሚረዳን እንዴት ነው? ስለ መንፈሳዊ ነገሮች መወያየት ያለብንስ መቼ ነው?
8 “መከራ ሲደርስባችሁ በይሖዋ ላይ ሙሉ ትምክህት ይኑራችሁ” የሚለው ንግግር አሳዛኝ ክስተቶችን፣ የኑሮ ውድነትን፣ የጤና እክልን፣ የቤተሰብ ችግሮችና የግል ድክመቶቻችንን እንዴት መቋቋም እንደምንችል ማብራሪያ ሰጥቶ ነበር። እንደዚህ ያሉ ችግሮች ሲያጋጥሙን በይሖዋ እንደምንመካ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
9 አዳዲስ መንፈሳዊ ሀብቶች፦ እውነተኛውን አንድ አምላክ አምልክ (እንግሊዝኛ) በሚል ርዕስ የወጣውን አዲስ መጽሐፍ በማግኘታችን ተደስተን ነበር። የመጽሐፉን ዓላማ በተመለከተ የቀረበው ማስታወቂያ ምን እንድናደርግ የሚያሳስብ ነበር? ይህን መጽሐፍ እንደ ሁለተኛ የማስጠኛ መጽሐፍ አድርጎ መጠቀሙ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራችን ጠቃሚ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
10 ቀጥሎ ይሖዋን የቅርብ ወዳጅህ አድርገው (እንግሊዝኛ) የተባለውን ውብ መጽሐፍ አገኘን። የመጽሐፉ አንዳንድ ልዩ ገጽታዎች ምንድን ናቸው? በተለይ በጣም የወደድሃቸው ሥዕሎች የትኞቹ ናቸው? ይህን መጽሐፍ ማንበብህ ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድትቀርብ ረድቶሃል? እነማን ጭምር ከዚህ መጽሐፍ ጥቅም ማግኘት ይችላሉ?
11 “ቀናተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች” የተሰኘው የአውራጃ ስብሰባ እነዚህን አስቸጋሪ ወቅቶች በጽናት ለመወጣት የሚያስፈልገንን መንፈሳዊ ማበረታቻ ሰጥቶናል። ከዚህ ልዩ መንፈሳዊ ዝግጅት የተሟላ ጥቅም ማግኘት እንችል ዘንድ የሰማነውን ለማስታወስ፣ በስብሰባው ላይ ለወ ጡት አዳዲስ ጽሑፎች አድናቆት ለማሳየትና የተማርነውን በሥራ ላይ ለማዋል የተቻለንን ሁሉ ጥረት እናድርግ። (2 ጴጥ. 3:14) እንዲህ ማድረጋችን ጽኑ አቋማችንን ጠብቀን እንድንኖርና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወልንን ምሳሌ በመኮረጅ ቀናተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች እንድንሆን የሚረዳን ሲሆን ይህም ይሖዋን ያስከብራል።—ፊልጵ. 1:9-11