የ2008 የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ
1. (ሀ) ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ በዛሬው ጊዜ አጣዳፊ የሆነው ለምንድን ነው? (ዕብራውያን 10:24, 25ን አንብብ።) (ለ) ጳውሎስ የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የምንችልበት ምን አጋጣሚ ከፊታችን ይጠብቀናል?
1 ሐዋርያው ጳውሎስ የዕብራውያን ክርስቲያኖች አንድ ላይ እንዲሰበሰቡና ቀኑ መቅረቡን ሲመለከቱ “ከበፊቱ ይበልጥ” (NW) እርስ በርስ እንዲበረታቱ አሳስቧቸዋል። (ዕብ. 10:24, 25) ጳውሎስ የተናገረው ይህ ‘ቀን’ በጣም መቅረቡን የሚያሳዩ ምልክቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ ናቸው! በመሆኑም፣ ከዕለት ዕለት እጅግ አደገኛ እየሆነ በመጣው በዚህ ‘የመጨረሻ ዘመን’ ውስጥ መመሪያ ሊሆነን የሚችል መንፈሳዊ ትምህርት ለማግኘት ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር አብረን የምንሰበሰብባቸውን አጋጣሚዎች በጉጉት እንጠብቃለን። (2 ጢሞ. 3:1) ከፊት ለፊታችን የሚጠብቁን በ2008 የሚደረጉት የአውራጃ ስብሰባዎች ደግሞ እንዲህ ያለውን አጋጣሚ እንድናገኝ ያስችሉናል።
2. (ሀ) በሦስቱም የስብሰባው ቀናት ላይ መገኘታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በስብሰባው ላይ ለመገኘት የምናደርገውን ዝግጅት መጀመር ያለብን እንዴት ነው?
2 በሦስቱም ቀናት ተገኙ፦ በሦስቱም የስብሰባ ቀናት እንድትገኙ እናበረታታችኋለን። “መሰብሰባችንን አንተው” የሚለውን ምክር በሥራ ላይ የምናውል ከሆነ በአውራጃ ስብሰባው ላይ የሚቀርበው አስፈላጊ የሆነው መንፈሳዊ ምግብ አያመልጠንም። (ዕብ. 10: 25) በስብሰባው ላይ ለመገኘት እንድትችሉ ከወ ዲሁ ዝግጅት ማድረግ ጀምሩ። አሠሪያችሁ አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግ እንዲችል ቀደም ብላችሁ ስለ ስብሰባው ለማሳወቅ ትፈልጉ ይሆናል። ልጆቻችሁ ስብሰባው በሚደረግበት ወቅት ትምህርት ካላቸው ለአስተማሪዎቻቸው ስለ ጉዳዩ አሳውቋቸው፤ እንዲሁም ስብሰባው ቋሚ የአምልኮታችሁ ክፍል እንደሆነ ንገሯቸው። ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለማስቀደም የምታደርጉትን ጥረት ይሖዋ እንደሚባርክላችሁ እርግጠኞች ሁኑ።—ማቴ. 6:33
3. ለሌሎች ትኩረት እንደሰጠን ማሳየት የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
3 ሌሎችም እንዲገኙ እርዱ፦ በተጨማሪም ጳውሎስ ለክርስቲያን ወንድሞቹ ‘አንዳቸው ለሌላው ትኩረት እንዲሰጡ’ ጽፎላቸዋል። (ዕብ. 10:24 NW) በጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት ቡድናችሁ ውስጥ ከሚገኙ ወንድሞችና እህቶች መካከል በአውራጃ ስብሰባው ላይ ለመገኘት የእናንተን እርዳታ የሚፈልጉ አሉ? የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችሁ ለአንድ ቀንም ቢሆን በስብሰባ ላይ እንዲገኙ ልትረዷቸው ትችላላችሁ? የአውራጃ ስብሰባውን አስመልክታችሁ ከማያምኑ የቤተሰባችሁ አባላት ጋር ስትነጋገሩ እነሱም በስብሰባው ላይ እንዲገኙ ጋብዟቸው። በፍቅር ተነሳስታችሁ የምታደርጓቸው ጥረቶች ያልተጠበቁ ውጤቶች ያስገኙ ይሆናል።
4. የማረፊያ ችግር ላለባቸው የተዘጋጀ ቅጽ የሚለውን ፎርም በተመለከተ የተሰጡ አንዳንድ ማሳሰቢያዎች ምንድን ናቸው?
4 የማረፊያ ችግር፦ አንድ አስፋፊ የአውራጃ ስብሰባው በሚደረግበት ቦታ የማረፊያ ዝግጅት እንዲደረግለት ከጠየቀ የጉባኤው የአገልግሎት ኮሚቴ አስፋፊው የማረፊያ ችግር ላለባቸው የተዘጋጀ ቅጽ የተባለውን ፎርም ለመሙላት ብቃቱ እንዳለውና እንደሌለው መወሰን ይኖርበታል። የጉባኤው ጸሐፊ ይህንን ፎርም ሞልቶ ለአውራጃ ስብሰባው የመስተንግዶ ክፍል ከመላኩ በፊት በቅጹ ላይ የሠፈሩትን መመሪያዎች እንዲሁም ታኅሣሥ 14, 2006 ለሁሉም የሽማግሌዎች አካላት የተላከውን ደብዳቤ መመልከት ይኖርበታል።
5. በማቴዎስ 4:4 ላይ የተገለጸው ሐሳብ በስብሰባው ላይ የሚቀርበውን እያንዳንዱን ክፍል በትኩረት መከታተል አስፈላጊ መሆኑን የሚያጎላው እንዴት ነው?
5 ኢየሱስ ሕልውናችን የተመካው ‘ከይሖዋ አፍ የሚወጣውን ቃል ሁሉ’ በማዳመጥ ላይ እንደሆነ ተናግሯል። (ማቴ. 4:4) ይሖዋ፣ በዓመት አንድ ጊዜ በምናደርገው የአውራጃ ስብሰባ አማካኝነት ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ የተዘጋጀ መንፈሳዊ ‘ምግብ በጊዜው’ እንዲቀርብ ያደርጋል። (ማቴ. 24:45 የ1954 ትርጉም) ይህን መንፈሳዊ ድግስ አዘጋጅቶ ለማቅረብ ብዙ ተደክሞበታል። በመሆኑም በስብሰባው ላይ በመገኘት እንዲሁም የሚቀርበውን እያንዳንዱን ክፍል ትኩረት ሰጥተን በማዳመጥ ለይሖዋ ፍቅራዊ አሳቢነት ያለንን አመስጋኝነት እናሳይ።
[በገጽ 1 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የስብሰባው ሰዓት:-
አርብና ቅዳሜ ከ3:20 እስከ 10:55
እሁድ ከ3:20 እስከ 10:00