የመንግሥቱን መልእክት አውጁ
1 “ስለዚህ ተልኬአለሁና . . . የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እሰብክ ዘንድ ይገባኛል።” (ሉቃስ 4:43) ኢየሱስ ከላይ ባሉት ቃላት የአገልግሎቱ ዋነኛ ጭብጥ የአምላክ መንግሥት መሆኑን ገልጿል። እኛም ዛሬ የምናውጀው መልእክት “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” በሚለው በማቴዎስ 24:14 መሠረት በመንግሥቱ ላይ ያተኮረ ነው። መንግሥቱን በሚመለከት ሰዎች መስማት የሚያስፈልጋቸው እውነታዎች ምንድን ናቸው?
2 የአምላክ መንግሥት በአሁኑ ወቅት ከሰማይ ሆኖ በመግዛት ላይ እንደሚገኝና በቅርቡም ሰብዓዊ አገዛዝን ጠራርጎ እንደሚያስወግድ መስማት አለባቸው። ሰይጣን ከሰማይ የተባረረ ሲሆን አሁን ያለው ክፉ ሥርዓት የቀረው እድሜ በጣም አጭር ሆኗል። (ራእይ 12:10, 12) አሮጌው የሰይጣን ክፉ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ይደመሰሳል፤ የአምላክ መንግሥት ግን ፈጽሞ አይናወጥም። ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።—ዳን. 2:44፤ ዕብ. 12:28
3 የአምላክ መንግሥት ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች ፍላጎቶቻቸውን በሙሉ ያሟላላቸዋል። ጦርነት፣ ወንጀል፣ ጭቆናና ድህነት ያስከተሉትን ሥቃይ ያስወግዳል። (መዝ. 46:8, 9፤ 72:12-14) ሁሉም ሰው የተትረፈረፈ ምግብ ያገኛል። (መዝ. 72:16፤ ኢሳ. 25:6) ሕመምና የአካል ጉዳተኝነት የተረሱ ነገሮች ይሆናሉ። (ኢሳ. 33:24፤ ኢሳ. 35:5, 6) የሰው ዘር ፍጹም እየሆነ ሲሄድ መላዋ ምድር ወደ ገነትነት ትለወጣለች፤ ሰዎችም እርስ በርስ ተስማምተው ይኖራሉ።—ኢሳ. 11:6-9
4 የአምላክ መንግሥት ተገዢዎች መሆን እንደምንፈልግ በአኗኗራችን እናሳያለን። የመንግሥቱ መልእክት የምናወጣውን ግብና ቅድሚያ የምንሰጣቸውን ነገሮች ጨምሮ በመላው ሕይወታችን ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይገባል። ለምሳሌ ያህል ለቤተሰባችን የሚያስፈልገውን ነገር የማሟላት ግዴታ ያለብን ብንሆንም ቁሳዊ ፍላጎቶቻችን የመንግሥቱን መልእክት እንዳናውጅ እንቅፋት እንዲሆኑብን መፍቀድ አይኖርብንም። (ማቴ. 13:22፤ 1 ጢሞ. 5:8) ከዚህ ይልቅ “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም [ለሕይወት የሚያስፈልጉ ቁሳዊ ነገሮች] ሁሉ ይጨመርላችኋል” የሚለውን የኢየሱስ ምክር መከተል አለብን።—ማቴ. 6:33
5 ጊዜው ከማለቁ በፊት ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት ሰምተው እርምጃ መውሰዳቸው በጣም አጣዳፊ ነው። ‘ስለ አምላክ መንግሥት በመናገርና በማስረዳት’ እንዲህ እንዲያደርጉ የምንረዳቸው እንሁን።—ሥራ 19:8