በሶቪዬት ሕብረት የተፈጸመውን ሁኔታ የሚያሳይ ልብ የሚነካ ፊልም!
ጊዜው ሚያዝያ 1951 ነበር። በቀድሞዋ ሶቪዬት ሕብረት የሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ከነቤተሰቦቻቸው ከያሉበት ተለቅመው በባቡር እየተጫኑ ወደ ሳይቤሪያ ተጋዙ። ኃያሉ የሶቪዬት መንግሥት እነዚህን ምሥክሮች ለማጥፋት ቆርጦ የተነሳው ለምን ነበር? ወንድሞቻችን ለብዙ አሥርተ ዓመታት ያለማቋረጥ ይደርስባቸው የነበረውን ስደት ሊቋቋሙ አልፎ ተርፎም በቁጥር ሊበዙ የቻሉት እንዴት ነው? በሶቪዬት ሕብረት ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በፈተና ወቅት ያሳዩት ጽናት በተሰኘው የቪዲዮ ፊልም ውስጥ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ታገኛላችሁ። በሶቪዬት ሕብረት ያሉ ወንድሞቻችን ስለደረሰባቸው ስደት የሚያሳየው ይህ ልብ የሚነካ ፊልም ምንም ዓይነት መከራ ቢደርስብህ ለይሖዋ ያለህን ታማኝነት ለመጠበቅ ያለህን አቋም ስለሚያጠናክርልህ እንድትመለከተው እንጋብዝሃለን!
እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ ትችላለህ? (1) የይሖዋ ምሥክሮች ለመጀመሪያ ጊዜ በሩስያ ሕጋዊ እውቅና ያገኙት መቼ ነበር? (2) ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊትና በኋላ በሶቪዬት ሕብረት የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥራቸው በሺዎች ሊጨምር የቻለው እንዴት ነው? (3) የይሖዋ ምሥክሮች እምነት ከሌኒን ፍልስፍና ጋር የሚጋጨው እንዴት ነው? (4) ኦፕሬሽን ኖርዝ በመባል የሚታወቀው ዘመቻ ምን ነበር? ስታሊን በዚህ ዘመቻ አማካኝነት ምን ለማከናወን አቅዶ ነበር? (5) ምሥክሮቹ በግዞት መወሰዳቸው ምን ያስከትልባቸዋል? በግዞት ላለመወሰድስ ምን እንዲያደርጉ ይጠየቁ ነበር? (6) ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ወደ ሳይቤሪያ ባደረጉት ረጅም የባቡር ጉዞ እርስ በእርስ ይበረታቱ የነበረው እንዴት ነው? ይህስ አጅበዋቸው የሚሄዱት ወታደሮች በአድናቆት እንዲዋጡ ያደረገው እንዴት ነው? (7) የይሖዋ ምሥክሮች በሳይቤሪያ ምን ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን መቋቋም ነበረባቸው? (8) የይሖዋ ሕዝቦች ለየትኞቹ መንፈሳዊ ዝግጅቶች የላቀ ቦታ ይሰጣሉ? ለምን? (9) ወንድሞቻችን ጽሑፎችን ለማግኘት ሲሉ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ይጥሉ የነበሩት ለምንድን ነው? ባለሥልጣናት ጽሑፎች በምሥክሮቹ እጅ እንዳይገቡ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም ወንድሞች ጽሑፎችን በማግኘት ረገድ የተሳካላቸው እንዴት ነበር? (10) ክሩሽቾቭ በአምላክ ሕዝቦች ላይ የሚሰነዘረውን ጥቃት የገፋበት እንዴት ነበር? (11) የመንግሥት ባለሥልጣናት የምሥክሮቹ ልጆች የነበራቸውን እምነት ለማጥፋት የሞከሩት እንዴት ነበር? (12) ወንድሞቻችን የሚሰደዱበትን ምክንያት በተመለከተ ምን ግንዛቤ ነበራቸው? (2002 የዓመት መጽሐፍ ገጽ 203-204) (13) የሶቪዬት ባለሥልጣናት ያለ የሌለ ኃይላቸውን ተጠቅመው በአምላክ ድርጅት ላይ የሰነዘሩት ጥቃት ካሰቡት ተቃራኒ የሆነ ውጤት ያስከተለባቸው እንዴት ነው? (2002 የዓመት መጽሐፍ ገጽ 220-221) (14) በቀድሞዋ ሶቪዬት ሕብረት የነበሩ ምሥክሮች በአንድ ወቅት እውን ይሆናሉ ብለው ያልጠበቋቸው ምን ነገሮች ሲፈጸሙ አይተዋል? (15) ወንድሞቻችን በፈተና ወቅት እንዲጸኑ ያስቻላቸው ምን ነበር? የፊልሙ የመጨረሻ ክፍል የኤርምያስ 1:19ን እውነተኝነት የሚያሳየው እንዴት ነው? (16) በፈተና ወቅት የታየ ጽናትን ከሚያጎሉት ሕያው ተሞክሮዎች ውስጥ በተለይ አንተን የነካህን ተናገር።