እናንተ ወጣቶች—ለሚመጣው ዘመን መልካም መሠረት ጣሉ
1. ክርስቲያን ወጣቶች ጠንካራ እምነት መገንባት የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?
1 የላቀ ግምት የምትሰጠው ነገር ምንድን ነው? ብዙውን ጊዜ የምታስበው ስለምን ጉዳይ ነው? በዋነኛነት ትኩረት የምትሰጠው ለጊዜያዊ ነገሮች ነው? ወይስ ዘላቂ ለሆኑና አምላክ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ለሚያተኩሩ ነገሮች? (ማቴ. 6:24, 31-33፤ ሉቃስ 8:14) ከአብርሃምና ከሙሴ ምሳሌ መማር እንደሚቻለው አምላክ ወደፊት እንደሚያመጣቸው ቃል በገባቸው ነገሮች ላይ ተስፋ መጣል ጠንካራ እምነት ይጠይቃል። (ዕብ. 11:8-10, 24-26) ታዲያ ወጣቶች እንዲህ ያለ እምነት ማዳበርም ሆነ ‘ለሚመጣው ዘመን ለራሳችሁ መልካም መሠረት’ መጣል የምትችሉት እንዴት ነው?—1 ጢሞ. 6:18, 19
2. ንጉሥ ኢዮስያስ ከተወው ምሳሌ ምን እንማራለን?
2 ይሖዋን ፈልጉ:- ቤተሰባችሁ በሚያደርጋቸው መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች በንቃት የመካፈል ልማድ ካላችሁ በእርግጥ ልትመሰገኑ ይገባል። ይሁንና እንዲህ ያለው ልማድ ብቻውን ጠንካራ እምነት ያስገኝልናል ብላችሁ አትጠብቁ። ‘የአምላክን እውቀት’ ለማግኘት በግላችሁ ይሖዋን መፈለግ ይኖርባችኋል። (ምሳሌ 2:3-5፤ 1 ዜና 28:9) ወጣቱ ንጉሥ ኢዮስያስ በዚህ ረገድ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። ያደገው ጥሩ መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ በማያስችል ሁኔታ ውስጥ ቢሆንም በ15 ዓመቱ “የአባቱን የዳዊትን አምላክ ይፈልግ ጀመር።”—2 ዜና 34:3
3. በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን ወጣቶች ይሖዋን መፈለግ የሚችሉት እንዴት ነው?
3 ይሖዋን መፈለግ የምትችሉት እንዴት ነው? የምታምኑበትን ነገር በጥሞና በመመርመርና እውነት መሆኑን ‘ፈትናችሁ በማወቅ’ ነው። (ሮሜ 12:2) ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ደምን አስመልክቶ ምን እንደሚል ወይም የአምላክ መንግሥት በሰማይ መግዛት የጀመረው በ1914 መሆኑን ማስረጃ እየጠቀሳችሁ ማስረዳት ትችላላችሁ? ለሚመጣው ዘመን መልካም መሠረት ለመጣል ትክክለኛውን ‘እውነት ማወቅ’ በእጅጉ ያስፈልጋል።—1 ጢሞ. 2:3, 4
4. ያልተጠመቁ አስፋፊዎች መንፈሳዊ እድገታቸው በግልጽ እንዲታይ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?
4 ኢዮስያስ አምላክን ለመፈለግ ያደረገው ጥረት መልካም ውጤት አስገኝቶለታል። ገና 20 ዓመት ሳይሞላው የሐሰት አምልኮን ከምድሪቱ ለማጥፋት በድፍረት እርምጃ ወስዷል። (2 ዜና 34:3-7) በተመሳሳይ የአንተም መንፈሳዊ እድገት ሊታይ የሚችለው በምታደርጋቸው ነገሮች ነው። (1 ጢሞ. 4:15) ያልተጠመቅህ አስፋፊ ከሆንክ የአገልግሎትህን ጥራት ለማሻሻል ጥረት አድርግ። ጽሑፎች ማበርከት ብቻውን በቂ እንደሆነ አይሰማህ። በአገልግሎት ላይ መጽሐፍ ቅዱስን የመጠቀም፣ አድማጮችህን ጥሩ አድርጎ የማስረዳትና የሰዎችን ፍላጎት የማሳደግ ግብ ይኑርህ። (ሮሜ 12:7) እንዲህ ማድረግህ በመንፈሳዊ እንድታድግ ይረዳሃል።
5. የተጠመቁ ክርስቲያኖች አገልግሎታቸውን ማስፋት የሚችሉባቸው መንገዶች ምን ምን ናቸው?
5 ለይሖዋ ምርጣችሁን ስጡ:- ራስህን ለይሖዋ መወሰንህን ለማሳየት በውኃ ስትጠመቅ የአምላክ አገልጋይ እንድትሆን ተሹመሃል። (2 ቆሮ. 3:5, 6) ይህም ይሖዋን በሙሉ ጊዜህ ለማገልገል የሚያስችል አጋጣሚ ከፍቶልሃል። አቅኚነት፣ በቤቴል ማገልገልና በመንግሥት አዳራሽ ግንባታ መካፈል ከሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ የሚመደቡ ናቸው። ሌላ ቋንቋ መማርና የምሥራቹ አገልጋዮች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉባቸው ቦታዎች ተዛውሮ ማገልገልም አገልግሎትህን ማስፋት የምትችልባቸው ሌሎች መንገዶች ናቸው።
6. ሁላችንም ለወደፊት ሕይወታችን መልካም መሠረት መጣል የምንችለው እንዴት ነው?
6 እርግጥ ነው፣ ሁሉም አስፋፊዎች በእነዚህ የአገልግሎት መብቶች ለመካፈል ራሳቸውን ማቅረብ ይችላሉ ማለት አይደለም። ሆኖም ሁላችንም ለይሖዋ ምርጣችንን ልንሰጠው እንችላለን። (ማቴ. 22:37) የምትገኝበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ይሖዋን ማገልገልን በሕይወትህ ውስጥ ዋነኛ ግብህ አድርገው። (መዝ. 16:5) እንዲህ በማድረግ ለወደፊት ሕይወትህ መልካም መሠረት ትጥላለህ።