ለምን አትጋብዟቸውም?
በበርካታ ጉባኤዎች ውስጥ በጤና እክል ወይም በዕድሜ መግፋት ምክንያት በአገልግሎት የሚያደርጉት ተሳትፎ ውስን የሚሆንባቸው አስፋፊዎች አሉ። (2 ቆሮ. 4:16) እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ወንድሞችንና እህቶችን ጥናት መጋበዝ ትችላላችሁ? አስፋፊው ከቤቱ መውጣት የማይችል ከሆነ ጥናቱን እሱ ቤት መምራት ትችሉ ይሆናል። የጤና ችግር ያለበት አንድ አስፋፊ ጥቂት ቤቶችን በማንኳኳት ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት ላይ እንዲካፈል ልትረዱት አሊያም አንድ ወይም ሁለት ተመላልሶ መጠየቅ እንዲያደርግ ልትወስዱት ትችላላችሁ? በርካታ በዕድሜ የገፉ አስፋፊዎች በአገልግሎት ጥሩ ልምድ አላቸው። በመሆኑም በዚህ ረገድ የምታደርጉት ጥረት እነሱን ከማበረታታት ያለፈ ጥቅም ይኖረዋል። ምክንያቱም እናንተም ትጠቀማላችሁ። (ሮም 1:12) በተጨማሪም በዚህ መልኩ ለወንድሞቻችሁ ፍቅር ለማሳየት የምታደርጉትን ጥረት ይሖዋ ይባርከዋል።—ምሳሌ 19:17፤ 1 ዮሐ. 3:17, 18