የተሟላ ምሥክርነት ስጡ
1 ኢየሱስ “አለቃና አዛዥ” እንደመሆኑ መጠን ደቀ መዛሙርቱን ከፊታቸው ለሚጠብቃቸው መጠነ ሰፊ የስብከት ሥራ አዘጋጅቷቸው ነበር። (ኢሳ. 55:4፤ ሉቃስ 10:1-12፤ ሥራ 1:8) ሐዋርያው ጴጥሮስ ኢየሱስ የሰጣቸውን ተልዕኮ እንዲህ በማለት ገልጾታል:- “ለሕዝብም እንድንሰብክና በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ በእግዚአብሔር የተወሰነ እርሱ እንደ ሆነ እንመሰክር [“የተሟላ ምሥክርነት እንሰጥ፣” NW ] ዘንድ አዘዘን።” (ሥራ 10:42) የተሟላ ምሥክርነት መስጠት የምንችለው እንዴት ነው?
2 የተሟላ ምሥክርነት በመስጠት ረገድ ሐዋርያው ጳውሎስ ከተወው ምሳሌ ብዙ መማር እንችላለን። ሐዋርያው ጳውሎስ ከኤፌሶን ሽማግሌዎች ጋር በተገናኘበት ወቅት እንዲህ ብሏቸው ነበር:- “ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ንስሐንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን ለአይሁድና ለግሪክ ሰዎች እየመሰከርሁ [“የተሟላ ምሥክርነት እየሰጠሁ፣” NW ] በጉባኤም በየቤታችሁም አወራሁላችሁና አስተማርኋችሁ እንጂ፣ ከሚጠቅማችሁ ነገር አንዳች ስንኳ አላስቀረሁባችሁም።” ጳውሎስ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢገጥሙትም ምሥራቹን በተቻለ መጠን ለበርካታ ሰዎች ለማዳረስ ጥረት አድርጓል። ለአድማጮቹ መሠረታዊ እውነቶችን ብቻ በማስተማር ሳይወሰን “የእግዚአብሔርን ምክር ሁሉ” ያካፍላቸው ነበር። ለዚህም ሲል ተጨማሪ ጥረት ለማድረግና መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኛ ነበር። “ሩጫዬንና ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን አገልግሎት እርሱም የእግዚአብሔርን ጸጋ ወንጌልን መመስከር እፈጽም [“በተሟላ ሁኔታ እመሰክር፣” NW ] ዘንድ ነፍሴን በእኔ ዘንድ እንደማትከብር እንደ ከንቱ ነገር እቈጥራለሁ” በማለት አክሎ ተናግሯል።—ሥራ 20:20, 21, 24, 27
3 ዛሬ እኛ የእሱን ምሳሌ መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው? (1 ቆሮ. 11:1) አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙንም ምሥራቹ የሚገባቸውን ሰዎች በመፈለግ፣ ከሁሉም ዓይነት ጎሳ ለመጡ ሰዎች ምሥራቹን ለማዳረስ ጥረት በማድረግና ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን በትጋት ተመላልሰን በመርዳት ምሳሌውን መኮረጅ እንችላለን። (ማቴ. 10:12, 13) ይህም ጊዜ፣ ጥረትና ለሰዎች ፍቅር ማሳየትን ይጠይቃል።
4 ረዳት አቅኚ ሆነህ ማገልገል ትችላለህ? በመጋቢትና በሚያዝያ ረዳት አቅኚ ሆነህ በማገልገል የተሟላ ምሥክርነት መስጠት የሚያስችል ግሩም አጋጣሚ አለህ። ባለፈው ዓመት በርካታ አስፋፊዎች ረዳት አቅኚ ሆነው ለማገልገል ልዩ ጥረት ማድረጋቸው በጣም የሚያበረታታ ነው!
5 በርካታ የጤና እክሎች ያሉባቸው አንዲት የ80 ዓመት አረጋዊት እህት ከይሖዋ ድርጅት ባገኙት ማበረታቻ የአገልግሎት ቅንዓታቸው ጨምሮ ነበር። እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “ማበረታቻው ለረጅም ጊዜ በውስጤ የነበረውን የአገልግሎት ፍላጎት ያቀጣጠለው ሲሆን ቢያንስ አንድ ጊዜ እንኳ ረዳት አቅኚ መሆን አለብኝ እንድል አድርጎኛል።” በመጋቢት ረዳት አቅኚ ለመሆን ግብ አወጡ። “የመጀመሪያ እርምጃዬ ሁኔታዬን በጥሞና መመርመር ነበር። የሴት ልጄ እርዳታ ያስፈልገኝ ስለነበር ከሷ ጋር በጉዳዩ ላይ ተነጋገርንበት። እሷም ረዳት አቅኚ ሆና ለማገልገል ስታመለክት በጣም ተገረምኩ” በማለት ተናግረዋል። እኚህ አረጋዊት እህት በዚያ ወር በአገልግሎት 52 ሰዓት ለማሳለፍ ችለዋል። “ብዙ ጊዜ ኃይሌ እንደተሟጠጠ ሲሰማኝ ይሖዋ ብርታት እንዲሰጠኝ በጸሎት እጠይቀው ነበር። በወሩ መጨረሻ ላይ ትልቅ ደስታና እርካታ የተሰማኝ ሲሆን ይሖዋም ስለረዳኝ በተደጋጋሚ አመስግኜዋለሁ። በድጋሚ ረዳት አቅኚ ሆኜ ማገልገል እፈልጋለሁ።” የእኚህ እህት አስደሳች ተሞክሮ ከባድ የጤና ችግሮች እያሉባቸው ረዳት አቅኚ ሆነው ማገልገል የሚፈልጉ ሌሎች አስፋፊዎችን ሊያበረታታ ይችላል።
6 በድንገት ከሥራው የተባረረ አንድ ወንድም አጋጣሚውን ረዳት አቅኚ ሆኖ ለማገልገል ተጠቀመበት። ወሩ እየተገባደደ ሲሄድ ለስብከቱ ሥራ የነበረው ቅንዓት የጨመረ ከመሆኑም በላይ በወሩ መጨረሻ ላይ አንድ አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማግኘት ችሏል። “በጣም አስደሳች ወር ነበር!” በማለት ተናግሯል። የይሖዋን አመራርና እርዳታ በማግኘቱ በጣም ተደስቷል። ይህ ወንድም አገልግሎቱን ለማስፋት ተጨማሪ ጥረት በማድረጉ ይሖዋ አትረፍርፎ እንደባረከው ሁሉ እናንተንም እንዲሁ ይባርካችኋል።—ሚል. 3:10
7 ለብዙ አስፋፊዎች ረዳት አቅኚ ሆኖ ማገልገል ቀላል አይደለም። ያም ሆኖ ግን ብዙ ወንድሞችና እህቶች ሰብዓዊ ሥራና የቤተሰብ ኃላፊነቶች እንዲሁም የግል ችግሮች ቢኖሩባቸውም ረዳት አቅኚ ሆነው ለማገልገል ችለዋል። ብዙውን ጊዜ የተሟላ ምሥክርነት መስጠት ውድ ጊዜያችንንና ጉልበታችንን መሥዋዕት ማድረግን የሚጠይቅብን ቢሆንም እንዲህ በማድረጋችን የምናገኘው በረከት ወደር የለውም።—ምሳሌ 10:22
8 መጋቢትና ሚያዝያ ረዳት አቅኚ ሆኖ ለማገልገል አመቺ ወራት ናቸው። መጋቢት አምስት ቅዳሜና እሁዶች አሉት። የሙሉ ቀን ሰብዓዊ ሥራ ያላቸው አስፋፊዎች እነዚህን ቀናትና ከሥራ በኋላ ያሉትን ሰዓታት በሚገባ በመጠቀም ረዳት አቅኚ ሆነው ማገልገል ይችላሉ። በሚያዝያ ወር ደግሞ በበዓል ቀናትም ማገልገል ትችሉ ይሆናል። አንዳንዶች በበዓላት ዋዜማና ማግሥት በሚኖሩት የእረፍት ቀናት በማገልገል በወሩ ውስጥ የሚፈለግባቸውን 50 ሰዓት ለማሟላት ይችሉ ይሆናል። ከዚህ ርዕስ ጋር ተያይዞ የቀረበውን የናሙና ፕሮግራም በመጠቀም በመጋቢትና በሚያዝያ ወራት 50 ሰዓት ለማገልገል የሚያስችልህን ፕሮግራም ማውጣት ትችል ይሆን? ስላወጣኸው ፕሮግራም ለሌሎች ንገራቸው፤ እንዲህ ማድረግህ አንዳንዶች አብረውህ እንዲያገለግሉ እንደሚያበረታታቸው አያጠራጥርም። በእነዚህ ወራት ረዳት አቅኚ ሆነህ ለማገልገል የማትችል ከሆነ የራስህን የሰዓት ግብ አውጣ፤ እንዲሁም ረዳት አቅኚ ሆነው ለማገልገል የቻሉትን ለመደገፍ ጥረት አድርግ። በመጋቢትና በሚያዝያ ወራት አገልግሎትህን ከፍ ለማድረግ ከአሁኑ እቅድ አውጣ።
9 ለመታሰቢያው በዓል አድናቆት አሳዩ:- በየዓመቱ በመታሰቢያው በዓል ሰሞን በርካታ አስፋፊዎች ለቤዛው ዝግጅት ባላቸው አድናቆት በመነሳሳት ‘ጊዜያቸውን ዋጅተው’ ረዳት አቅኚ ይሆናሉ። (ኤፌ. 5:15, 16) ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ በመጋቢት ወር 1, 918፣ በሚያዝያ ደግሞ 765 ረዳት አቅኚዎች ነበሩ። ይህም በሁለቱ ወራት በእያንዳንዳቸው በአማካይ 1, 342 የሚያህሉ አስፋፊዎች ረዳት አቅኚ ሆነው ነበር ማለት ነው። ይህ ቁጥር በዚያ የአገልግሎት ዓመት ከዚያ ቀደም በነበሩት ወራት ከነበረው 267 የሚያህል አማካይ የረዳት አቅኚዎች ቁጥር በእጅጉ ይበልጣል። በዚህ ዓመት በሚከበረው የመታሰቢያ በዓል ወቅትም በመስክ አገልግሎት የምናደርገውን ተሳትፎ ከፍ በማድረግ ለክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ያለንን ልባዊ አድናቆት የምናሳይበት አጋጣሚ ተከፍቶልናል።
10 ሚያዝያ 16 እየተቃረበ ሲሄድ የመታሰቢያው በዓል ለአንተ ምን ትርጉም እንዳለው ትኩረት ሰጥተህ አስብበት። ከክርስቶስ ሞት ጋር ስለተያያዙት ሁኔታዎችና በጣም ያሳስቡት ስለነበሩት ነገሮች ለማስታወስ ሞክር። ከፊቱ ይጠብቀው ስለነበረው ደስታና ይህም የደረሰበትን ከባድ መከራ ለመቋቋም እንዴት እንደረዳው አሰላስል። የጉባኤው ራስ ሆኖ የስብከቱንና ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ በበላይነት ለመቆጣጠር ስላገኘው ሥልጣን አስብ። (1 ቆሮ. 11:3፤ ዕብ. 12:2፤ ራእይ 14:14-16) ከዚያም ክርስቶስ ላደረገልህ ለዚህ ሁሉ አመስጋኝነትህን ለማሳየት ሁኔታዎችህ በሚፈቅዱልህ መጠን በስብከቱ ሥራ የተሟላ ተሳትፎ አድርግ።
11 ሌሎችም የተሟላ ምሥክርነት እንዲሰጡ አበረታቷቸው:- ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች ረዳት አቅኚ ሆነው በማገልገል ሌሎችም እንዲሁ እንዲያደርጉ ሊያበረታቷቸው ይችላሉ። ከሌሎች ጋር አብረው ሲያገለግሉና እረኝነት ሲያደርጉ በዚህ ልዩ የአገልግሎት እንቅስቃሴ ሌሎችም የተሟላ ተሳትፎ እንዲያደርጉ በግል ለመርዳት የሚያስችል ግሩም አጋጣሚ አላቸው። ሁላችንም ይህን ልዩ የአገልግሎት እንቅስቃሴ በሚመለከት አዘውትረን በመጸለይ የተሟላ ምሥክርነት ለመስጠት የምናደርገው የጋራ ጥረት እንዲጠናከር እናድርግ።
12 ሁሉም ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች ጉባኤው በመጋቢትና በሚያዝያ ወራት ለሚደረገው ሰፊ የአገልግሎት እንቅስቃሴ ያደረጋቸውን ዝግጅቶች መደገፍ የሚጠበቅባቸው ቢሆንም የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ የወንጌላዊነቱን ሥራ በማደራጀት በኩል የበለጠ ኃላፊነት አለበት። የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎችን ሲያደራጅ ለአብዛኞቹ አስፋፊዎች አመቺ የሆኑ ቦታዎች፣ ቀኖችና ሰዓታት መምረጥ ያለበት ሲሆን እነዚህ ዝግጅቶች በማስታወቂያ እንዲነገሩ ያደርጋል። ሁሉም የጉባኤው አባላት በሁሉም የአገልግሎቱ ዘርፎች መካፈል እንዲችሉ በቀኑ ውስጥ በተለያዩ ሰዓታት የስምሪት ስብሰባ እንዲደረግ ዝግጅት ማድረግ ይቻላል። እነዚህ የአገልግሎት ዘርፎች በንግድ አካባቢዎች፣ ከመንገድ ወደ መንገድ፣ ከቤት ወደ ቤት፣ መመስከርንና ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግን እንዲሁም የስልክ ምሥክርነት መስጠትን ያካትታሉ። ከዚህም በላይ የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ በእነዚህ ወራት በቂ ጽሑፎች፣ መጽሔቶችና የአገልግሎት ክልሎች መኖራቸውን ማረጋገጥ ይኖርበታል።
13 በመጋቢት ወር የሚበረከተው ጽሑፍ እውቀት መጽሐፍ ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ለማስጀመር ልዩ ጥረት ይደረጋል። የእውቀት መጽሐፍን ለማበርከት የሚረዱ ግሩም የመግቢያ ሐሳቦች በጥር 2002 የመንግሥት አገልግሎታችን አባሪ ላይ ወጥተዋል። በሚያዝያ ደግሞ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ይበረከታሉ። “መጽሔቶችን ለማበርከት ምን ማለት ይቻላል?” በሚለው ርዕስ ሥር የሚወጡትን አቀራረቦች በሚገባ ተጠቀሙባቸው። ሁሉም አስፋፊዎች የተሟላ ምሥክርነት ለመስጠት ይችሉ ዘንድ ጊዜ መድበው ጥሩ ዝግጅት ማድረግ ይኖርባቸዋል።
14 የጉባኤው ራስ በሆነው በክርስቶስ ኢየሱስ አመራር ሥር የመሥራትና ምሥራቹን ለሌሎች የማካፈል መብት በማግኘታችን ምንኛ ተባርከናል! በመጋቢትና በሚያዝያ ወራት በአገልግሎታችን ከምንጊዜውም የበለጠ ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ ኢየሱስ የተሟላ ምሥክርነት እንድንሰጥና እንድንሰብክ የሰጠንን ትእዛዝ እንፈጽም።
[ገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በመጋቢትና በሚያዝያ 2003 ረዳት አቅኚ ሆኖ ለማገልገል የሚያስችሉ የተለያዩ ፕሮግራሞች
ቀን ሰዓታት
ሰኞ 1 2 — — 2 —
ማክሰኞ 1 — 3 — — —
ረቡዕ 1 2 — 5 — —
ሐሙስ 1 — 3 — — —
አርብ 1 2 — — — —
ቅዳሜ 5 4 3 5 6 7
እሁድ 2 2 3 2 2 3
መጋቢት 56 56 54 55 50 50
ሚያዝያ 50 50 51 53 — —
ከእነዚህ ፕሮግራሞች መካከል ከአንተ ሁኔታ ጋር የሚስማማ ይኖር ይሆን?