ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ማዳበር
1. አንዲት እህት መንፈሳዊ ልማዷን በተመለከተ ምን ነገር ተገንዝባለች?
1 “ላለፉት 20 ዓመታት ገደማ እውነት ውስጥ የቆየሁት እንዲያው ስብሰባ በመሄድና መስክ አገልግሎት በመካፈል ብቻ ነበር” በማለት አንዲት ክርስቲያን እህት ሳትሸሽግ ተናግራለች። ይሁን እንጂ በመቀጠል እንዲህ ብላለች:- “እነዚህ ነገሮች አስፈላጊ ቢሆኑም ሁኔታዎች እየከበዱ ሲሄዱ ስብሰባ በመገኘትና በማገልገል ብቻ ጸንቼ መቆም እንደማልችል ተረዳሁ። . . . ይሖዋን በሚገባ ለማወቅና እርሱን ለማፍቀር እንዲሁም ልጁ ያደረገልንን ነገር በአድናቆት ለመመልከት አስተሳሰቤን ማስተካከልና ትርጉም ያለው የግል ጥናት ማድረግ እንዳለብኝ ተገንዝቤአለሁ።”
2. ከይሖዋ ጋር ያለንን ወዳጅነት ጠብቀን ማቆየታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
2 ከይሖዋ ጋር የጠበቀ የግል ዝምድና መገንባት ጥረት ይጠይቃል። በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች በዘልማድ መካፈል ብቻውን በቂ አይደለም። አዘውትረን ከይሖዋ ጋር በጸሎት የማንነጋገር ከሆነ ከጊዜ በኋላ ዝምድናችን በአንድ ወቅት የቅርብ ጓደኛችን ከነበረ አሁን ግን እምብዛም ከማናገኘው ሰው ጋር የሚኖረን ዓይነት ይሆናል። (ራእይ 2:4) የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና ጸሎት ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንድናዳብር እንዴት ሊረዳን እንደሚችል እስቲ እንመርምር።—መዝ. 25:14
3. ወደ አምላክ ለመቅረብ ምን ዓይነት የግል ጥናት ሊኖረን ይገባል?
3 ጸሎትና ማሰላሰል የግድ አስፈላጊ ናቸው:- በግል ጥናት አማካኝነት ልባችንን መመገብ ከፈለግን በጥናት ርዕሱ ላይ ያሉትን ዋና ዋና ነጥቦች በማስመርና ጥቅሶችን በማንበብ ብቻ አናበቃም። ትምህርቱ ስለ ይሖዋ መንገዶች፣ መሥፈርቶችና ባሕርያት በሚያሳውቀን ነገር ላይ ማሰላሰል ይኖርብናል። (ዘጸ. 33:13) መንፈሳዊ ቁም ነገሮችን መረዳት መቻል ውስጣዊ ስሜታችንን የሚነካ ከመሆኑም ሌላ ስለ ሕይወታችን እንድናስብ ያነሳሳናል። (መዝ. 119:35, 111) የግል ጥናት የምናደርግበት ዓላማ ወደ ይሖዋ ለመቅረብ መሆን አለበት። (ያዕ. 4:8) በትኩረት ለማጥናት ጊዜና አመቺ ሁኔታ አስፈላጊ ነው። በዚህ ረገድ ቋሚ ልማድ ለመከተል ራሳችንን መገሰጽ ይኖርብናል። (ዳን. 6:10) ጊዜህ የተጣበበ ቢሆንም እንኳ ግሩም በሆኑት የይሖዋ ባሕርያት ላይ ለማሰላሰል በየቀኑ ጊዜ ትመድባለህ?—መዝ. 119:147, 148፤ 143:5
4. የግል ጥናት ከመጀመራችን በፊት መጸለያችን ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንድናዳብር የሚረዳን እንዴት ነው?
4 ትርጉም ያለው የግል ጥናት ለማድረግ ልባዊ ጸሎት ማቅረብ ትልቅ ድርሻ አለው። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ውስጣዊ ስሜታችንን እንዲነካና ‘በማክበርና በፍርሃት እግዚአብሔርን እንድናመልክ’ እንዲያነሳሳን የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ያስፈልገናል። (ዕብ. 12:28) በመሆኑም ማጥናት ከመጀመራችን በፊት ምንጊዜም ይሖዋ መንፈሱን እንዲሰጠን መለመን ይኖርብናል። (ማቴ. 5:3) በቀረቡት ጥቅሶች ላይ ስናሰላስልባቸውና የይሖዋ ድርጅት በሚያቀርብልን ጽሑፎች ስንጠቀም ልባችንን ለይሖዋ ክፍት እናደርጋለን። (መዝ. 62:8) በዚህ መንገድ የምናከናውነው ጥናት የአምልኳችን ክፍል ከመሆኑም በላይ ለይሖዋ ያደርን መሆናችንን የምናሳይበትና ከእርሱ ጋር ያለንን ወዳጅነት የምናጠናክርበት አጋጣሚ ነው።—ይሁዳ 20, 21
5. በየቀኑ በአምላክ ቃል ላይ ለማሰላሰል ጊዜ መዋጀታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
5 እንደ ማንኛውም ዓይነት ዝምድና ሁሉ ከይሖዋ ጋር ያለን ዝምድናም በሕይወት ዘመናችን በሙሉ እየጎለበተ እንዲሄድ ያለማቋረጥ ልንንከባከበው ይገባል። በመሆኑም እኛ ወደ አምላክ ከቀረብን እርሱም ወደ እኛ እንደሚቀርብ በመገንዘብ በየቀኑ ወደ እርሱ ለመቅረብ ጊዜ እንዋጅ።—መዝ. 1:2, 3፤ ኤፌ. 5:15, 16