የበለጠ ተሞክሮ ካላቸው አስፋፊዎች መማር
በጉባኤያችን ውስጥ ያሉትን ተሞክሮ ያላቸው አስፋፊዎች ከፍ አድርገን እንመለከታቸዋለን። አንዳንዶቹ ለብዙ ዓመታት ይሖዋን በታማኝነት አገልግለዋል። ሌሎቹ ደግሞ በእውነት ቤት ብዙ ባይቆዩም እንኳ በአገልግሎት ረገድ ጥሩ ችሎታ አላቸው። ተሞክሮ ያላቸው አስፋፊዎች ኢየሱስ በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት የስብከቱና ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ እያደገ እንዲሄድ በማድረግ የክርስቲያን ጉባኤን እንዴት እየመራው እንዳለ ተመልክተዋል። (ማቴ. 28:19, 20) ከገጠሟቸው ችግሮችና ፈተናዎች ጋር እየታገሉ በዚህ ሥራ ሲካፈሉ ይሖዋ ‘ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነ ኃይል’ ሰጥቷቸዋል። (2 ቆሮ. 4:7) በእርግጥም ተሞክሮ ካላቸው ከእነዚህ አስፋፊዎች ብዙ መማር ይቻላል። እነሱም አጋጣሚውን ሲያገኙ በሕይወታቸው የተማሩትን ነገር ለሌሎች ማካፈል ያስደስታቸዋል። (መዝ. 71:18) በመሆኑም አጋጣሚዎችን ፈልገን ከእነሱ ለመማር ጥረት ማድረግ አለብን። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
በአገልግሎት ላይ፦ አዳዲሶች ወይም ብዙም ተሞክሮ የሌላቸው አስፋፊዎች በአገልግሎት ረገድ ውጤታማ እንዲሆኑ ሥልጠና ያስፈልጋቸዋል። ብስለት ያላቸው አስፋፊዎች አገልግሎታቸውን የሚያከናውኑበትን መንገድ በሚገባ በመመልከት ብዙ መማር ይቻላል። (በየካቲት 15, 2015 መጠበቂያ ግንብ ላይ “ለአገልግሎት ያላችሁ ቅንዓት እንዳይቀዘቅዝ ጥረት አድርጉ” በሚለው ርዕስ ላይ “ብዙም ተሞክሮ የሌላቸውን መርዳት” በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር የሚገኘውን ሦስተኛ አንቀጽ ተመልከቱ።) ከእነዚህ ወንድሞች ጋር በማገልገል ምን ጥቅም አግኝታችኋል?
በአገልግሎት ጥሩ ብቃት ያለውን አንድ አስፋፊ አብሯችሁ እንዲያገለግል ልትጠይቁት ትችላላችሁ? ይህ አስፋፊ በጤና ችግር ወይም በዕድሜ መግፋት የተነሳ የአቅም ገደብ ካለበት ደግሞ አልፎ አልፎ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችሁን ወደ እሱ ቤት ይዛችሁ በመሄድ ጥናቱን መምራት ትችሉ ይሆናል። ጥናቱ ከተደመደመ በኋላ አስፋፊውን ምክር እንዲሰጣችሁ ጠይቁት።
ከእነሱ ጋር በግል ጊዜ በማሳለፍ፦ ተሞክሮ ካላቸው አስፋፊዎች ጋር ጊዜ በማሳለፍ ከእነሱ ጋር በደንብ መተዋወቅ ትችላላችሁ። በቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችሁ ላይ እንዲገኙ በማድረግ ቃለ መጠይቅ ልታደርጉላቸው ትችላላችሁ። አስፋፊው የአቅም ገደብ ያለበት ከሆነ ደግሞ የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችሁን እሱ ቤት ማድረግ ትችሉ ይሆን? አስፋፊው ወደ እውነት የመጣው እንዴት እንደሆነ ጠይቁት። በተጨማሪም ምን በረከቶችን እንዳገኘ፣ ወደ እውነት ከመጣ ወዲህ በአካባቢው የይሖዋ ምሥክሮች ምን ያህል እድገት እንዳደረጉ እንዲሁም ይሖዋን በማገልገል ስላገኘው ደስታ ልትጠይቁት ትችላላችሁ።
ተሞክሮ ካላቸው አስፋፊዎች በምትጠብቁት ነገር ረገድ ምክንያታዊና ሚዛናዊ መሆን አለባችሁ። ለረጅም ጊዜ በእውነት ቤት የቆዩ አስፋፊዎች ልክ እንደ ሌሎቻችን ሁሉ በአገልግሎት ረገድ ያላቸው ተሰጥኦ የተለያየ ነው። (ሮም 12:6-8) አንዳንዶቹ በዕድሜ የገፉ ስለሆኑ ከእኛ ጋር የሚያሳልፉት ጊዜ ውስን ሊሆን ይችላል። ያም ቢሆን ይሖዋን በታማኝነት በማገልገል ካሳለፉት ተሞክሮ ብዙ መማር እንችላለን።