መንፈስን የሚያድስ ሥራ
1 የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ተቀብለው በሥራ ላይ የሚያውሉ ሁሉ የመንፈስ እርካታ ያገኛሉ። (መዝ. 19:7, 8) ይህ መልእክት ከሐሰት ትምህርቶችና ጎጂ ከሆኑ ልማዶች ነጻ የሚያወጣቸው ከመሆኑም በላይ የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ አስተማማኝ ተስፋ እንዲኖራቸው ያደርጋል። ይሁን እንጂ ጥቅም የሚያገኙት መልእክቱን የተቀበሉት ሰዎች ብቻ አይደሉም። የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለሌሎች የሚያካፍሉ ሰዎችም የመንፈስ እርካታ ያገኛሉ።—ምሳሌ 11:25
2 አገልግሎት ኃይል ያድሳል:- ኢየሱስ ስብከትንና ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ የሚያቅፈውን የክርስትናን ቀንበር የሚሸከሙ ሰዎች ‘ለነፍሳቸው እረፍት እንደሚያገኙ’ ተናግሯል። (ማቴ. 11:29) እርሱም ለሌሎች በመመስከሩ ኃይሉ የታደሰ ሲሆን አገልግሎት እንደ ምግብ ሆኖለት ነበር። (ዮሐ. 4:34) ሰባ የሚያህሉ ደቀ መዛሙርቱን ምሥራቹን እንዲሰብኩ በላካቸው ወቅት ይሖዋ ጥረታቸውን ስለባረከላቸው ተደስተው ነበር።—ሉቃስ 10:17
3 ዛሬም በተመሳሳይ በርካታ ክርስቲያኖች በስብከቱ ሥራ በመካፈላቸው መንፈሳቸው ይታደሳል። አንዲት እህት እንዲህ ብላለች:- “አገልግሎት ሕይወቴን አቅጣጫ ስለሚያስይዝልኝና ዓላማ እንዲኖረኝ ስለሚያደርግ እረፍት ያስገኛል ለማለት እችላለሁ። በአገልግሎት ስካፈል የግል ችግሬንና የዕለት ተዕለት ጭንቀቴን እረሳለሁ።” ሌላ ቀናተኛ አገልጋይ ደግሞ “አገልግሎት . . . በየዕለቱ ይሖዋ እውን እንዲሆንልኝ እንዲሁም በሌላ በምንም መንገድ ማግኘት የማልችለውን ሰላምና ይህ ነው የማይባል ውስጣዊ ደስታ እንዳገኝ ይረዳኛል” ብላለች። ከአምላክ ጋር ‘አብሮ መሥራት’ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!—1 ቆሮ. 3:9
4 የክርስቶስ ቀንበር ልዝብ ነው:- ኢየሱስ “ተጋደሉ” በማለት ቢያሳስበንም ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር እንድናደርግ አይጠብቅብንም። (ሉቃስ 13:24) እንዲያውም ‘ቀንበሩን አብረነው እንድንሸከም’ ፍቅራዊ ግብዣ አቅርቦልናል። (ማቴ. 11:29 NW የግርጌ ማስታወሻ) ከአስቸጋሪ ሁኔታዎች ጋር እየታገሉ የሚኖሩ ክርስቲያኖች፣ በሙሉ ነፍሳቸው የሚያቀርቡት አገልግሎት መጠኑ ውስን ቢሆንም አምላክን ከልብ እንደሚያስደስተው እርግጠኞች መሆን ይችላሉ።—ማር. 14:6-8፤ ቆላ. 3:23
5 ለስሙ ብለን የምናከናውነውን ማንኛውንም ነገር በአድናቆት የሚመለከትን አምላክ ማገልገል ምንኛ መንፈስን የሚያድስ ነው! (ዕብ. 6:10) ምንጊዜም አቅማችን የፈቀደውን ያህል እርሱን ለማገልገል ጥረት እናድርግ።