“ለአምላክ ክብር ስጡት” የ2003 የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ
1 ይሖዋ ታማኝ በሆነው በነቢዩ በኢሳይያስ አማካኝነት “ወገኔ ሆይ፣ አድምጠኝ፤ ሕዝቤ ሆይ፣ ስማኝ” የሚል ትእዛዝ አስተላልፏል። (ኢሳ. 51:4) ከጊዜ ወደ ጊዜ በጣም አስጨናቂ እየሆነ በሚሄደው በዚህ የመጨረሻ ቀን ከመቼውም ይበልጥ ለይሖዋ ትእዛዝ ትኩረት መስጠት አስፈላጊ ነው ቢባል አንስማማም? ይሖዋን ‘የምንሰማበት’ አንደኛው መንገድ ለአምልኮ እንድንሰበሰብ የሰጠንን ትእዛዝ በማክበር ነው። በዓመት አንድ ጊዜ በምናደርገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ በአንድነት ተሰብስበን ለመማር ያለንን ልዩ አጋጣሚ በጉጉት እንጠባበቃለን!
2 በሦስቱም ቀን ተገኙ:- በታማኝና ልባም ባሪያ አማካኝነት ከሚቀርበው ትምህርት የተሟላ ጥቅም ለማግኘት በስብሰባው ላይ ተገኝተን ሙሉውን ፕሮግራም መከታተል እንድንችል አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እናድርግ። (ማቴ. 24:45) በአውራጃ ስብሰባው ላይ ሦስቱንም ቀን መገኘት እንድትችል አሠሪህን ፈቃድ መጠየቅ ያስፈልግህ ይሆን? ነህምያ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ቅጥሮቿን መልሶ ለመገንባት ንጉሥ አርጤክስስን ፈቃድ ከመጠየቁ በፊት ‘ወደ ሰማይ አምላክ ጸልዮአል።’ (ነህ. 2:4) አንተም በሦስቱም ቀናት ስብሰባው ላይ መገኘት እንድትችል አሠሪህን ፈቃድ ለመጠየቅ ድፍረት እንዲሰጥህ ወደ ይሖዋ መጸለይ ይገባሃል። አሠሪህ ፈቃድ ለመስጠት ባይስማማስ? በአውራጃ ስብሰባዎቻችን ላይ የምናገኘው ሥልጠና ሐቀኞች፣ ትጉዎችና እምነት የሚጣልብን ሠራተኞች እንድንሆን እንደሚረዳን ብትነግረው ፈቃድ ሊሰጥህ ይስማማ ይሆናል። ከዚህም በላይ ከቤተሰባችን አባላት መካከል የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ካሉ የስብሰባ ፕሮግራማችንን በተቻለ መጠን አስቀድመን መንገራችን አሳቢነት ነው።
3 “የዚች ዓለም መልክ አላፊ” በመሆኑ በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን ለመኖር የአውራጃ ስብሰባዎቻችን በጣም ያስፈልጉናል። (1 ቆሮ. 7:31) በስብሰባው ላይ ሁሉንም ቀን ለመገኘት ዝግጅት ማድረግ ጥረት የሚጠይቅ ቢሆንም እንደዚህ ማድረጋችን አያስቆጭም። “ለአምላክ ክብር ስጡት” የተባለው የዚህ ዓመት የአውራጃ ስብሰባ ይሖዋ በሰይጣን ዓለም ላይ የሚያመጣውን ጥፋት በምንጠባበቅበት ጊዜ በአቋማችን ጸንተን መቀጠል እንድንችል ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀ ነው። ይሖዋ ያዘጋጀልንን ትምህርት ለመከታተል በአውራጃ ስብሰባው ላይ እንዳንገኝ እንቅፋት የሚሆንብንን ማንኛውንም ነገር እናስወግድ።—ኢሳ. 51:4, 5