በተገቢው ጊዜ የቀረበ መንፈሳዊ ምግብ
1 ሉዓላዊ ጌታ የሆነው ይሖዋ “እህሉን እጠራለሁ፤ አበዛዋለሁም፤ ራብንም አላመጣባችሁም” በማለት ተናግሯል። (ሕዝ. 36:29) እነዚህ ትንቢታዊ ቃላት በዛሬው ጊዜ በሚገኙ የአምላክ ሕዝቦች ላይ ተግባራዊ ሆነዋል። በምሳሌያዊ አነጋገር ይሖዋ ሕይወት ሰጪ የሆነው እህል ለሕዝቡ እንዲትረፈረፍላቸው አድርጓል። በአውራጃ ስብሰባዎቻችን አማካኝነት በጊዜው የሚቀርብልን መንፈሳዊ ምግብ ይህንን በሚገባ ይመሠክራል።
2 ይሖዋ በ1931 በኮሎምበስ፣ ኦሃዮ በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ሕዝቦቹ የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን አዲስ ስም እንዲያገኙ አደረገ። (ኢሳ. 43:10-12) በ1935 በራእይ 7:9-17 ላይ የተገለጹት እጅግ ብዙ ሰዎች ማንነት በትክክል ታወቀ። በ1942 ወንድም ኖር “ሰላም—ዘላቂ ሊሆን ይችላል?” የተሰኘውን ንግግር አቀረበ። ይህ ንግግር ምሥክሮቹ ዓለም አቀፉን የስብከት ሥራ በተጠናከረ መልኩ እንዲያከናውኑ ያነሳሳቸው ከመሆኑም በላይ የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት እንዲቋቋም መንገድ ጠርጓል። አንዳንዶቹ የአውራጃ ስብሰባዎች ለየት ባለ መንገድ የሚታወሱ ቢሆንም በሁሉም ስብሰባዎች ላይ ገንቢና ወቅታዊ የሆነ መንፈሳዊ ማዕድ ተትረፍርፎ ቀርቧል።—መዝ. 23:5፤ ማቴ. 24:45
3 በደንብ እየተመገብህ ነው? በዙሪያችን ምግብ ተትረፍርፎ እያለም ለመመገብ ጥረት ካላደረግን ልንራብ እንችላለን። (ምሳሌ 26:15) በመንፈሳዊ ሁኔታም ተመሳሳይ ነገር ሊያጋጥመን ይችላል። በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ አንዳንዶች ሳያስፈልግ ወዲያና ወዲህ ሲዘዋወሩ ወይም ስብሰባው እየተካሄደ ከሌሎች ጋር ሲያወሩ ተስተውለዋል። ከወንድሞቻችን ጋር የሚያንጽ ጭውውት ማድረግ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የስብሰባው ክፍል ቢሆንም ይህን ማድረግ የሚገባን ስብሰባው ከመጀመሩ በፊት ወይም ካበቃ በኋላ ነው። (መክ. 3:1, 7) ሁላችሁም በመግቢያ መዝሙሩና በጸሎቱ ላይ ከልባችሁ መካፈል እንድትችሉ ስብሰባው ከመጀመሩ በፊት በቦታችሁ እንድትቀመጡ እናበረታታችኋለን። በዚህ ዓመት ዓርብና ቅዳሜ ፕሮግራሙ ጠዋት በ3:30 ጀምሮ በ11:05 የሚያበቃ ሲሆን እሁድ ደግሞ በ3:30 ጀምሮ በ10:05 ያበቃል። ስብሰባው በሚካሄድበት ወቅት ቁጭ ብለን በትኩረት ካላዳመጥን ጠቃሚ የሆነ ነጥብ ሊያመልጠን ይችላል። የአውራጃ ስብሰባው የክፍል ኃላፊዎችና ሥራ የተሰጣቸው ወንድሞች አንዳንድ ጊዜ ፕሮግራሙ እየተካሄደ እያለ ስብሰባውን የሚመለከቱ ጉዳዮችን አንስተው መወያየት ያስፈልጋቸው ይሆናል። ከዚህ ውጪ ግን ፕሮግራሙን በትኩረት በመከታተል ረገድ አርዓያ ሊሆኑ ይገባል። ማናችንም ብንሆን የሚቀርበው መንፈሳዊ ምግብ ሊያመልጠን አይገባም።—1 ቆሮ. 10:12፤ ፊልጵ. 2:12
4 ሕዝበ ክርስትና ከምታቀርበው የማይጠቅም የሐሰት ትምህርት በተቃራኒ ይሖዋ አትረፍርፎ የሚሰጠን መንፈሳዊ እውነት በጣም ያስደስተናል! (ኢሳ. 65:13, 14) ለዚህ ማዕድ ‘የምናመሰግን መሆናችንን’ የምናሳይበት አንዱ መንገድ የአውራጃ ስብሰባውን ከይሖዋ የምንማርበት አጋጣሚ እንደሆነ አድርገን በመመልከት ነው። (ቆላ. 3:15) ከተናጋሪው ይልቅ በንግግሩ ላይ ትኩረት በማድረግ መልእክቱ ከታላቁ ‘አስተማሪያችን’ እንደሚመጣ አድርጋችሁ ተመልከቱት። (ኢሳ. 30:20, 21፤ 54:13) በጥሞና በማዳመጥ ቁልፍ ነጥቦችን አጠር አድርጋችሁ በማስታወሻ ያዙ። በእያንዳንዱ ዕለት ምሽት የፕሮግራሙን ዋና ዋና ነጥቦች ከልሱ። የተማራችሁትንም ተግባራዊ አድርጉ።
5 ስብሰባውን የምናደርገው በስደተኞች መጠለያ ካምፕም ይሁን በጦርነት በሚታመስ አገር ወይም ሰፊና ሰላማዊ በሆነ አካባቢ ከአርማጌዶን በፊት የምናደርገው እያንዳንዱ የአውራጃ ስብሰባ በሰይጣን ላይ ድል ለመቀዳጀት አጋጣሚ ይሰጠናል! አንድነት ያለው የወንድማማች ማኅበር አባላት እንደመሆናችን በአንድ ላይ ሆነን በአውራጃ ስብሰባዎቻችን ላይ መገኘት ያስደስተናል። (ሕዝ. 36:38) አፍቃሪው አምላካችን ይሖዋ በዚህ ዓመት በሚደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይም ‘ምግባችንን በተገቢው ጊዜ እንደሚሰጠን’ እርግጠኞች ነን።—ሉቃስ 12:42
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
1. ሕዝቅኤል 36:29 በዛሬው ጊዜ ፍጻሜውን እያገኘ ያለው እንዴት ነው?
2. ይሖዋ በአውራጃ ስብሰባዎች አማካኝነት በተገቢው ጊዜ መንፈሳዊ ምግብ ያቀረበው እንዴት ነው?
3. በአውራጃ ስብሰባ ላይ ከሚቀርበው መንፈሳዊ ግብዣ ጥቅም ለማግኘት ምን ማድረግ አለብን?
4. ይሖዋ አትረፍርፎ ለሰጠን ማዕድ አመስጋኝ መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
5. በአውራጃ ስብሰባዎቻችን ለመደሰት የሚያበቃ ምን ምክንያት አለን?
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የሥዕል መግለጫ]
የይሖዋን ማዕድ እንደምታደንቁ አሳዩ
◼ በጥሞና አዳምጡ
◼ ቁልፍ ነጥቦችን በማስታወሻ ያዙ
◼ በእያንዳንዱ ዕለት ምሽት የፕሮግራሙን ዋና ዋና ነጥቦች ከልሱ
◼ የተማራችሁትን ተግባራዊ አድርጉ