በታማኝነት የሚመላለሱ አረጋውያንን አስቡ
1 ምንም እንኳን መበለትና በእድሜ የገፋች ብትሆንም የ84 ዓመቷ አረጋዊት ሐና “ከመቅደስ አትለይም ነበር።” ይሖዋም ይህን ታማኝነቷን በመመልከት ክሷታል። (ሉቃስ 2:36-38) በዛሬው ጊዜም በርካታ ወንድሞችና እህቶች አስቸጋሪ ሁኔታዎች እያሉባቸው እንደ ሐና ያለ የታማኝነት መንፈስ ያሳያሉ። እነዚህ ታማኝ ምሥክሮች የጤና ችግሮቻቸውን ወይም የእድሜ መግፋት የሚያስከትልባቸውን የአቅም ገደብ እየታገሉ የሚኖሩ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሊያድርባቸው ይችላል። እነዚህን አረጋውያን ምሥክሮች ማበረታታትና ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ እንዲኖራቸው መርዳት የምንችልባቸውን አንዳንድ ጠቃሚ መንገዶች እስቲ እንመልከት።
2 በስብሰባዎችና በአገልግሎት፦ አንዳንዶች በፍቅር ተነሳስተው መጓጓዣ የሚያመቻቹላቸው ከሆነ በርካታ ታማኝ አረጋውያን ምሥክሮች በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ መገኘት ቀላል ይሆንላቸዋል። ይህም እነዚህን ለብዙ ዓመታት ያገለገሉ ታማኝ ምሥክሮች በመንፈሳዊ የሚገነባቸው ሲሆን ጉባኤውንም ይጠቅማል። በዚህ መልካም ተግባር ተካፍለህ ታውቃለህ?—ዕብ. 13:16
3 አዘውትሮ በአገልግሎት መካፈል ለእውነተኛ ክርስቲያኖች ደስታና እርካታ ያስገኝላቸዋል። ይሁን እንጂ እንዲህ ማድረጉ ለአረጋውያንና አቅመ ደካማ ለሆኑት ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። ከእነዚህ ውድ ምሥክሮች መካከል አንዳቸው በአንድ ዓይነት የአገልግሎት ዘርፍ ‘አብረውህ እንዲሠሩ’ ማድረግ ትችላለህ? (ሮሜ 16:3, 9, 21) የስልክ ምሥክርነት በምትሰጥበት ወቅት ወይም ተመላልሶ መጠይቅ ስታደርግ ወይም የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስትመራ ይዘሃቸው ልትሄድ ትችላለህ። ከቤት መውጣት የማይችሉ ከሆነም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህን እቤታቸው ይዘህ በመሄድ አብራችሁ ልታስጠኑት ትችላላችሁ?
4 የቤተሰብ ጥናትና ማኅበራዊ ግንኙነት፦ አንዳንዶች በቤተሰብ ጥናታቸው ላይ አብረዋቸው እንዲገኙ በእድሜ የገፉ ወይም አቅመ ደካማ የሆኑ ምሥክሮችን አልፎ አልፎ ወደ ቤታቸው ይጋብዟቸዋል፤ አልፎ ተርፎም ጥናቱ በእነርሱ ቤት እንዲካሄድ ያደርጋሉ። አንዲት እናት የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን የያዘው መጽሐፌ የተባለውን መጽሐፍ የሚያጠኑ ሁለት ትናንሽ ልጆቿን ወደ አንዲት አረጋዊት እህት ቤት ይዛ ሄዳ እዚያ በማስጠናቷ ሁሉም ሊበረታቱ ችለዋል። አረጋውያንን ለምግብ ወይም ለሌላ ማኅበራዊ ጭውውት እቤታችሁ ብትጋብዟቸው በጣም ይደሰታሉ። ረዘም ያለ ሰዓት አብረውህ መቆየት የማይችሉ ከሆነም ስልክ ልትደውልላቸው ወይም ቤታቸው ጎራ ብለህ ልታነብላቸው፣ አብረሃቸው ልትጸልይ ወይም አንድ የሚያንጽ ተሞክሮ ልታካፍላቸው ትችላለህ።—ሮሜ 1:11, 12
5 ይሖዋ በታማኝነት የሚመላለሱ አረጋዊ ምሥክሮችን ያስብላቸዋል። (ዕብ. 6:10, 11) እኛም ለእነርሱ ያለንን አክብሮት በመግለጽና ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ እንዲኖራቸው በመርዳት የእሱን ምሳሌ መኮረጅ እንችላለን።